ዋትስአፕ ደንበኞቹ ያለ ስልክ መልዕክት እንዲላላኩ ሊያስችል ነው

ዋትስአፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ዋትስአፕ ለመጀመሪያ ግዜ ተገልጋዮቹች ስልካቸውን ሳይጠቀሙ መልዕክት እንዲለዋወጡ የሚያስችል ዘዴ ተገባራዊ ለማድረግ ሙከራ ጀመረ።

በአሁኑ ወቅት ዋትስአፕን በዴስክቶፕ መተግበሪያ አልያም በድረ-ገጹ ላይ ለመጠቀም ግዴታ ደንበኞች በስልካቸው ላይ ያለው የዋትስአፕ መተግበሪያ ከኢንተርኔት መገናኘት እና መልዕክት መቀበል መቻል አለበት።

ነገር ግን አዲሱ ስርዓት ተጠቃሚዎች ስልካቸው ባትሪ ጨርሶም መልዕክቶችን እንዲልኩ እና እንዲቀበሉ ያስችላቸዋል።

እንደ ኮምፒዮተር እና ታብሌት ያሉ እስከ አራት የሚደርሱ ሌሎች መሳሪያዎች በአንድ ጊዜ አብረው ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ ብሏል ዋትስአፕ።

አገልግሎቱ ለሁሉም ተጠቃሚዎች ይፋ ከመደረጉ በፊት ለሙከራ አሰራሩ ለተወሰነ ቡድን ይለቀቃል። በሂደትም አፈፃፀሙን ለማሻሻል እና ማስተካከያዎች ለመጨመር ታቅዷል።

ከሁለት ቢሊዮን በላይ ተጠቃሚዎች ያሉት ዋትስአፕ 'ከላኪው እስከ ተቀባዩ' ድረስ የሚላኩ መልዕክቶች በሚስጥር የሚጠበቁ ናቸው ማለቱ መተግበሪያውን ተመራጭ ያደረገው ሲሆን አሁንም በአዲሱ ስርዓት ይህ አሰራር እንደሚቀጥል ዋትስአፕ አስታውቋል።

ዋና ተቀናቃኙ ሲግናልን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የመልእክት መላላኪያ መተግበሪያዎች ቀድሞውኑ እንደዚህ ዓይነት ባህሪ አላቸው።

ይህን አማራጭ በቢሊዮን የሚቆጠሩ የዋትስአፕ ተገልጋዮች ለረጅም ጊዜ ሲጠይቁ ቆይተዋል።

በፌስቡክ ባለቤትነት የሚተዳደረው ዋትስአፕ አሁን የሚደረገው ማሻሸያ የዋትስአፕን የሶፍትዌር ዲዛይን በድጋሚ መከለስ የሚጠይቅ ነው።

ነገር ግን በኮምፒውተር ፀረ-ቫይረስ ኩባንያው ኢሴት ውስጥ የደህንነት ባለሙያ የሆኑት ጃክ ሙር እንደሚሉት አንድ መተግበሪያ ደህንነቱ ምንም ያህል ጠንካራ ቢሆንም በብዙ መሣሪያዎች ላይ መልዕክቶች መቀመጣቸው አሳሳቢ ሊሆን ይችላል ብለዋል።

"የቤት ውስጥ ጥቃት አድራሾች እና ሰላዮች የግል ግንኙነቶችን ለማግኘት ተጨማሪ ነጥቦችን በመፍጠር ይህንን አዲስ ባህሪ ለራሳቸው ጥቅም የማዋል እድል ሊኖራቸው ይችላል" ሲሉም ተናግረዋል።

በተጨማሪም ማህበራዊ ኢንጂነሪንግ "ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ" ስጋት ነው ያሉት ኃላፊው አላግባብ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችልበትን ሁኔታ መከታተል የተጠቃሚው ኃላፊነት ነው ብለዋል።