ባይደን እና መርክል የሩስያን ጠብ አጫሪነት ለመግታት አንድ ላይ እንቆማለን አሉ

ባይደን እና መርክል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሜሪካ እና ጀርመን የሩስያን ጠብ ጫሪነት ለመግታት በአንድነት እንደሚቆሙ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ተሰናባቿን መራሔተ መንግሥት አንጌላ መርክልን በዋሽንግተን ሲቀበሉ ተናግረዋል፡፡

ባይደን ከሩስያ እስከ ጀርመን በተዘረጋው የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ ዙሪያ ያላቸውን ስጋት ለመርክል እንደነገሯቸው ገልጸው፤ ሁለቱም ሞስኮ ኃይልን እንደ መሣሪያ እንድትጠቀም ሊፈቀድላት እንደማይችል ተስማምተዋል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት እንዳሉት ሁለቱ አጋር አገራት በቻይና የሚደረጉ ፀረ ዴሞክራሲያዊ እርምጃዎችንም ይቃወማሉ፡፡

ከአራት የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ጋር የሠሩት መርክል ሥልጣናቸውን ሊለቀቁ እየተዘጋጁ ነው፡፡

ባይደን ሐሙስ ከመርክል ጋር በጋራ ለጋዜጠኞች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "እኛ በኔቶ ያሉንን አጋሮቻችንን ከሩስያ ተግባር ለመከላከል አንድ ላይ እንቆማለን። መቆማችንንም እንቀጥላለን" ብለዋል።

ሁለቱ መሪዎች ሊጠናቀቅ በተቃረበው እና 11 ቢሊዮን ዶላር ገደማ በሚፈጀው የኖርድ ስትሪም 2 የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ ቧንቧ ላይ ዓይን ለዓይን አለመተያየታቸውን አምነዋል፡፡

ኋይት ሃውስ ሩስያ ቧንቧውን በዩክሬይን እና በሌሎች ጎረቤቶቿ ላይ ልትጠቀምበት እንደምትችል አስታውቋል፡፡

በቅርቡ በኖርድ ስትሪም 2 ላይ ማዕቀብ የጣሉት ባይደን "ጥሩ ጓደኞች ላይስማሙ ይችላሉ" ብለዋል፡፡

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት አክለውም "ቻይናም ሆነች ሌላ አገር ነፃ እና ግልጽ ማኅበረሰብን ለማዳከም ሲሠሩ ስናይ ለዴሞክራሲያዊ መርሆዎች እና ለሰብዓዊ መብቶች እንቆማለን" ብለዋል፡፡

ጀርመን እና ቻይና ጠንካራ የንግድ አጋር ቢሆኑም በሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ አንዳንድ ጊዜ በርሊን ቤጂንግን ትተች ነበር፡፡

ባይደን በተጨማሪም ፕሬዚዳንቷ ከተገደሉ በኋላ ሁከት እየተባባሰባት በሄደው ሄይቲ አሜሪካ ወታደሮቿን ለመላክ "በዚህ ጊዜ" ዝግጁ አለመሆኗን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡

በኩባ እየተካሄደ ስላለው ተቃውሞ ተጠይቀውም ባይደን "የከሸፈችው አገር ዜጎቿን እያፈነች ነው" ብለዋል፡፡

"ኮሚኒዝም የከሸፈ ሥርዓት ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ የወደቀ ነው፡፡ ሶሻሊዝምን ጠቃሚ ሆኖ አላየውም" ብለዋል፡፡

ሁለቱም መሪዎች ለሰዓታት የዘለቀ ስብሰባቸውን ወዳጃዊነት አጽንኦት የሰጡት ሲሆን፤ መርክል በተደጋጋሚ ፕሬዝዳንቱን "ወዳጄ" ብለዋቸዋል፡፡

መርክል በጀርመን በከባድ ጎርፍ ሕይወታቸውን ላጡ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ሃዘናቸውን ገልጸዋል፡፡

የጀርመኗ መራሔተ መንግሥት ከባይደን በፊት ከነበሩት መሪ ዶናልድ ትራምፕ ጋር ቀዝቃዛ ግንኙነት የነበራቸው ሲሆን፤ በሥልጣን ዘመናቸው ፕሬዝዳንት ከነበሩት ከጆርጅ ቡሽ እና ከባራክ ኦባማ ጋርም አልፎ አልፎም ውጥረት ታይቷል፡፡

እአአ በ2005 መራሔተ መንግሥት ሆነው የተሾሙት መርክል፤ በመስከረም ወር በሚካሄደው ምርጫ እንደገና አይወዳደሩም፡፡ ፓርቲያቸው ክርስቲያን ዴሞክራቲክ ዩኒየን ከሕዝብ በተሰበሰበ ድምጽ ይመራል፡፡