እስላማዊ አብዮታዊያንን ያንቀጠቀጠው የኢራን ተቃውሞ እንዴት ሊስፋፋ ቻለ?

የኢራንን መንግሥት የሚቃወሙ ሰልፈኞች አደባባይ ወጥተዋል።

የፎቶው ባለመብት, MAHSA / Middle East Images / AFP via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኢራንን መንግሥት የሚቃወሙ ሰልፈኞች አደባባይ ወጥተዋል።

ኢራን ውስጥ ባለፉት 47 ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ ተቃውሞ ተቀጣጥሏል። የኢራንን መንግሥት የሚቃወሙ ሰልፈኞች አደባባይ ወጥተዋል።

ተቃውሞው በተለያዩ የኢራን ከተሞች ተስፋፍቷል። መንግሥት በተቃዋሚ ሰልፈኞች ላይ እርምጃ መውሰዱን የሚቀጥል ከሆነ "በኢራን ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወሰድ" የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስጠንቅቀዋል።

አሜሪካ ኢራናውያንን ለመርዳት "በተጠንቀቅ እየተጠባበቀች ነው" ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

የኢራን ባለሥልጣናት በምላሹ በቀጣናው ያሉ የአሜሪካ አጋሮች ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ዝተዋል።

በኢራን ተቃውሞ ሲነሳ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ለመሆኑ የአሁኑ ተቃውሞ ከዚህ ቀደም ከነበሩት በምን ይለያል?

ተንታኞች እንደሚሉት የአሁኑ ተቃውሞ ባልተጠበቀ ሁኔታ መጠነ-ሰፊ ሆኗል።

የማኅበረሰብ ሳይንስ አጥኚ ኤሊ ኮራሳንድፋር እንደሚሉት ተቃውሞው በዋነኞቹ የኢራን ከተሞች ብቻ ሳይሆን በአነስተኛ ከተሞችም ጭምር እየተካሄደ ይገኛል።

"የእነዚህን አነስተኛ ከተሞች ስም ብዙዎች ከዚህ ቀደም ሰምተው አያውቁም" ሲሉ የተቃውሞውን መስፋፋት ያስረዳሉ።

ተቃውሞው በዋነኛ የኢራን ከተሞች ብቻ ሳይሆን በአነስተኛ ከተሞችም እየተካሄደ ይገኛል።
የምስሉ መግለጫ, ተቃውሞው በዋነኛ የኢራን ከተሞች ብቻ ሳይሆን በአነስተኛ ከተሞችም እየተካሄደ ይገኛል።

በአውሮፓውያኑ 2009 'ግሪን ሙቭመንት' የተሰኘ ተቃውሞ ተነስቶ ነበር። መካከለኛ መደብ ላይ በሚገኙ ኢራናውያን የተነሳው ይህ ንቅናቄ ከምርጫ መጭበርበር ጋር የተያያዘ ነበር።

ተቃውሞው ሰፊ ቢሆንም በዋነኛ ከተሞች ውስጥ ብቻ የተካሄደ ነበር።

በአውሮፓውያኑ 2017 እና 2019 የተነሱ ተቃውሞዎች ድሃ ኢራናውያን በሚኖሩባቸው አካባቢዎችም ተስፋፍተዋል።

በቅርብ ጊዜ ከተነሱ የኢራን ተቃውሞዎች መካከል የ2022ቱ በዋነኛነት ይጠቀሳል።

የ22 ዓመቷ ማሳ አሚኒ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሳለች ከሞተች በኋላ ነበር ተቃውሞው የተነሳው። ማሳ በኢራን የሞራል ፖሊስ የታሰረችው ሒጃብ ከለበሰችበት መንገድ ጋር በተያያዘ ነበር።

ከማሳ ሞት በኋላ ተቃውሞው ተቀጣጥሎ ቀጥሏል።

አሁን የተነሳው ተቃውሞ ከዚህ ቀደም ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ሰፊ ሲሆን፤ ለተከታታይ ቀናት የዘለቀም ነው።

በቅርብ ጊዜ ከተነሱ የኢራን ተቃውሞዎች መካከል የ2022ቱ በዋነኛነት ይጠቀሳል።

የፎቶው ባለመብት, Ameer Alhalbi/Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በቅርብ ጊዜ ከተነሱ የኢራን ተቃውሞዎች መካከል የ2022ቱ በዋነኛነት ይጠቀሳል። የ22 ዓመቷ ማሳ አሚኒ በፖሊስ ይዞታ ሥር ካለች ከሞተች በኋላ ነበር ተቃውሞው የተነሳው።

'ሞት ለአምባገነኑ'

በ2022 እንደተነሳው ተቃውሞ ሁሉ የአሁኑም ተቃውሞ አንድን አስተዳደራዊ ግድፈት መነሻው አድርጎ ጠቅላላ የሥርዓት ለውጥ እንዲመጣ ይጠይቃል።

"የ2022 ንቅናቄ መነሻው የሴቶች ጉዳይ ነበር። ጎን ለጎን ሌሎችም ጉዳዮች ተነስተዋል። 2025 ማገባደጃ ላይ የተነሳው ተቃውሞ መነሻው የምጣኔ ሃብት ጉዳይ ቢሆንም በአጭር ጊዜ ውስጥ ሌሎች ጉዳዮችንም የሚዳስስ ሆኗል" ሲሉ የማኅበራዊ ሳይንስ አጥኚዋ ያብራራሉ።

የኢራን መገበያያ ገንዘብ ሊያል ከአሜሪካ ዶላር አንጻር ምንዛሬው መዋዠቁን በመቃወም በቴህራን የባዛር ነጋዴዎች የሥራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው ተቃውሞው የተቀሰቀሰው።

ተቃውሞው በብዛት ድሃ ኢራናውያን ወደሚኖሩበት የአገሪቱ ምዕራባዊ ክፍል ተስፋፋ። በ2022 የተነሳው ተቃውሞ በተመሳሳይ መንገድ ተስፋፍቶ ነበር።

ከፍተኛ ተቃውሞ የተደረገባቸው ከተሞች ኢላም እና ሎርስታን ናቸው።

ተቃውሞው ከመነሳቱ በፊት ታኅሣሥ ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢራናውያን በዋጋ ንረት ተፈትነዋል።

ይህም መካከለኛው መደብ ላይ የሚገኙ ኢራናውያንን ይጨምራል። በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች አደባባይ የወጡትም ለዚህ ነው።

'ሞት ለአምባገነኑ' ሲሉ በአደባባይ ተቃውሟቸውን አስተጋብተዋል። የኢራን ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኒ ከሥልጣን እንዲነሱም ጠይቀዋል።

ከአገራቸው ሸሽተው የሚኖሩት ረዛ ፓህቫሊ ከተቃውሞው ዘዋሪዎች አንዱ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከአገራቸው ሸሽተው የሚኖሩት ረዛ ፓህቫሊ ከተቃውሞው ዘዋሪዎች አንዱ ናቸው።

የፓህላቪ ሚና

በ2022 የተነሳው ተቃውሞ መሪ አልነበረውም። ብዙም ሳይቆይ ከስሟል።

አሁን የተነሳው ተቃውሞ ግን መሪዎች አሉት። ከአገራቸው ሸሽተው የሚኖሩት ሬዛ ፓህቫሊ ከተቃውሞው ዘዋሪዎች አንዱ ናቸው።

ሬዛ ፓህቫሊ በአውሮፓውያኑ 1979 ከኢራን የተባረሩት ሻህ ልጅ ናቸው።

ሬዛ ፓህቫሊ ከኢራን ርቀው ቢኖሩም ለተቃውሞው አቅጣጫ ለመቀየስ እየሞከሩ ነው። ተቃውሞው ዘልቆ የቀጠበለት አንደኛው ምክንያት ይሄ ሊሆን ይችላል።

በተቃውሞው ፓህላቪ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ የሚጠይቁ ድምጾች ተስተጋብተዋል።

ፓህላቪ በአሜሪካ በስደት እየኖሩ ሳለ ራሳቸውን የኢራን ሻህ (ንገሥ) አድርገው ሰይመዋል።

ወጣቶች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሌሎች ወጣቶች ተቃውሞውን እንዲቀላቀሉ እየቀሰቀሱ ነው።

በቴህራን የቀጠለው ተቃውሞ የፓህቫሊን ተጽዕኖ ፈጣሪነትን የሚያሳይ ነው።

አሁን ያለው መንግሥት ቢወድቅ ኢራንን የሚያስተዳድር አማራጭ መንግሥት እንዳለ በመጠቆም ተቃውሞውን እንዳቀጣጠሉት ተንታኞች ይናገራሉ።

በሌላ በኩል ደግሞ ኢራናውያን ለፓህላቪ ያሳዩት ድጋፍ የቀድሞው ሥርወ መንግሥት እንዲመለስ መፈለጋቸውን አያሳይም ብለው የሚከራከሩ አሉ።

ሆኖም ግን አሁን ያለው አስተዳደር እንዲወድቅ ያለው ፍላጎት ጠንካራ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።

አሜሪካ ኢራናውያንን ለመርዳት "በተጠንቀቅ እየተጠባበቀች ነው" ብለዋል ትራምፕ።

የፎቶው ባለመብት, Chip Somodevilla/Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አሜሪካ ኢራናውያንን ለመርዳት "በተጠንቀቅ እየተጠባበቀች ነው" ብለዋል ትራምፕ።

የትራምፕ ጣልቃ ገብነት

ከዚህ ቀደም ከተነሱት ተቃውሞዎች የአሁኑ የሚለየው አንድም በአሜሪካ ጣልቃ ገብነት ነው።

ትራምፕ ተቃዋሚዎቹን በመደገፍ የኢራን መንግሥት ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ዝተዋል። ከዚህ ቀደም እንዲህ ያለ ማስፈራሪያ ደርሶ አያውቅም።

በአውሮፓውያኑ 2009 ተቃውሞ ሲነሳ "ኦባማ፣ ኦባማ፣ ወይ ከእነሱ ጋር ወይ ከኛ ጋር ነህ!" የሚሉ መፈክሮች ተሰምተዋል።

ኋላ ላይ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ከተቃዋሚዎች ጎን አለመቆማቸው እንደሚቆጫቸው ተናግረዋል።

የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዤስኪያን እንደሚሉት ተቃውሞው "በኢራን ጠላቶች" የተቀነባበረ ነው ብለዋል።

ኢራን ያሏት ወዳጅ አገራት ቁጥር ባለፉት ዓመታት እየቀነሰ መጥቷል።

የሶሪያው ፕሬዝዳንት ባሻር አል-አሳድ ከሥልጣን ሲወገዱ ኢራን ደጋፊዋን አጥታለች። ሌላኛው የኢራን አጋር የሊባኖሱ ሔዝቦላህም በእስራኤል ጥቃት ተዳክሟል።

ተቃዋሚዎቹ 'ሞት ለአምባገነኑ' ሲሉ በአደባባይ ተቃውሟቸውን አስተጋብተዋል። የኢራን ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኒ ከሥልጣን እንዲነሱም ጠይቀዋል።

የፎቶው ባለመብት, Morteza Nikoubazl/NurPhoto via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ተቃዋሚዎቹ 'ሞት ለአምባገነኑ' ሲሉ በአደባባይ ተቃውሟቸውን አስተጋብተዋል። የኢራን ጠቅላይ መሪ አሊ ኻሜኒ ከሥልጣን እንዲነሱም ጠይቀዋል።

ተንታኞች እንደሚሉት፤ ያለፈው ዓመት የኢራን መከላከያ የደረሰበት ጥቃት የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ክብርን የነካ ነው።

የማኅበረሰብ ሳይንስ አጥኚ ኤሊ ኮራሳንድፋር እንደሚሉት፤ የ2022ቱን ተቃውሞ የተመረኮዘው የአሁኑ ንቅናቄ ዘላቂ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል።

ከሦስት ዓመት በፊት ለተቃውሞ የወጣች ኢራናዊት እንደምትለው፤ ትልቁ ስኬት ጨቋኙን መንግሥት መፍራት ማቆም ነው።

የአሁኑን ተቃውሞ ከ2022ቱ የሚለየው ኢራን ከእስራኤል ጋር ለ12 ቀናት ከተዋጋች በኋላ መነሳቱ ነው። ከውጊያው በኋላ አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ ጥቃት ፈጽመዋል።

ጋዜጠኛው አባስ አብዲ እንደሚለው፤ የኢራን ባለሥልጣኖች እነዚህን ጥቃቶች ሕዝቡን ለማስተባበር ሊጠቀሙባቸው ይችሉ ነበር። ሆኖም ግን ያንን አላሳኩም።