በርካቶች የተገደሉበትን የኢራን ተቃውሞን ተከትሎ ዘጠኝ አውሮፓውያን ታሰሩ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በኢራን ሒጃብ አለበሽም በሚል በፖሊስ ድብደባ ተፈፅሞባት ለሞት በቅታለች በተባለች ሴት ምክንያት የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ ዘጠኝ የአውሮፓ አገራት ዜጎች መታሰራቸው ተገለጸ።
የደኅንነት መኮንኖች፣ በተቃውሞ ሰልፎች ላይ አሊያም ከጀርባ ሆነው የሚሰሩ የውጭ የስለላ ድርጅቶች ወኪሎች ናቸው የሚሏቸውን ሰዎች በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን የኢራን መገኛኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ተቃውሞው ከተቀሰቀሰ ቀናት ቢቆጠሩም አሁንም የመረጋጋት ምልክቶች አይታዩም፣ እንዲሁም የሚሞቱ ሰዎችም ቁጥር እየጨመረ ነው።
ኩርዳዊቷ ሴት ማህሳ አሚኒ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሳለች በመሞቷ ነበር በኢራን ዋና መዲና ቴህራን ተቃውሞው የተቀሰቀሰው። ከዚያም በኋላ ተቃውሞው ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተስፋፍቷል።
ነዋሪነቷ በሰሜን ምዕራብ ከተማዋ ሳቄዝ የሆነችው የ22 ዓመቷ ሴት፣ “ሴቶች ፀጉራቸውን እንዲሸፍኑ የሚያዘውን ሕግ ተላልፈሻል” በሚል በቴህራን በሥነ ምግባር ተቆጣጣሪ ፖሊስ መኮንኖች በቁጥጥር ሥር የዋለችው ከሁለት ሳምንታት በፊት ነበር።
የኢራን ፖሊስ ከተቃውሞው ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ዘጠኙ የአውሮፓ አገራት ዜጎች የት እንደታሰሩ አልገለጸም።
ፖሊስ በተቃውሞ ሰልፎቹ ውስጥ የውጭ ዜጎች እና ተቀማጭነታቸው በውጭ አገር የሆኑ ተቃዋሚ ቡድኖች እጃቸው አለበት ብሎ ይከሳል።
የኢራን የደኅንነት ሚኒስቴር፣ የታሰሩት የአውሮፓውያን ከፖላንድ፣ ከስዊድን፣ ከጀርመን፣ ከጣሊያን፣ ከፈረንሳይ እና ከኔዘርላንድስ የመጡ መሆናቸውን ገልጿል።
ወኪሎቻቸው በፀረ መንግሥት ተቃውሞ ሰልፎች ላይ እንዳይሳተፉ ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው ኤምባሲዎች መካከልም የጀርመን፣ የፈረንሳይ ፣ የዩናይትድ ኪንግደም እና የስዊድን ኤምባሲዎች እንደሚገኙበትም ሚኒስቴሩ አክሏል።
ሚኒስቴሩ ጨምሮም ከተቃውሞው በፊት እና በተቃውሞው ወቅት፣ የሳይበር ጥቃትን እና ቢቢሲ ፐርሺያን እና ኢራን ኢንተርናሽናልን የመሳሰሉ የመገናኛ ብዙኃን “ሐሰተኛ እና አመጽን የሚደግፉ ዜናዎች” ማሰራጨትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ሴራዎች ሲፈጽሙ እንደነበር አስታውቋል።
ወጣቷ አሚኒ ራሷን የሳተችው “እንድትማር” በሚል በፖሊሶች ተይዛ ወደ እስር ቤት ከተወሰደች በኋላ ነበር። ከዚያም ሦስት ቀናትን በሞት አፋፍ ላይ ሆና በሆስፒታል ካሳለፈች በኋላ ሕይወቷ አልፏል።
ቤተሰቦቿ፣ ልጃቸው አሚኒ በፖሊስ ድብደባ እንደተፈፀመባት ቢያምኑም ፖሊስ ግን የሞተችው በድንገት ባጋጠማት የልብ ህመም ነው ብሏል።
ኢራን በርካታ ሰዎች ለተገደሉበት ለዚህ ተቃውሞ “የውጭ ጠላቶች” ያለቻቸውን ተጠያቂ ታደርጋለች።
ተቀማጭነቱን ኖርዌይ ያደረገው የኢራን የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ቡድን፣ በተቃውሞው ሕጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 83 ሰዎች መገደላቸውን ማረጋገጡን በትዊተር ገጹ አስታውቋል።
አርብ ዕለት ደግሞ በደቡብ ምሥራቃዊ ክፍል የሲስታን - ባሉቺስታን ግዛት ዋና ከተማ ዛሄዳን በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ በተቃዋሚዎች እና በፖሊስ መካከል በተፈጠረ ግጭት ተጨማሪ 19 ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።
ከሞቱት መካከል የአገሪቱ አብዮታዊ ዘብ ኮሎኔል እንደሚገኙበት ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል። ይሁን እንጂ ግጭቱ ከአሚኒ ሞት ጋር ተያይዞ በተነሳው ተቃውሞ ሳቢያ ስለመሆኑ የታወቀ ነገር የለም።
የግዛቱ ገዢ ሆሴን ኪያባኒ፣ በግጭቱ 19 ሰዎች ሲገደሉ 20 ሰዎች ደግሞ ጉዳት እንደደረሰባቸው ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።
ሆሴን አክለውም “የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጓድ የግዛቱ የደኅንነት መኮንን ኮሎኔል አሊ ሙሳቪ ተገድለዋል” ብለዋል።
ከአፍጋኒስታን እና ፓኪስታን ጋር የምትዋሰነው ሲስታን - ባሉቺስታን ከአደንዛዥ እፅ አዘዋዋሪ ቡድኖች እንዲሁም በቁጥር አነስተኛ ከሆኑት ከባሉቺ አማጺያን እና የሱኒ ሙስሊም ጽንፈኛ ቡድኖች ጋር ግጭት የሚካሄድባት ቦታ ናት።
ባለፈው አርብም በዛህዳን የሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ በታጣቂዎች ጥቃት በደረሰበት ወቅት የፀጥታ ኃይሎች የአጸፋ ተኩስ መተኮሳቸውን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።












