የሴቶችን አለባበስ የሚቆጣጠሩት የኢራን የሞራል ደንብ አስከባሪ ፖሊሶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኢራን ሒጃብ አልለበሽም በሚል በሞራል ደንብ አስከባሪዎች ድብደባ ተፈፅሞባት ለሞት በቅታለች በተባለችው የ22 ዓመቷ ማህሳ አሚኒ ጉዳይ በአገሪቱ ከፍተኛ ቁጣ ተቀስቅሷል።
በርካታ ሴቶች የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ ጥብቅ የአለባበስ ሕግን እንዲሁም ይህንን የሚያስፈፅሙትን የሞራል ደንብ አስከባሪዎች በመቃወም የሚጠመጥሙትን ሒጃብ አቃጥለዋል።
የሞራል ደንብ አስከባሪዎቹ 'ጋሽት-ኢ-ኢርሻድ' ይሰኛሉ።
እስላማዊ ሥነ ምግባር ማስፈፀምና ይህንንም ተላልፈው 'ያልተገባ አለባበስ' የሚለብሱ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የተሰማሩ ልዩ የፖሊስ ክፍሎች ናቸው።
ሸሪዓን መሠረት አድርጌያለሁ በሚለው የኢራን ሕግ መሠረት ሴቶች ፀጉራቸውን በሒጃብ መሸፈን፣ እንዲሁም የሰውነት ቅርፃቸውን የማያሳይ ሰፋ ያለና ረዥም ቀሚስ መልበስ እንዳለባቸውም ያስገድዳል።
ማህሳ አሚኒ ከሳምንት በፊት ቴህራን ውስጥ በሞራል ደንብ አስከባሪዎች በቁጥጥር ሥር የዋለችው ሒጃብ ብትጠመጥምም የተወሰነ ፀጉሯ በመታየቱ ነበር።
እስር ቤት ከገባች በኋላም ራሷን ስታ ፅኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ ገብታ የነበረ ሲሆን፣ ከሦስት ቀናት በኋላ ሕይወቷ አልፏል።
ፖሊስ የማህሳን ጭንቅላት በዱላ እንደደበደባትና ከመኪና ጋርም እንዳጋጯት ሪፖርት የተደረገ ሲሆን፣ ፖሊስ በበኩሉ ተደብድባ ነው የሞተችው የሚለውን ክስ አስተባብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Mahsa Amini Family
ባልተለመደ ሁኔታ ማንነቱ እንዲጠቀስ ያልፈለገ አንድ የሞራል ደንብ አስከባሪ ለቢቢሲ በዚህ ክፍል ውስጥ የነበረውን ልምድ ተናግሯል።
"በሞራል ደንብ አስከባሪነት የምንሠራበት ዋነኛ ምክንያት ሴቶችን ለመጠበቅ ነው" የሚለው አስከባሪው፤ "ምክንያቱም ሴቶች በአግባቡ ካልለበሱ የወንዶችን ስሜት ቆስቁሰው ሊጎዱዋቸው ይችላሉ ተብለናል" ይላል።
አራት ወንድና ሁለት ሴቶችን ባቀፈ ስድስት አባላት ባሉት ቡድን እንደሚሠሩና ሰዎች በሚጨናነቁባቸውና ሕዝብ በሚሰበሰብበት አካባቢ ላይ ያትኩረት እንደሚያደርጉ ይናገራል።
"የሚያስገርም ነው፤ ምክንያቱም ሰዎችን ትክክለኛ አቅጣጫ ለማሳየት ከሆነ በርካታ ሰዎች የሚበዙበትን ቦታ ለምን እንመርጣለን? ይህ ማለት በርካታ ሰዎችን ማሰር የምንችልባቸው ስፍራዎችን ነው ኢላማ ያደረግነው" የሚለው ደንብ አስከባሪው፤ "ለአደን የምንወጣ ያህል ነው የሚሰማኝ" ብሏል።
መኮንኑ አክሎም ከእሱ በላይ ያለው አዛዥ የአለባበስ መመሪያውን የሚጥሱ በቂ ሰዎችን ማምጣት ካልቻለ ሥራውን በትክክል እየሠራ እንዳልሆነ እንደሚነግረው ያስረዳል።
ግለሰቦችን በቁጥጥር ለማዋል መሞከሩንም ፈታኝ ሆኖ አግኝቶታል።
"መኪና ውስጥ እንዲገቡ ማስገደድ ይጠበቅብናል። ምን ያህል ጊዜ እንዳለቀስኩ ታውቃላችሁ?"
"ከደንብ አስከባሪዎቹ አንዱ እንዳልሆንኩ ልነግራቸው እፈልጋለሁ። አብዛኞቻችን አስገዳጅ የሆኑ ወታደራዊ አገልግሎቶችን መፈጸም ያለብን ተራ ወታደሮች ነን። በጣም መጥፎ ስሜት ይሰማኛል" ይላል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ድኅረ አብዮት ድንጋጌ
የኢራን ባለሥልጣናት "መጥፎ ሒጃብ" ብለው ከሚጠሩት አለባበስ ጋር የሚያደርጉት ትግል የተጀመረው ከአውሮፓውያኑ 1979 የእስልምና አብዮት በኋላ ብዙም ሳይቆይ ነበር።
የዚህም ዋና አላማ ሴቶችን 'ጨዋ' የሆነ ልብስ እንዲለብሱ ማድረግ ነበር።
በወቅቱ ብዙ ሴቶች ይህንን ቢያደርጉም በተመሳሳይ መልኩ አጭር ቀሚስ መልበስ፣ ፀጉር አለመሸፈን በቴህራን ጎዳናዎች ላይ የተለመዱ ነበሩ።
ይህም የምዕራባውያን ደጋፊ የነበረው ሻህ ረዛ ፓህላቪ ከሥልጣን ከመገልበጡ በፊት ሲሆን፣ የምዕራባውያን አለባበስ የምታዘወትረው ባለቤቱ ፋራህ የዘመናዊ ሴት ተምሳሌትም ነበረች።
የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ በተመሠረተ በወራት ውስጥ፣ በሻህ ዘመን የተደነገጉ የሴቶችን መብት የሚያስጠብቁ ሕጎችን መሻር ተጀመረ። የመጀመሪያውን ፀረ-ሒጃብ ተቃውሞ በማዘጋጀት የረዱት የ78 ዓመቱ መህራንጊዝ ካር፣ "ይህ በአንድ ጀምበር የተከሰተ አይደለም፣ ደረጃ በደረጃ ከፍ ያለ ሂደት ነበር" ብሏል። "ከአብዮቱ በኋላ ልክ በስጦታ ወረቀት ለታሸጉ ሴቶች ነፃ የራስ መሸፈኛ የሚያቀርቡ ወንዶች እና ሴቶች በመንገድ ላይ ነበሩ።"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአውሮፓውያኑ 1979 የአብዮቱ መሪ አያቶላህ ሩሆላህ ኾሚኒ ሁሉም ሴቶች በሥራ ቦታቸው ሒጃብ አስገዳጅ እንደሚሆንባቸው እና ያልተሸፈኑ ሴቶችን "ራቁታቸውን" እንደሆኑ አድርገው እንደሚመለከቷቸው ተናገሩ።
"ይህ ንግግር በብዙ አብዮተኞች ዘንድ ሴቶች ሒጃብ እንዲጠመጥሙ የሚያስገድድ ትዕዛዝ ነው በሚል ነው የታየው" የሚሉት በዋሽንግተን ዲሲ ነዋሪ የሆኑት ካር "ብዙዎች ይህ በአንድ ሌሊት ተግባራዊ እንዲሆን በማሰብም በርካቶች መቃወም ጀመሩ" ይላሉ።
ፈጣን ምላሽ በመስጠትም ከ100 ሺህ የሚበልጡ አብዛኛው ሴቶች የተሳተፉበት ተቃዋሚዎች በቴህራን ጎዳናዎች ላይ በዓለም የሴቶች ቀን ተቃውሟቸውን ገለጹ።
የአያቶላህ ኾሚኒ ድንጋጌ ቢኖርም ለሴቶች "ትክክለኛ አለባበስ የትኛው ነው?" የሚለውን ለመወሰን ባለሥልጣናቱ የተወሰነ ጊዜ ወስደዋል።
"ግልጽ የሆነ መመሪያ ስላልነበረም፤ በቢሮ ግድግዳዎች ላይ የሚንጠለጠሉ ሞዴሎችን የሚያሳዩ ፖስተሮች እና ባነሮች ይዘው መጡ። ሴቶች ሒጃብ ለመልበስ እነዚህን ፖስተሮች ተግባራዊ ማድረግ ካልቻሉ ወደ ቢሮዎቻቸው መግባት አይችሉም የሚል ትዕዛዝም አመጡ" ሲሉ ካር ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, BBC Persian
በአውሮፓውያኑ 1981 ሴቶች እና ልጃገረዶች 'ጨዋ የሆነ እስላማዊ ልብስ' እንዲለብሱ በሕግ አስገዳጅ ሆነባቸው።
ይህ ማለት በተግባር ሙሉ ሰውነታቸውን የሚሸፍን ልብስ፣ እንዲሁም ጭንቅላታቸውን በስካርቭ መሸፈን ይጠበቅባቸዋል።
"ነገር ግን አስገዳጅ ሒጃብ መጠምጠም ላይ የሚደረገው ትግል በግለሰብ ደረጃ ቀጠለ። እኛም ኮፍያ በማጥለቅ ወይም ፀጉራችንን በአግባቡ ባለመሸፈን ፈጠራዎቻችንም ማምጣት ጀመርን" ሲሉ ካር ያስረዳሉ።
"እነሱ ባስቆሙን ቁጥር እኛም መታገላችንን ቀጠልን" ይላሉ።
በአውሮፓውያኑ 1983 ፓርላማው ፀጉራቸውን በአደባባይ ያልሸፈኑ ሴቶች በ74 ጅራፍ እንዲቀጡ ውሳኔ አሳለፈ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ እስከ 60 ቀናት የሚደርስ እስራት ቅጣት ተጨመረበት።
ሆኖም ግን ባለሥልጣናት ሕጎቹን ለማስከበር ሲታገሉ ቆይተዋል።
በሁሉም ዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች በአደባባይ ጠባብ ልብሶችን በመልበስ፣ ጭናቸው ላይ የሚደርስ ርዝመት ያለው ኮት በመደረብ እና ባለቀለም ሒጃቦችን በመጠምጠም ትግላቸውን አቀጣጥለውት ቆይተዋል።
እነዚህ ሕጎች ምን ያህል ተፈፃሚ እንደሆኑ እና የሚተላለፉት የቅጣት መጠን የተለያዩ ፕሬዚዳንቶች በሥልጣን ላይ በነበሩባቸው ዓመታትም የተለያየ ሆኖ ቆይቷል።
እጅግ ወግ አጥባቂውና በወቅቱ የቴህራን ከንቲባ የነበሩት ማህሙድ አህመዲን ነጃድ በአውሮፓውያኑ 2004 ለፕሬዚዳንትነት ምርጫ ዘመቻ ሲያደርጉ በጉዳዩ ላይ የበለጠ ተራማጅ መሆናቸውን ለማሳየት ሞክረዋል።
"ሰዎች የተለያየ ፍላጎት ስላላቸው ሁሉንም በእኩል ሁኔታ ማገልገል አለብን" ብለው ነበር ባደረጉት የቴሌቪዥን ቃለ ምልልስ።

የፎቶው ባለመብት, AFP
ነገር ግን በቀጣዩ ዓመት ምርጫ ማሸነፋቸውን ተከትሎ ብዙም ሳይቆይ ጋሽት-ኢ-ኢርሻድ በይፋ ተቋቋመ።
እስከዚያ ድረስ አለባበስን ይቆጣጠሩ የነበሩት ደንቦቹ መደበኛ ባልሆነ መልኩ የሕግ አስከባሪ አካላት ነበሩ።
የሞራል ደንብ አስከባሪዎች አብዛኛውን ጊዜ በሚያሳዩት ጭካኔ በሕዝብ ዘንድ ይወቀሳሉ።
እንዲሁም በተደጋጋሚ በቁጥጥር የሚውሉ ሴቶች የሚለቀቁትም ዘመዶቻቸው ቀርበው ለወደፊቱ መመሪያዎቹን እንደሚያከብሩ ማረጋገጫ ሲሰጡ ብቻ ነው።
"ከልጄ ጋር ያስቆሙን በሊፒስቲካችን ምክንያት ሲሆን ከዚያም በቁጥጥር ስር አዋሉን" በማለት በማዕከላዊ ኢራን በምትገኘው የኢስፋሃን ከተማ ነዋሪ የሆነች አንዲት ግለሰብ ለቢቢሲ ተናግራለች።
"ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱን፣ ከዚያም ባለቤቴን ጠርተው ሒጃብ ሳንጠመጥም ከቤት እንደማያስወጣን እንዲፈርም ጠየቁት" ብላለች።
ሌላኛዋ የቴህራን ነዋሪ የሆነች ሴት ለቢቢሲ እንደገለፀችው፣ ያደረገችው ቡትስ ጫማ ለወንዶች "በጣም ሊማርክና ሊያጓጓ" ይችላል በሚልም አንዲት ሴት መኮንን በቁጥጥር እንዳዋለቻት ተናግራለች።
"ባለቤቴን ደወልኩና ጫማ እንዲያመጣልኝ ጠየቅኩት" በማለትም ታስረዳለች።
"ከዚያም አግባብ የሌለለው ልብስ ለብሼ እንደነበር በማመን ፈረምኩኝ እና አሁን የወንጀል ሪከርድ አለብኝ” ትላለች።
ሌሎች ደግሞ በሞራል ደንብ አስከባሪዎች እንደተደበደቡ እንዲሁም ጭካኔ የተሞላባቸውና ያልተለመዱ ቅጣቶች እንደተፈጸሙባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አንዲት ሴት በቁጥጥር ሥር በዋለችበት ጊዜ ፖሊሶች በሰውነቷ ላይ በረሮዎች እንዲርመሰመሱ ሊለቁባት እንደሚችሉ ተናግራለች።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አዲስ እስር
ባለፈው ዓመት የተመረጡት አክራሪው የሃይማኖት መሪ እና ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ አዲስ እገዳዎችን ያካተተ ትዕዛዝ ነሐሴ አጋማሽ ላይ ፈርመዋል።
ያልተሸፈኑ ሴቶችን ለመከታተል እና ለመቅጣት ወይም "ለምክር" ለመጥራት የስለላ ካሜራዎችን ማስተዋወቅ፤ እንዲሁም በኢንተርኔት የሒጃብ ሕግጋትን የሚጻረር ይዘትን ለለጠፉ ወይንም ጥያቄ ያቀረቡ በሙሉ የእስራት ቅጣት እንዲጣልባቸው የሚል ያካትታል።
እነዚህ ክልከላዎች እስራትን እንዲጨምሩ ቢያደርጉም በሌላ መልኩ ያለ ሒጃብ ፎቶግራፎችን እና ቪዲዮዎችን በማኅበራዊ ድረ-ገጾች ላይ የሚለጥፉ ሴቶች ቁጥር እንዲበራከት አድርጓል።
በተለይም የማሀሳንን ሞት ተከትሎ ባሉት ቀናት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።
በአሁኑ ወቅት መቀመጫዋን አሜሪካ ያደረገችው ጋዜጠኛ እና አክቲቪስት ማሲህ አሊነጃድ፣ የማህሳን ሞት ተከትሎ የተቀሰቀቀው ሕዝባዊ ተቃውሞ ጥልቅ ስሜት እንዳሳደረባት ተናግራለች።
ባለፉት ዓመታት በሒጃብ ሕግጋት ላይ 'ማይስቲልዚፕሮቴስት' የተሰኘውን ተቃውሞ ጨምሮ ታዋቂ ዘመቻዎችን ስታካሂድ የቆየች ሲሆን፣ መንግሥትን ጨምሮ በርካቶች አሁን ላለው ተቃውሞ አነሳሽ አድርገው ይመለከቷታል።
ቅዳሜ በምዕራብ የሳቄዝ ከተማ በነበረው የማህሳን የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ሴቶች ሒጃባቸውን በማውለቅና እና በአየር ላይ በማውለብለብ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል።
በቀጣዮቹ ቀናት በመላ አገሪቱ ጎዳናዎች በርካታ ተቃዋሚዎች የወጡ ሲሆን፣ የተወሰኑት ደግሞ ሒጃባቸውን ሲያቃጥሉና ወንድ ተቃዋሚዎች ሲያጨበጭቡላቸው የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ወጥተዋል።
"ተቃዋሚዎች ይህንን ሲያደርጉ፣ ሰዎች የበርሊንን ግንብ ማፍረስ የጀመሩበትን ያንን ጊዜ አስታወሰኝ" ስትል ማሲህ ተናግራለች።
"በጣም እንዲሰማኝ ያደረገውና ተስፋ የሰጠኝም ጉዳይ ቢኖር እነዚህ ሴቶች ለመጀመሪያ ጊዜ ብቻቸውን አይደሉም። በአሁኑ ወቅት ወንዶች ከሴቶች ጎን አብረው ቆመዋል" ትላለች።












