የኢራን ፖሊስ 'ሒጃብ አልለበሽም' በሚል በቁጥጥር ስር በዋለችው ግለሰብ ሞት ማዘኑን ገለጸ

የፎቶው ባለመብት, MAHSA AMINI FAMILY
በኢራን ሒጃብ አልለበሽም በሚል በሞራል ደንብ አስከባሪዎች ድብደባ ተፈጽሞባት ለሞት በቅታለች የተባለች ሴት ጉዳይ እንዳሳዘነው ተናገረ።
የፖሊስ ዋና ኃላፊ እንዳሉት የማህሳ አሚኒ ሞት ‘አሳዛኝ አጋጣሚ ነው’ ብለዋል።
ማህሳ አሚኒ የ22 ዓመት ወጣት ስትሆን የኢራል የሞራል ደንብ አስከባሪዎች ሒጃብን በአግባቡ አልጠመጠምሽም በሚል በቁጥጥር ሥር ካዋሏት በኋላ አደረሱባት በተባለ ድብደባ መሞቷን የዓይን እማኞች ገልጸዋል።
ፖሊስ ግን ይህን ክስ ውድቅ አድርጎታል።
የፖሊስ አዛዥ ብርጋዴየር ጄኔራል ሁሴን ረሒሚ የወጣቷ ሞት ከሞራል ደንብ አስከባሪዎች ድብደባ በኋላ የተከሰተ ነው መባሉ ‘ተራ አሉባልታ’ ብለውታል።
እርሳቸው እንደሚሉት ማህሳ አሚኒ የልብ ችግር ነበረባት።
የማህሳ አሚኒ የቀብር ሥነ ሥርዓትን ተከትሎም በመላ አገሪቱ ቁጣ የተቀሰቀሰ ሲሆን አንዳንድ ሴቶች ሒጃባቸውን በማውለቅና በማቃጠል ተቃውሟቸውን ገልጠዋል።
የማህሳ ቀብር ሥነ ሥርዓት የተፈጸመው በምዕራብ ኩርዲስታን ግዛት ሳቄዝ በምትባል የትውልድ ስፍራዋ ነበር።
የቀብር ሥነ ሥርዓቱን ተከትሎ ተቃውሞ ሊቀሰቀስ ይችላል በሚል ፖሊስ ቀድሞ በስፍራው የተገኘ ሲሆን የተፈራው ደርሶ በተፈጠረ ረብሻ ሁለት ሰዎች ተገድለዋል።
በማኅበራዊ ትስስር መድረኮች በተጋሩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች እንደታየው ደግሞ ተቃዋሚዎች በፖሊስ ላይ ድንጋይ ሲወረውሩ ነበር።
ፖሊስም በምላሹ ተኩስ ሲከፍትና ሰልፈኞችን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ሲጠቀም ይታያል።
ሌሎች ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ደግሞ በዋና ከተማዋ ቴህራን አደባባይ የወጡ ሴቶች “ሞት ለአምባገነኑ!’ እያሉ ሲዘምሩ ያሳያል።
በኢራን በተቃውሞ ሰልፎች ላይ ‘አምባገነኑ’ የሚለው ቃል መንፈሳዊው መሪን አያቶላህ ኻሚኒን የሚጠቁም ነው።
ማህሳ አሚኒ የኩርድ ዝርያ ያላትና በምዕራብ ኩርዲስታን አውራጃ ሳቄዝ በምትባል መንደር ነዋሪ ስትሆን ድብደባ ከተፈጸመባት በኋላ ራሷን ለሦስት ቀናት ስታ በሆስፒታል አልጋ ላይ ውላ ነው የሞተችው።
የሞራል ደንብ አስከባሪ ፖሊሶች በቁጥጥር ሥር ያዋሏት ግን ማክሰኞ ዕለት በቴህራን በሚገኝ ባቡር ጣቢያ ነበር።
ክሳቸው የነበረውም ጸጉርሽን ሙሉ በሙሉ አልሸፈንሽም፣ ክንድሽና እግርሽም በስስ ልብስ ሸፈን አልተደረገም የሚል ነው።
የዓይን እማኞች እንደሚሉት ከሆነ ማህሳ አሚኒ ደንብ አስከባሪ ፖሊሶች መኪናቸው ውስጥ ካስገቧት በኋላ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እየወሰዷት ድብደባ ፈጽመውባታል።
ፖሊስ ይህን ክስ ያጣጣለው ሲሆን የሞተችውም በድንገተኛ የልብ ህመም ነው ብሏል።
ይህን ያሳያል ያሉትን አንድ የሲሲቲቪ ተንቀሳቃሽ ምሥል ያሳዩ ሲሆን በዚህ ቪዲዮ አሚኒ ናት የተባለች ወጣት ከሴት የፖሊስ መኮንን ጋር ስታወራ ይታያል። ከአፍታ በኋላም ጭንቅላቷን በእጇ ደገፍ አድርጋ በድንገት ራሷን ስታ ስትወድቅ ያሳያል።
የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ እንዳሉት አሚኒ ቀድሞውኑም የጤና እክል ነበረባት።
ይሁንና የማህሳ አሚኒ አባት ለአንድ ለውጥን በመሻት የሚታወቅ የሰንበት ጋዜጣ እንደተናገሩት ልጃቸው ምንም ዓይነት የጤና እክል አልነበረባትም።
ፖሊስ የለቀቀው ቪዲዮም የተቀናበረ እንጂ እውነተኛ አይደለም ብለዋል።
ብራጋዲየር ጄኔራል ራሒሚ ለቤተሰቦቿ መጽናናትን ተመኝተው ካበቁ በኋላ፣ ይሁንና ሟች በሞራል ደንብ አስከባሪዎች የደረሰባት አንዳችም ድብደባ የለም ብለዋል።












