የአሜሪካው ልዩ መልዕክተኛ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር መነጋገራቸው ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, GOOBJOG NEWS
በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ መንግሥት ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት አምባሳደር ማይክ ሐመር በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር መገናኘታቸው ተገለጸ።
ለወራት ጋብ ብሎ የነበረው በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት መልሶ ከተቀሰቀሰ በኋላ ወደ አፍሪካ ቀንድ በመምጣት ለቀናት የቆዩት ልዩ ልዑኩ በዋናነት ጦርነት ቆሞ ሁለቱም ወገኖች ድርድር እንዲጀምሩ ግፊት ሲያደርጉ መቆየታቸው ተነግሯል።
ነሐሴ 30/2014 ዓ.ም. አዲስ አበባ የገቡት አምባሳደር ሐመር አስከ መስከረም 05/2015 ዓ.ም. ድረስ በነበራቸው ቆይታ ዋነኛ አጀንዳቸው የነበረው የሰሜን ኢትዮጵያው የእርስ በርስ ጦርነት እንደነበር የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ያወጣው መግለጫ አመልክቷል።
ልዩ መልዕክተኛው በአዲስ አበባ የአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ ከሆኑት ትሬሲ አን ጃኮብሰን ጋር በመሆን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተገናኝተው መወያየታቸው ተገልጿል።
በዚህ ጊዜም በሰሜን ኢትዮጵያ እንደ አዲስ ስላገረሸው ውጊያ እና ኤርትራ ወደ ግጭቱ ተመልሳ ስለመግባቷ አሜሪካ ስላላት ስጋት እንዲሁም ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት የሚካሄደው ጥረት ስለሚጠናከርበት ሁኔታ መነጋገራቸውን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ጠቅሷል።
በተጨማሪም አምባሳደር ሐመር ከትግራይ ክልል ባለሥልጣናት ጋር መነጋገራቸውን በማመልከት ከሁለቱም ወገኖች ጋር በተደረገው ውይይት ወቅት፣ ወደ ትግራይ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች ያልተገደበ የሰብአዊ እርዳታ ስለሚቀርብበት ሁኔታ መነጋገራቸው ተገልጿል።
ማይክ ሐመር ለቀናት በአዲስ አበባ ውስጥ በነበራቸው ቆይታ ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር፣ ከኢትዮጵያ የፍትሕ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ እና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን ጋር መገናኘታቸው የተገለፀ ሲሆን፣ ከየትኞቹ የትግራይ አመራሮች ጋር እንደተወያዩ ግን የተጠቀሰ ነገር የለም።
እንዲሁም ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ እንዲደረግ፣ የሰብአዊ መብት እንዲከበር ልዩ መልዕክተኛው ማንሳታቸውንና ብሔር ተኮር እስርን በተመለከተ የሚወጡ ሪፖርቶችን አንስተዋል። አክለውም ከተፈጸሙ ጭፍጨፋዎች ጋር በተያያዘ ተጠያቂነት እንዲኖር እና ለሰለባዎችና ከጥቃት ለተረፉት ፍትሕ ስለሚያገኙበት ሁኔታ መነሳቱ ተነግሯል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት እንዳለው ልዩ ልዑኩ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት በተጨማሪ ከአፍሪካ ኅብረት ተወካዮች እና ከዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ወደፊት መወሰድ ስላለባቸው እርምጃዎች ተወያይተው መስከረም 06/2015 ዓ.ም. ወደ ዋሽንግተን መመለሳቸውን ገልጿል።
አምባሳደር ሐመር ሰኞ መስከረም 09/2015 ዓ.ም. አሜሪካ ኒው ዮርክ ውስጥ ከጀመረው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን የዲፕሎማሲ ጥረታቸውን እንደሚቀጥሉ ተገልጿል።
በአዲስ አበባ ቆይታቸው በአፍሪካ ኅብረት ተሰይመው ጦርነቱን ለማስቆም ጥረት ሲያደርጉ ከነበሩት የኅብረቱ ከፍተኛ ተወካይ ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ ጋር በተደጋጋሚ ተገናኝተው አሜሪካ ሰላም ለማምጣት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ማድረግ በምትችለው ድጋፍ ዙሪያ ተወያይተዋል።
በአፍሪካ ኅብረት ሽምግልና ላይ ያላቸውን አለመተማመን በተደጋጋሚ ሲገልጹ የቆዩት የትግራይ ኃይሎች ከሳምንት በፊት በአህጉራዊው ድርጅት ጥላ ስር ለሚካሄድ ድርድር ዝግጁ መሆናቸውን በመግለጽ በአስቸኳይ ግጭቶች እንዲቆሙ መግለጻቸው ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ ለቀናት ይፋዊ ምላሽ ሳይሰጥ የቆየው የኢትዮጵያ መንግሥት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን በኩል መንግሥታቸው በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር ለመደራደር ቁርጠኛ መሆኑን ለአውሮፓ ኅብረት ባለሥልጣናት መናገራቸው ተዘግቧል።
የአሜሪካ መንግሥትም ሁለቱም ወገኖች በድርድር ለመሳተፍ ያሳዩትን ዝግጁነት በበጎ እንደሚመለከተው በመግለጽ፣ ይህንንም ተከትሎ ሁሉም ወገኖች ተጨባጭ እርምጃ በመውሰድ በቅን ልቦና ወደ ድርድር እንዲገቡ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ጠይቋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ አሜሪካ በልዩ መልዕክተኝነት ለአፍሪካ ቀንድ ከሰየመቻቸው መካከል ሦስተኛው የሆኑት አምባሳደር ማይክ ሐመር ሥራ የጀመሩት ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ነበር።
ሐመር በመልዕክተኝነት ወደ ኢትዮጵያ ባደረጉት በመጀመሪያ ጉዟቸው በአዲስ አበባ እና በመቀለ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት እና ከትግራይ አመራሮች ጋር መወያየታቸው ይታወሳል።
ባለፈው መጋቢት ወር የሰብአዊ እርዳታን ለማቅረብ ተደርሶ የነበረው የተኩስ አቁም ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም. በተቀሰቀሰው ጦርነት ፈርሶ በበርካታ የሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች ውጊያዎች እየተካሄዱ መሆናቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ።
የትግራይ ኃይሎች እና መንግሥት በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን እና የትግራይ ክልል በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች የተቀሰቀሰውን የአሁኑን ጦርነት በመጀመር አንዳቸው ሌላኛቸውን የሚከሱ ሲሆን፣ በአፋር ክልል በኩልም ግጭት መኖሩ ተገልጾ ነበር።
ሰላም የሚያወርድ ድርድር ይጀመራል ተብሎ በሚጠበቅበት ጊዜ ያገረሸውን ጦርነት ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት “የህወሓት ኃይሎች ጦርነቱን በተለያዩ ቦታዎች ላይ ከፍተዋል" ሲል የከሰሰ ሲሆን፣ የትግራይ ኃይሎችም አዋሳኝ ከሆኑት የአማራ ክልል ቦታዎች በተጨማሪ በኤርትራ በኩልም መጠነ ሰፊ ጥቃት ተከፍቶብናል ማለታቸው ይታወሳል።
አሜሪካንን ጨምሮ የተለያዩ አገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሁሉም ወገኖች ከግጭት እንዲታቀቡ ጠይቀው፣ ውጥረቱን በማርገብ በተለይ ሰብአዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ሁሉ አቅርቦቱ መልሶ እንዲጀመር ጥሪ ሲያርቡ ቆይተዋል።
በመጪው ጥቅምት ማብቂያ ላይ ሁለት ዓመት የሚሞላው የእርስ በርስ ጦርነት ትግራይ ክልል ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሞቱበት የሚታመን ሲሆን፣ በመቶ ሺዎች ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል።
ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመትን ባስከተለው በዚህ ጦርነት ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኙ ነዋሪዎች እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል።












