ባገኙት አጋጣሚ ከአገር ወጥተው እየቀሩ ያሉ የትግራይ ተወላጆች

ፊቱን አዙሮ ያለ ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአንድ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ በኃላፊነት ይሰራ የነበረው ጌትነት አጽብሃ፣ ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ከሌሎች አምስት ባለሙያዎች ጋር ለሥልጠና ወደ ዴንማርክ ተላከ።

ኮፐንሃገን ውስጥ ለሁለት ሳምንታት ያህል የተሰጠው ሥልጠና አጠናቀው ባልደረቦቹ ሲመለሱ ጌትነት ግን እዚያው መቅረትን መርጧል።

በአሁኑ ወቅት ዴንማርክ በሚገኝ የስደተኛ ካምፕ ውስጥ የሚገኘው ጌትነት፣ “እንደ ጡረተኛ የመንግሥት ገንዘብ እየተቀበልኩ ነው የምኖረው” ይላል።

እንደ ጌትነት የተሻለ ኑሮ፣ ጥሩ ደሞዝና ሙያቸውን ትተው በሄዱበት ስደትን እየመረጡ ያሉ የትግራይ ተወላጆች ጥቂት አይደሉም።

ጦርነቱ ያስከተለው ቀውስ

ጌትነት በሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ኃይሎች ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ጦርነት ከጀመሩ ወዲህ ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ሲንቀሰቃቀስ በርካታ ጫናዎቸን ማስተናገዱን ይናገራል።

በተለይ አዲስ አበባ፣ በሐዋሳ እና በቡታጅራ አካባቢዎች በሚሰራበት ወቅት የትግራይ ተወላጅ በመሆኑ ብቻ፣ “ለመሳቀቅና ለመሸማቀቅ” ይጋለጥ፣ ወደ ተለያዩ ቀበሌዎችና መንደሮች በሚሄድበት ወቅት ደግሞ ይታሰር እንደነበር ያስታውሳል።

“በጥርጣሬ ዓይን ያዩኛል...ለተወሰነ ጊዜ ፖሊስ ጣቢያ ያቆዩኝ ነበር። ሐዋሳ ቢሮ ከሚገኙ ተወካዮቻችን ጋር በመነጋገር ነበር የተፈታሁት።”

“የወንድሜ ልጅ ታስሮ የት እንዳለ አላውቅም” የሚለው ጌትነት፣ እርሱ ብቻ ሳይሆን ቤተሰቦቹም እስርና እንግልትን እንደገጠማቸው ይገልጻል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኮተቤ የሚገኝ የንግድ ድርጅቱ “ያለምንም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ” የተዘጋበት አጎቱ ቤተሰቡን ማስተዳደር አለመቻሉንና ባጋጠመው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ምክንያት ለህመም መጋለጡን ጨምሮ ያስረዳል።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ የትግራይ ኃይሎች ወደ ደቡብ ወሎ ከተሞች መጠጋታቸውን ተከትሎ የፌደራል መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጎ ነበር።

ይህንን አዋጅ ተከትሎም የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰድ በመጀመሩ በትግራይ ተወላጆች ላይ የሚደርሰው የመብት ጥሰት እንዲባባስ እንዳደረገው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ይገልጻሉ።

መንግሥት ግን በፀጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች በማንነታቸው ሳይሆን ከሕገ ወጥ ቡድኖች ጋር ባላቸው ግንኙነት ምክንያት ነው ሲል ያስተባብላል።

በአንድ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ ዲቨሎፕመንታል ስተዲስ ረዳት ፕሮፌሰር የነበረው ኪሩቤል*፣ “ጦርነት ላይ ሽንፈት ሲያጋጥም ንዴታቸውን አዲስ አበባ በሚኖረው የትግራይ ተወላጅ ላይ ግፍ በመፈጸም ይወጡታል” ሲል የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎችን ይወቅሳል።

በዚያን ወቅት “የትግራይ ተወላጅ ሆነህ መንቀሳቀስ ‘እንዴ! ይሄ ደሞ አልታሰረም እንዴ?’ የሚያስብል ጊዜ ነበር” ይላል ሁኔታውን የሚያስታውሰው ታምራት*

ታምራት ከአገር እስከወጣበት ጊዜ ድረስ በአንድ የፌደራል መንግሥት መሥርያ ቤት ውስጥ በዳይሬክተር የኃላፊነት ደረጃ ሰርቷል።

ትልልቅ መንግሥታዊ የልማት ፕሮጀክቶችንም መመራቱን የሚናገረው ታምራት “ምንም ዓይነት የፖለቲካ ተሳትፎ አልነበረኝም” ይላል።

ታምራት በተደጋጋሚ የትግራይ ተወላጆች ሲታሰሩ ሲመለከት ጊዜው ያላበቃ የአሜሪካ ቪዛ ስለነበረው አገር ለቅቆ መውጣቱን ይናገራል።

በአንድ የመንግሥት ኮሌጅ ውስጥ የአስተዳደር ምክትል ዲን የነበረው እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች እሰራ እንደነበር የሚናገረው መብርሃቶም* በበኩሉ፣ ትግራይ ውስጥ በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት ሲሰራበት የነበረው ድርጅት ፕሮግራሙን ሲያቆም እሱም ሥራውን ለማቋረጥ እንደተገደደ ገልጿል።

ለመሰደድ የተገደደው ጌትነት

‘ስደትን መርጬው አይደለም’

በተለያየ አጋጣሚ ከኢትዮጵያ የሚወጡ ባለሙያዎች በተለያየ ምክንያት በሄዱበት ይቀራሉ። ለዚህም ያሉበት የሥራ እና የኑሮ ሁኔታ ስደትን ስለሚያስመርጣቸው ነው።

ነገር ግን የኪሩቤል ውሳኔ ከዚህ ይለያል። “ስደትን መርጬው አይደለም” በማለት ይናገራል።

ከዚህ በፊት “አገሬ ይሻለኛል” ብሎ ከአውሮፓ መመለሱን የሚናገረው ኪሩቤል “በአገሬ ልሰራ የምችልበት ሁኔታ ቢኖር ኖሮ [እዚህ] አልቀርም ነበር” ይላል።

ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ በወቅቱ ተባብሶ ከነበረው የጅምላ እስር “ማምለጥ እንደማልችል” ተገነዘብኩ የሚለው ጌትነት ዴንማርክ ውስጥ ጥገኝነት ጠይቆ በዚያው ቀረ።

“ወጥቼ እቀራለሁ የሚል ሃሳብ አልነበረኝም” የሚለው ታምራት ግን የልጆቹ እና የባለቤቱ ናፍቆት ሲብስበት ለመመለስ ወስኖ የነበረ ቢሆንም፣ ከአገር ከወጣ በኋላ ቤቱ እንደተፈተሸና የት እንዳለ እንደተጠየቀ በመስማቱ “እንዳልመለስ አደረገኝ። ‘በቃ አገሬ አይደለም’ ብዬ አሰብኩ” ይላል።

እንደሱ ያሉ በተለያዩ የሙያ መስኮች ላይ የነበሩ በርካታ የትግራይ ተወላጆችም እየተሰደዱ እንደሆነ ጨምሮ ይገልጻል። “እዚህ የምኖርበት ከተማ ራሱ ከሰባት በላይ የማውቃቸው ሰዎችን አግኝቻለሁ።”

የስደት ኑሮ ፈተና

ጓደኞቹ ጋር ተዳብሎ እንደሚኖር የሚናገረው ታምራት፣ “ጥሩ ሥራ የነበረኝ፣ ልጆቼን በጥሩ ሁኔታ አስተምር፣ ትዳሬን በጥሩ ሁኔታ እመራ የነበርኩ ሰው አሁን ገንዘብ እንኳን ልልክላቸው የማልችልበት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለሁት” በማለት ስደት እንዳልተመቸው ይናገራል።

“የእኔን እችለዋለሁ፤ ቤተሰቦቼ ግን ከባድ ችግር ውስጥ ይገኛሉ። ጓደኞቼ እየደገፏቸው ነው እየኖሩ ያሉት…መጥፎ ሁኔታ እያሳለፉ እንደሆነ ይገባኛል።”

የቤተሰቡ ሁኔታ ማወቅ ያልቻለው ጌትነትም “ትልቅ ጭንቀት፣ ትልቅ ችግር ፈጥሮብኛል” ይላል።

“ከነበርኩበት ጥሩ ኑሮ፣ ከለመድኩት ማኅበራዊ ህይወት፣ ከለመድኩት ማኅበረሰብ…ሁሉንም የለመድኳቸውን ነገሮች ድንገት ስጣቸው ህይወቴን በስቃይ የተሞላ አድርጎታል።”

በዚህ ላይ ከመንግሥት ጠባቂ መሆኑ አእምሮን የሚነካ ቢሆንም በአንጻሩ ግን ከሥነ አእምሯዊ እና አካላዊ ጥቃት “በማምለጤ ደስ ይለኛል” ይላል።

“እዚህ…በሰላም ወጥቼ በሰላም እገባለሁ። የአእምሮ እረፍት አለኝ። ስጋት ስለሌለብኝ…ጥሩ ሁኔታ ላይ እገኛለሁ ብዬ መመስከር እችላለሁ” ይላል።

ኪሩቤልም በበኩሉ “የትግራይ ተወላጅ ሆኜ ወደ አዲስ አበባ መመለስ ማለት በቃ ‘ወደ ገሃነመ መመለስ ማለት’ኮ ነው” ይላል።

“በየቀኑ አሰሩኝ እያልኩ በጠራራ ፀሐይ ምድር ሁለት ሱሪና ሁለት ጃኬት ከመልበስ ተገላገልኩ። የህሊና እስረኛ ነበርኩ፤ የህሊና ነጻነት አገኘሁ” ሲል ከስደት ያገኘውን ስሜት ያስረዳል።

ኪሩቤል እንደሚለው ሲንቀሳቀስ ልታሰር እችላለሁ በሚል ስጋት ለለውጥ የሚሆነውን ልብስ ደርቦ ከቤቱ እንደሚወጣ ተናግሯል።

“እዚህ ቢቸግረኝም… የትግራይ ተወላጅ በመሆኔ የሚደርስብኝ ግፍ የለም። የትግራይ ተወላጅ በመሆኔ አልሰቃይም።”

በአንጻሩ ግን ኢትዮጵያ፣ ሕዝብን እና አገርን ሊያገለግሉ የሚችሉ የሰለጠኑ ከፍተኛ ባለሙያዎች ማጣቷ ማኅበራዊ፣ መንግሥታዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖ ሊያሳድር እንደሚችል ባለሙያዎቹ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

መብራህቶም በዋነኛነት አስፈላጊ የሆኑ ሙያተኞች ከአገር መውጣታቸው “ትልቅ ጉዳት አለው ብዬ ነው የማምነው” ይላል።

ኢትዮጵያ በዓለም የነበራት መልካም ገጽታ እንዲበላሽ ትልቅ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል የሚገልጸው ደግሞ ጌትነት ነው።

መንግሥት “ማግኘት የሚገባውን ገቢ አያገኝም ማለት ነው። ይሄ ደግሞ የአገሪቱ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲበላሽ ምክንያት ሊሆን ይችላል” ይላል።

መንታ መንገድ

“አእምሮዬ ውስጥ የነበረው አገር የሚል እምነት እንዲፈርስ ስለተደረገ፣ ስለደበዘዘ አገር የምለው የለኝም” ያለው መብራሃቶም ወደ ኢትዮጵያ የሚመለስበት ዕድል እንደማይታየው ይናገራል።

ታምራትም ከዚህ የተለየ ሃሳብ የለውም።

ኪሩቤል በበኩሉ “ትግራይ እንደ አገር ከቆመች ወደ ሃገሬ የመመለስ ፍላጎት አለኝ።…በአገሬ በሰላም መስራት ከቻልኩ ለአገሬና ለራሴ ስል እመለሳለሁ። ይሄ ካልሆነ ግን ኢትዮጵያ አገሬ ናት ብዬ ወደ ኢትዮጵያ የምመለስበት ሁኔታ ያለ አይመስለኝም። እንጃ፣ እናየዋለን” ብሏል።

ጋብ ብሎ የነበረውና በፌደራል መንግሥትና በትግራይ ኃይሎች መካከል ሲካሄድ ቆይቶ ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በቅርቡ ተቀስቅሷል።

ይህ ተመልሶ የተቀሰቀሰው ጦርነት ተጨማሪ የጅምላ እስር፣ ግፍ እና የባለሙያዎች ስደት ያስከትል ይሆናል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

*ለቤተሰባቸው ደኅንነት ሲሉ ስማቸው እንዲቀየር የጠየቁ