አሜሪካን በጦርነት ማሸነፍ የሚከብዳት ኢራን የምትከተለው የፍልሚያ አማራጭ

ወታደር

የፎቶው ባለመብት, BBC World Service

የንባብ ጊዜ: 4 ደቂቃ

አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ እየፈጸሙ ባሉት ጥቃት ምክንያት የቴህራን ወታደራዊ አቅም እንደተዳከመ ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ "የአየር እና የባሕር ኃይላቸው ወድሟል። አመራሮቻቸው ሞተዋል። እንነጋገር ብለው ጠይቀውኝ ነበር። ግን 'ዘግይቷል' አልኳቸው" ብለዋል።

ኢራን በእስራኤል እንዲሁም የአሜሪካ ወታደራዊ ሰፈር በሚገኝባቸው የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ላይ የአጸፋ ጥቃት መፈጸም ቀጥላለች።

አሜሪካ እና እስራኤል በወታደራዊ አቅም የበላይነቱን ይዘዋል በተባለበት ሁኔታ ውስጥ የኢራን ወታደራዊ ስትራቴጂ ምን ይመስላል?

አቅም የማስጨረስ ስትራቴጂ

ሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ኢንስቲትዩት በተባለው ዩናይትድ ኪንግደም በሚገኘው ቲንክ ታንክ ውስጥ የመካከለኛው ምሥራቅ ተንታኝ የሆኑት ዶ/ር ኤች ኤ ሄልየር እንደሚሉት፤ ኢራን እየተከተለች ያለው ወታደራዊ ስትራቴጂ አሜሪካ እና እስራኤልን "በተለመደው የጦርነት ስልት" የማሸነፍ አይደለም።

የኢራን ግጭቱን "ማራዘም፣ ቀጣናዊ ማድረግ እና የምጣኔ ሃብት ቀውስ መፍጠር" መሆኑን ያስረዳሉ።

"ኢራን በመደበኛ ጦርነት ልታሸንፍ አትችልም። ሌሎች አገራት በቀላሉ ድል እንዳያገኙ በማድረግ እና የምጣኔ ሃብት ውድቀት በማስከተል ነው ልትቀጥል የምትችለው" ይላሉ።

በፈረንሳይ በሚገኘው 'ሴንተር ፎር ኢንተርናሽናል ስተዲስ' ተባባሪ ፕሮፌሰር ኒኮል ግራጅዊስኪ እንደሚናገሩት የኢራን አካሄድ "የማዳከም ጦርነት" ማድረግ ነው።

ተዋጊዎች እንዲዳከሙ እና አቅማቸው እንዲሟጠጥ ማድረግ ትሻለች።

የጦር መሣሪያ

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto via Getty Images

ይህ ወታደራዊ ስትራቴጂ የሥነ ልቦና ገጽታም አለው።

ኢራን ባለፈው ዓመት ከእስራኤል ጋር ባደረገችው የ12 ቀናት ጦርነት "ዒላማ መምታትን ሳታስብ ንጹኃን የሚኖሩባቸው አካባቢዎች ላይ ጥቃት በመፈጸም ሥነ ልቦናዊ ጫና ለመፍጠር" መሞከሯን ባለሙያዋ ይገልጻሉ።

ኢራን በዋነኛነት ጥቅም ላይ የምታውለው ሚሳዔል እና ድሮን ነው።

ኢራን ከእስራኤል ጋር ባደረገችው የ12 ቀናት ጦርነት ባለስቲክ ሚሳዔሎቿ ተጎድተዋል። ምን ያህል ባለስቲክ ሚሳዔል እንደቀራትም በግልጽ አይታወቅም።

ኢራን የጦር መሣሪያውን የምታመርተው እና የምታከማቸው በድብቅ ሥፍራዎች መሆኑን ተንታኟ ይጠቅሳሉ።

እስራኤል እንደምትለው፤ እስከ አውሮፓውያኑ ጥር 2026 ድረስ በሰበሰበችው መረጃ መሠረት ኢራን 2,500 ሚሳዔሎች አሏት።

እነዚህ ሚሳዔሎች በአጭር ርቀት የሚወነጨፉ (እስከ 1,000 ኪሎ ሜትር ድረስ) እና የረዥም ርቀት ተወንጫፊ (ከ1,000 አስከ 3,000 ኪሎ ሜትር ድረስ) ናቸው።

የኢራን ባለሥልጣናት እንደሚሉት ሰጂል የተባለውን ሚሳዔል ጨምሮ ሌሎች የጦር መሣሪያዎችን ተጠቅማለች።

ይህ ሚሳዔል እስከ 2,000 ኪሎ ሜትር ድረስ እንደሚወነጨፍ ተገልጿል። መሣሪያው ከድምጽ የሚፈጥን (hypersonic) መሆኑን ቴህራን አስታውቃለች።

'የሚሳዔል ከተሞች'

የኢራን መገናኛ ብዙኃን ከምድር በታች የተገነቡ ሚሳዔሎች ማምረቻ እና ማከማቻዎች የሚገኙባቸውን አካባቢዎች 'የሚሳዔል ከተሞች' ብሎ ይጠራቸዋል። ስለ ትክክለኛ መጠናቸው እና አቅማቸው የተረጋገጠ መረጃ የለም።

ከፍተኛ የአሜሪካ ኮማንደር ጄነራል ዳን ክሬን እንደሚሉት፤ ኢራን ውጊያው ከተጀመረበት ቀን አንስቶ የባለስቲክ ሚሳዔል ክምችቷ ወደ 86 በመቶ ወርዷል።

የኢራን ሚሳዔል በአውሮፓውያኑ የካቲት 4 ድረስ ወደ 23 በመቶ እንደሚያሽቆለቁል የአሜሪካ ማዕከላዊ ዕዝ አስታውቋል።

የመካከለኛው ምሥራቅ ተንታኝ የሆኑት ዶ/ር ኤች ኤ ሄልየር እንደሚሉት፤ ኢራን የእስራኤልን መሠረተ ልማት እና የአሜሪካን የመካከለኛው ምሥራቅ የጦር ሰፈሮች ለመምታት የሚያስችል አቅም አላት። በሆርሙዝ ሰርጥ የሚጓጓዛውን ነዳጅ ማስተጓጎልም ትችላለች።

"በሆርሙዝ ሰርጥ የተወሰነ ቢሆንም ቀውስ ከተፈጠረ ዓለም አቀፍ ምጣኔ ሃብት ይናጋል" ይላሉ።

ከዓለም ነዳጅ 20 በመቶው በሆርሙዝ ሰርጥ ይተላለፋል። ኢራን ሰርጡን ከመዝጋቷ ባሻገር መርከቦች ላይ ጥቃት ለመፈጸም ዝታለች።

የሻሂድ ድሮን

ተባባሪ ፕሮፌሰር ኒኮል ግራጅዊስኪ እንደሚናገሩት፤ ኢራን የላቀ አቅም ያላቸው ሚሳዔሎች እጥረት ቢገጥማት እንኳ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ድሮን ያከማቸች አገር ናት።

ከጦርነቱ በፊት በሺዎች የሚቆጠሩ ድሮኖች እንዳመረተች ይታመናል። የድሮኖቹ ዲዛይን ከሩሲያ የተቀዳ ነው።

ይሄንን ቴክኖሎጂ አሜሪካም ለመጠቀም ሞክራለች። እነዚህ ድሮኖች ቀጥተኛ ጥቃት ከመፈጸም ባሻገር የአየር ክልልን ያውካሉ።

"የአየር መቃወሚያን ማዳከም የሚችሉ ድሮኖች ናቸው። ሩሲያ በዩክሬን ላይ ተመሳሳይ መሣሪያ ተጠቅማለች" በማለት ባለሙያዋ ያስረዳሉ።

አሜሪካ በበኩሏ የኢራን የድሮን ክምችት 73 በመቶ መውረዱን ገልጻለች።

ቴል አቪቭ መቀመጫውን ያደረገው 'ኢንስቲትዩት ፎር ናሽናል ሰኪውሪቱ ስተዲስ' እንደሚለው፤ አሜሪካ እና እስራኤል በተለያዩ የጦር መሣሪያዎች ከ2,000 በላይ ጥቃት ፈጽመዋል።

ኢራን የፈጸመችው የአጸፋ ጥቃት 571 ሚሳዔሎች እና 1,391 ድሮኖች ያካተተ ነው።

ጦርነቱ እየተራዘመ ከሄደ በዚህ መጠን የጦር መሣሪያ መጠቀም ለተዋጊዎቹ እንደሚከብድ ተንታኞች ይናገራሉ።

የኢራን ተዋጊ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የተራዘመ ውጊያ

ኢራን በመካከለኛው ምሥራቅ ለረዥም ጊዜ የዘለቀ የታጠቀ ኃይል ያላት አገር ናት።

ኢራን አሁን ላይ መሠማራት የሚችሉ 610 ሺህ ተዋጊዎች እንዳሏት ይገመታል። ይህም 350 ሺህ መደበኛ ወታደሮችን እና 190 ሺህ የእስላማዊ አብዮታዊ ዘብ አባላትን ይጨምራል።

ኢራን በየመን የሚገኙት የሁቲ አማጽያንን ጨምሮ በኢራቅ ያሉ ተዋጊዎችም ይደግፏታል። የሊባኖሱ ሄዝቦላህ እንዲሁም የፍልስጤሙ ሐማስም ከጎኗ ናቸው።

እነዚህ 'አክሲስ ኦፍ ሬዚስታንስ' በሚል የሚጠሩት ቡድኖች በቀጣናው ኢራንን ይደግፋሉ። ሐማስ ከአውሮፓውያኑ 2023 ወዲህ በእስራኤል በደረሰበት ጥቃት ተዳክሟል።

ሆኖም ኢራን የተራዘመ ውጊያ ማካሄድ እንደምትችል ተንታኞቹ ይናገራሉ።

ኢራን እና ኢራቅ በተዋጉት ወቅት ኢራን ያነሰ ወታደራዊ አቅም ስላላት የቴህራን ከተሞች ጥቃት ቢፈጸምባቸውም ውጊያውን ማስቀጠል ችላለች።

"ዋናው ነጥብ የደኅንነት እና የፖለቲካ መዋቅሩ ምን ያህል ታማኝ ሆኖ ይቀጥላል? የሚለው ነው" ሲሉ ተባባሪ ፕሮፌሰር ኒኮል ግራጅዊስኪ ያስረዳሉ።

"ሚሳዔል ተኳሾቹ ከፍተኛ ጫና እና ድካም ውስጥ ስለገቡ ከዒላማ ውጭ እየተኮሱ ነው። የቅንጅት መጓደል ይስተዋላል። የኢራን የሚሳዔል ክምችት ላይ የሚደርሰው ጥቃት ሲበረታ የጦርነቱ ቀጣናዊነት እየሰፋ ይሄዳል" ሲሉም ያክላሉ።

ቀጣናዊ ጦርነት

ወደ ቱርክ የአየር ክልል የገባ የኢራን ባለስቲክ ሚሳዔል በሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) የአየር መቃወሚያ አማካኝነት መክሸፉ ተገልጿል።

ኢራን እና አሜሪካን ለማሸማገል ጠይቃ የነበረችው ቱርክ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ "ሁሉም ወገኖች ግጭቱን ከማባባስ መቆጠብ አለባቸው" ብላለች።

ተንታኟ እንደሚሉት፤ የኢራን ግብ አጎራባት አገራት ጦርነቱን መቋቋም እንዲያቅታቸው ማስገደድ ነው።

በዚህ መንገድ አሜሪካን ወደ ድርድር ጠረጴዛ ለማምጣት እና የሚደርሰውን ጥቃት ለማስቆም ይሞከራል።

"ኢራን በዚህ መንገድ ምን ያህል ስኬታማ እንደምትሆን አሁን ላይ ለመገመት አልችልም" ይላሉ ባለሙያዋ ተባባሪ ፕሮፌሰር ኒኮል ግራጅዊስኪ።

ዶ/ር ኤች ኤ ሄልየር በበኩላቸው የባሕረ ሰላጤው አገራት ኢራን ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ቢቃወሙም የቴህራን የአጸፋ ምላሽ የደኅንነት ስጋት ከሆነባቸው አሜሪካን መደገፍ ሊጀምሩ ይችላሉ ይላሉ።

"የባሕረ ሰላጤው አገራት እዚያ ነጥብ ላይ ደርሰዋል ብዬ አላስብም። ግን ያንን የምናይበት ጊዜ እየተቃረበ ይመስለኛል" ሲሉ ያክላሉ።