የኢራን ጦርነትን ለማስቆም የቀረበውን ሃሳብ ኮንግረሱ ውድቅ ማድረጉን ዋይት ሃውስ በደስታ ተቀበለ

ካፒቶል ሂል

የፎቶው ባለመብት, Bloomberg via Getty Images

የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

ዋይት ሃውስ፤ የአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ እየወሰዱ ያሉትን ወታደራዊ እርምጃ ለማስቆም የተደረገውን ሙከራ ውድቅ ማድረጉን በደስታ መቀበሉ ተገለጸ። የአገሪቱ ሴኔት ተመሳሳይ እርምጃ ከአንድ ቀን በፊት መውሰዱም ይታወሳል።

ምክር ቤቱ የጦርነት የሥልጣን ውሳኔ የተሰኘውን ሕግ 219 ለ212 በሆነ ጠባብ ድምጽ ውድቅ አድርጎታል። ህጉ ቢጸድቅም ከፕሬዝዳንቱ ድምጽን በድምጽ መሻር ላያልፍ ስለሚችል ከተምሳሌታዊነት ያለፈ ሚና አይኖረውም ነበር ተብሏል።

ትራምፕ የኮንግረሱን ፈቃድ ሳያገኙ ጥቃት መጀመራቸው የተቹት ዴሞክራቶች፤ ፕሬዚዳንቱ በራሳቸው ጥቃት ለመፍቀድ የሚያስችል አይነት ስጋት ነበር ወይ ሲሉ ጠይቀዋል።

አሜሪካ እና እስራኤል ባለፈው ቅዳሜ በኢራን ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ የጀመሩ ሲሆን ጦርነቱ ለምን ያህል ጊዜ ሊቆይ እንደሚችል ግልጽ አይደለም።

ሐሙስ ዕለት ከተካሄደው የምክር ቤቱ ድምጽ አሰጣጥ በኋላ ዋይት ሃውስ ባወጣው መግለጫ "ኮንግረሱ የአሜሪካን ህዝብ ከኢራን አገዛዝ ምኞቶች እና ሊመጡ ከሚችሉ ስጋቶች ለመጠበቅ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዡን ህገ መንግሥታዊ ሥልጣንን አረጋግጧል" ብሏል።

ዴሞክራቶቹ የሜይኑ ጃሬድ ጎልደን፣ የኦሃዮው ግሬግ ላንድስማን፣ የቴክሳሱ ሄንሪ ኩዌላር እና የካሊፎርኒያው ሁዋን ቫርጋስ ከሪፐብሊካኖች ጋር ቆመው ውሳኔውን በመቃወም ከፓርቲያቸው በተቃራኒ ቆመዋል።

ሪፐብሊካኖቹ የኬንታኪው ቶማስ ማሲ እና የኦሃዮው ዋረን ዴቪድሰን በበኩላቸው ሕጉን በመደገፍ ከዴሞክራቶች ጋር ተቀላቅለዋል።

የቀድሞው የአገሪቱ ጦር አባል ዴቪድሰን በሰጡት መግለጫ "የፕሬዚዳንት ትራምፕ የቅድሚያ ለአሜሪካ መርህ የዓለም አቀፍ ጦርነትን ውድቅ ማድረግ ነበር ተብሎ ይታሰብ ነበር" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ውሳኔው በኮንግረሱ ጸድቆ ቢሆን ኖሮ የአሜሪካ ጦር በኢራን የጀመረው እርምጃ ቆሞ በሕግ አውጪዎች ይሁንታ ላይ እንዲመሠረት ያደርግ ነበር።

ኮንግረሱ ሕጉን እንዲቃወም የገፋፉት የምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤ ማይክ ጆንሰን ውጤቱን አወድሰው፤ ሕጉ በኮንግረሱ ጸድቆ ቢሆን በጣም ከባድ ስህተት" ይሆን ነበር ብለዋል።

"ጦርነት ላይ አይደለንም" ሲሉ ከመከራከር ባለፈ "ጦርነት ውስጥ የመሆን ፍላጎት የለንም። ይህ የተወሰነ ዘመቻ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

በሁለቱም ምክር ቤቶች ውስጥ ያሉ ዴሞክራቶች ትራምፕ የኮንግረሱን ሃሳብ ችላ ብለው ለጦርነቱ ግልጽ ያልሆኑ ምክንያቶችን እና ዓላማዎችን አቅርበዋል ሲሉ ተከራክረዋል። ይህንን ሃሳብ ዋይት ሃውስ ውድቅ አድርጎታል።

በኮንግረሱ እና በሴኔት ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሪፐብሊካኖች ውሳኔውን ለጊዜው ቢቃወሙም ጦርነቱ ከተስፋፋ ወይም ከዘገየ አቋማቸውን ሊቀይሩ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ትራምፕ ሐሙስ ዕለት በዋይት ሃውስ እንደተናገሩት አሜሪካ የኢራንን የድሮን እና የሚሳኤል መሠረተ ልማት "በየሰዓቱ" እየመታች ነው።

"ስለዚህ የአየር ኃይል የላቸውም፣ የአየር መከላከያ የላቸውም። ሁሉም ጠዋጊ ጄቶቶቻቸው ወድመዋል። የመገናኛ ዘዴያቸው ተመቷል" ብለዋል።

ኢራን "እንዴት ስምምነት መፈጸም እንችላለን" በማለት መደወሏንም ትራምፕ ተናግረዋል።

"ትንሽ ዘግይታችኋል ብያቸዋለሁ" ሲሉ ፕሬዝዳንቱ ገልጸው "አሁን ከእነሱ በላይ መዋጋት እንፈልጋለን።"

ፕሬዝዳንቱ ያለ መደበኛ የጦርነት አዋጅ ወታደራዊ እርምጃ የመውሰድ ሰፊ ስልጣን ቢኖራቸውም፣ በሕግ መሰረት ጦርነቱ በጀመረ በ48 ሰዓታት ውስጥ ኮንግረሱን ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ የትራምፕ አስተዳደር ይህንን ሂደት ማክበሩን አረጋግጠዋል።

አፈ ጉባኤ ጆንሰን በበኩላቸው የትራምፕ አስተዳደር ለስምንቱ ከፍተኛ የኮንግረስ መሪዎች ቡድን ከጥቃቱ በፊት ማሳወቃቸውን ገልጸዋል።