አሜሪካ እና ቬንዙዌላ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ለማስቀጠል ተስማሙ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ታህሳስ ላይ ባካሄደችው ወታደራዊ ዘመቻ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን የወሰደችው አሜሪካ እና ቬንዙዌላ የዲፕሎማሲ እና የቆንስላ ግንኙነታቸውን በድጋሚ ለማስቀጠል ተስማሙ።
የአሜሪካ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ሁለቱ ወገኖች መረጋጋትን ለማስፈን፣ የኢኮኖሚ ማገገምን ለመደገፍ እና የፖለቲካ ስምምነት ለመፍጠር የጋራ ጥረት እንደሚያደርጉ ገልጿል።
የአሜሪካ ጦር በታህሳስ መጨረሻ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን ከያዘበት ዘመቻ በኋላ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸው እየተሻሻለ ቢሆንም፣ የሁለትዮሽ ግንኙነቱ ይፋ መደረጉ እጅግ ተምሳሌታዊ እርምጃ ተደርጎ ተወስዷል።
በካራካስ የሚገኘው እና በ2019 የተዘጋው የአሜሪካ ኤምባሲ በድጋሚ የተከፈተ ሲሆን ዋሽንግተን ለቬንዙዌላ አዲስ ዲፕሎማት ሾማለች።
የቬንዙዌላ መንግስት "በጋራ መከባበር ላይ የተመሰረተ አዲስ ገንቢ ውይይትን ለማራመድ ፈቃደኛ መሆኑን" ሐሙስ ዕለት አስታውቋል።
ግንኙነቱ "የቬንዙዌላ ህዝብን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ደስታ" ማስገኘት እንዳለበት ገልጿል።
የካራካስ መግለጫ ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለየ መልኩ ስለሽግግር መንግሥት ወይም ወደፊት ስለሚኖር ምርጫ ምንም የገለጸው ነገር የለም።
በዚህ ወር በአሜሪካ ችሎት የሚቀርቡትን ኒኮላስ ማዱሮን እና ሌሎች ባለስልጣናት እንደ ህገወጥ የማዕድን ቁፋሮ እና የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ባሉ ተግባራት ውስጥ የሚሳተፍ የወንጀል ድርጅትን እየመሩ ነው ስትል አሜሪካ ከሳለች።
ምንጮች ለቢቢሲ እንደገለጹት በቦጎታ፣ ኮሎምቢያ ከሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ተጨማሪ ዲፕሎማቶች በቅርቡ ወደ ካራካስ እንደሚዛወሩ ይጠበቃል። ይህ እርምጃ ባለስልጣናት ፊት ለፊት እንዲደራደሩ እና የቆንስላ አገልግሎቶችን እንዲሰጡ ያግዛቸዋል ተብሏል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተሳትፎው የቬንዙዌላ ሕዝብ "በዴሞክራሲያዊ መንገድ ወደተመረጠ መንግስት ሰላማዊ ሽግግር እንዲያደርግ ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥር ሂደት" በማመቻቸት ላይ ያተኮረ ነው ብሏል።
የአሜሪካ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ዳግ ቡርጋም ሐሙስ ዕለት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ዋሽንግተን ከኢራን በፊት በቬንዙዌላ ጣልቃ መግባቷ "ድንቅ ስትራቴጂካዊ እርምጃ" ነው።
አሜሪካ እና እስራኤል ባለፈው ቅዳሜ በኢራን ላይ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ ጀምረዋል። የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ በመጀመሪያው ዕለት ጥቃት ተገድለዋል።
የፕሬዚዳንት ትራምፕን ብሔራዊ የኢነርጂ የበላይ ምክር ቤት የሚመሩት ቡርጋም ሐሙስ ዕለት ጣልቃ ገብነቱ "ነዳጅ ወደ አሜሪካ እንዲፈስ" እንደሚያግዝ አክለዋል።
የአሜሪካ ጦር በቬንዙዌላ ላይ ጥቃት ሰንዝሮ ማዱሮን ከተቆጣጠረ በኋላ አሜሪካ ከቬንዙዌላ ጋር አዲስ የነዳጅ ስምምነቶችን ፈጽማለች።
ካራካስ በአሜሪካ ቁጥጥር ስር የታገደባትን ነዳጅ እንድትሸጥ ዋሽግተን የፈቀደች ሲሆን፣ ቬንዙዌላም በነዳጅ ዘርፍ ላይ ተጨማሪ የውጭ ኢንቨስትመንት እንዲገባ ለመፍቀድ ሕጓን ቀይራለች።
ረቡዕ ዕለት የቬንዙዌላ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት ዴልሲ ሮድሪጌዝ እና ቡርጋም ሁለቱ አገራት በማዕድን ቁፋሮ ልማት አብረው እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
ቬንዙዌላ በዓለም ላይ ትልቁን የነዳጅ ክምችት ከመያዟ በተጨማሪ በወርቅ፣ በአልማዝ፣ በአስፈላጊ ማዕድናት እና በብርቅዬ ማዕድናት የበለፀገች አገር ናት።















