የኢራን አዲሱ ጠቅላይ መሪ ፈተናዎች፡ ጦርነት፣ ቅቡልነት እና ሥልጣን

የሞጅታባ ኻሜኒን ምስል የያዘ ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images, BBC

የንባብ ጊዜ: 5 ደቂቃ

እሁድ ዕለት ምሽት የኢራን ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ መደበኛ ዝግጅቱን አቋርጦ እምብዛም ባልተለመደ ሁኔታ ስሜት በተመላበት መልኩ የአዲሱን መሪ መመረጥ ይፋ አደረገ።

የፕሮግራሙ አቅራቢ የቀድሞው መሪ አሊ ኻሜኒ ልጅ፣ ሞጅታባ ኻሜኒ አባታቸውን ተክተው መመረጣቸውን ተናገረ።

የኢራን የሊቃውንት ጉባዔ አዲሱን መሪ ለመምረጥ የፈጀበት ጊዜ በጣም አጭር የሚባል ነው።

አሜሪካ እና እስራኤል የካቲት 21 2018 ዓ.ም ለመጀመርያ ጊዜ በወሰዱት ወታደራዊ እርምጃ አሊ ኻሜኒ ከተገደሉ በኋላ በሳምንቱ ልጃቸው የአገሪቱን ከፍተኛ ሃይማኖታዊ እና ፖለቲካዊ ሥልጣን ተረክበዋል።

የአሊ ኻሜኒ ሞት እስላማዊ ሪፐብሊክ እአአ በ1979 ሥልጣን ከያዘበት ጊዜ አንስቶ ታይቶ የማይታወቅ እና አስደንጋጭ ነበር።

አዲሱን የኢራን መሪ ለመምረጥ ምክክሩ የተደረገው በዝግ ስብሰባ ነው። 88 አባላት ያሉት የሊቃውንት ጉባዔ አዲሱን መሪ የመምረጥ ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነት ያለበት ሲሆን ቦታው ክፍት በሚሆንበት ወቅትም እስላማዊ ሪፐብሊኩን የመከታተል ኃላፊነት ተጥሎበታል።

አይደለም አገሪቱ በጦርነት እና በቀውስ መሃል ሆና ቀርቶ በሰላማዊ ወቅትም ይህ የሊቃውንት ጉባዔ ውሳኔዎችን የሚያሳልፈው እጅግ ሚስጥራዊነቱ በተጠበቀ ሁኔታ ነው።

ከጀርባ የነበሩት ሞጅታባ ኻሜኒ

ስለ ሞጅታባ ኻሜኒ የሚታወቀው እጅግ በጣም ትንሽ ነው። የ56 ዓመቱ ሞጅታባ ተመርጠው ወይንም ተሹመው የመንግሥት ኃላፊነት ይዘው አያውቁም።

በሺአዎች ዘንድ እንደ ቅዱስ ከተማ በምትቆጠረው ቆም በሚገኝ ሃይማኖታዊ ትምህርት ቤት ሥነ መለኮት አጥንተዋል። ለተወሰኑ ዓመታት ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን አስተምረዋል።

ይህ ግን አያቶላህ ለመሆን ለሚፈልጉ የሃይማኖት ሊቃውንት የተለመደ ነው።

ምንም እንኳ አባታቸው ሥልጣናቸውን እንዲረከቡ እንደማይፈልጉ በስፋት ቢነገርም፣ ሞጅታባ ኻሜኒ የሚሰጧቸውን ትምህርቶች በራሳቸው ተነሳሽነት ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ማቆማቸው ተገልጿል።

አሊ ኻሜኒ ልጃቸው በአገሪቱ ፖለቲካም ሆነ በሕዝብ ጉዳዮች በግልጽ እንዲሳተፉ ለማድረግ ዳተኛ መሆናቸው በዘር የሚወረስ ሥልጣን ላይ ያላቸው አመለካከት የፈጠረው መሆኑ ሲነገር ቆይቷል።

የሞጅታብ ኻሜኒን እና የአባታቸውን ምስል ያዙ ደጋፊዎች

የፎቶው ባለመብት, Majid Asgaripour/WANA (West Asia News Agency) via REUTERS

የምስሉ መግለጫ, የሞጅታብ ኻሜኒን እና የአባታቸውን ምስል ያዙ ደጋፊዎች

ነገር ግን ከመጋረጃ ጀርባ ሞጅታባ የአገሪቱን አስተዳደር ሲያሽከረክሩ እንደነበር ይታመናል። እነዚህም የአገሪቱ ደህንነት፣ ወታደራዊ ተቋማት፣ ንግድ እና ፖለቲካዎችን የሚመለከቱ ናቸው።

አንዳንድ ተንታኞች በዝምታ በኢራን ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደሩ እንደነበር በማንሳት ይከራከራሉ።

በኢራን እአአ በ 2005 በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ እና ማህሙድ አህመዲነጃድ ሥልጣን ላይ በወጡበት ወቅት በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ ገብተዋል በሚል ውንጀላ ቀርቦባቸው ነበር።

በ2005 ምርጫ ወቅት ሞጅታባ ወግ አጥባቂ ሃይማኖታዊ ቡድኖች እና ከደህንነት ኃይሎች ጋር ግንኙነት ያላቸውን አካላት አህመዲንነጃድን እንዲደግፉ ለማድረግ መንቀሳቀሳቸውን የኢራን የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ ያሉ ብዙ ሰዎች ያምናሉ።

እአአ በ2009 አህመዲነጃድ ሁለተኛውን ምርጫ ማሸነፋቸው ይፋ ሲደረግ ውጤቱን የተቃወሙት የተቃዋሚ መሪው ሚር ሁሴን ሞሳቪን ጨምሮ በርካታ ተቃዋሚዎች አደባባይ ወጡ። በወቅቱ የአገሪቱ መንግሥት በተቃዋሚ ሠልፈኞቹ ላይ ጠንካራ እርምጃ የወሰደ ሲሆን ሙሳቪ ከአስራ ስድስት ዓመታት በላይ በቁም እስር ላይ ቆይተዋል።

በአንድ ሰው ዙሪያ የተመሰረተ ሥርዓት

ሞጅታባ ኻሜኒ

የፎቶው ባለመብት, Morteza Nikoubazl/NurPhoto via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በኢራን የሚተላለፉ በርካታ ወሳኝ ውሳኔዎች የአዲሱን የበላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ የመጨረሻ ይሁንታ ማግኘት ይኖርባቸዋል

የአገሪቱን ከፍተኛ ሥልጣን ለተቆጣጠሩት ሞጅታባ ሁኔታዎች የበለጠ ውስብሰብ ናቸው። ኢራን ከዩናይትድ ስቴትስ እና ከእስራኤል ጋር ውጊያ ውስጥ ገብታለች። በቅርቡ አገዛዙን በመቃወም በመላ አገሪቱ የተካሄደው ሕዝባዊ አመጽም ካስከተለውን ተጽዕኖም ሥርዓቱ አላገገመም።

እስላማዊ ሪፐብሊክ ከአራት አስርት ዓመታት በላይ ሲንቀሳቀስ የቆየው በፖለቲካ ቡድኖች መካከል ከፍተኛ ፉክክር እንዲኖር በማድረግ እና ለተቋማት አነስተኛ ሥልጣን በመስጠት ነው።

ነገር ግን ሁል ጊዜ ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮች ላይ የመጨረሻው ይሁንታን የሚሰጡት የበላይ መሪው ናቸው።

አሊ ኻሜኒ ከሞቱ በኋላ ያለው ሳምንት ስርዓቱ በአንድ ሰው ላይ ምን ያህል ጥገኛ እንደሆነ አሳይቷል። የበላይ መሪው በሌለበት፣ የውሳኔ አሰጣጡ ቆሟል እና እርግጠኛ አለመሆን በፖለቲካ ሥርዓቱ ውስጥ ሰፍኗል።

የሃይማኖት ሊቃውንቱ ሞጅታባን ለመሾም በፍጥነት መንቀሳቀሳቸውም ግልጽ የሆነ ምልክት ለመላክ ይመስላል። በኢራን ምንም መሠረታዊ ነገር አልተለወጠም፤ ባለሥልጣናቱ በግል እንደሚናገሩት "ሕይወት በተለመደው መንገድ ቀጥሏል።"

ሆኖም አዲስ መሪን መቀበል እንደማስታወቁ ቀላል አይደለም።

ታማኝነት ማሳየት

የአዲሱ መሪ መመረጥ ይፋ ከተደረገ ጀምሮ በሥርዓቱ ውስጥ ጫና መፈጠር ጀምሯል። የፖለቲካ እና ወታደራዊ ተቋማት ለአዲሱ መሪ ያላቸውን አጋርነት በይፋ ገልጸዋል።

አብዮታዊ ዘብ በበኩሉ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች ያላቸውን ታዛዥነትን ከማወጅ ባለፈ ሞጅታባን አዲሱ "የድብቁ ኢማም ምክትል" በማለት በሺዓ የፖለቲካ ንግግር ዘንድ ጥቅም ላይ የሚውል ትልቅ አገላለጽን ተጠቅሟል።

ሞጅታባ ሥልጣን መያዛቸውን ተከትሎ የጸጥታ አካላት ተቃውሟቸውን ለማሰማት ለሚሞክሩ ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

እነዚህ እርምጃዎች በግዛቲቱ የሥልጣን ቁንጮ ላይ ያለውን አንድነት ለማሳየት የታቀዱ ናቸው። ነገር ግን ለሌላ ዓላማም ያገለግላሉ።

የአገሪቱ በተለያየ መዋቅር ውስጥ ያሉ የደህንነት እና ወታደራዊ ተቋማት ለበላይ መሪው ያላቸውን ታማኝነት ካልገለፁ ለተፎካካሪ የፖለቲካ ቡድኖች ወይም የስርዓቱ ተቺዎች ለውጡን ላይ ያላቸውን ተቃውሞ እንዲያጠናክሩ ዕድል ሊፈጥር ይችላል።

አመራሩ ይህንን ለመከላከል የቆረጠ ይመስላል።

የቅቡልነት ጥያቄ

አዲሱ የበላይ መሪ የልሂቃን ድጋፍ በፍጥነት እየተጠናከሩ ቢሄዱም፣ የቅቡልነት ጥያቄዎች ከፊታቸው ተደቅኗል።

ከብዙ የሃይማኖት አባቶች በተለየ ሞጅታባ በሃይማኖታዊ ሰዎች ዘንድ አያቶላህ በመባል አይጠሩም። የመንግሥት ቴሌቭዥን ይህንን ክፍተት ለመቅረፍ በሚመስል መልኩ "አያቶላህ ሞጅታባ ኻሜኒ" በማለት ጠርቷቸዋል።

እአአ በ1989 አባታቸው የበላይ መሪ ሲሆኑ ተመሳሳይ ፈተና አጋጥሟቸው ነበር።

የአዲሱ የኢራን የበላይ መሪ ምስል

የፎቶው ባለመብት, Majid Asgaripour/WANA (West Asia News Agency) via Reuters

የምስሉ መግለጫ, ሞጅታባ ከኢራን መሪዎች ጀርባ በመሆን ለረዥም ዓመታት ሲሰሩ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን የኢራን ባለሥልጣናትን ፊት ለፊት መጋፈጥ ይጠበቅባቸዋል

አሊ ኻሜኒ በፕሬዚዳንትነት ለአስር ዓመታት ያህል ያገለገሉ ሲሆን በፖለቲካ ስርዓቱ ውስጥም ጠንካራ አጋሮች ነበሯቸው። ሞጅታባ በተቃራኒው አብዛኛውን ጊዜ ያሳለፉት ከሕዝብ ዕይታ ውጪ ነው።

በአንድ ወቅት በአዛውንቱ ኻሜኒ ዙሪያ የነበሩ ከፍተኛ አዛዦች፣ የስለላ ኃላፊዎች እና የፖለቲካው ዘዋሪዎች ባለፈው ዓመት በሰኔ ወር ለ12 ቀናት በዘለቀው ጦርነት ተገድለዋል። የተረፉትም ቢሆኑ ባለፈው ሳምንት አባታቸውን፣ እናታቸውን እና ሚስታቸውን በገደለው የአየር ድብደባ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ለብዙ ቀናት ሞጅታባ ራሳቸው በእነዚያ ጥቃቶች እንደሞቱ ይታመን ነበር።

ከባድ የሆኑት ከፊት ያሉት ቀናት

ሞጅታባ የኢራንን ሰፊ ስትራቴጂ ከመቅረጻቸው በፊት፣ አዲሱ መሪ በመጀመሪያ ራሳቸውን በእስላማዊ ሪፐብሊክ ውስብስብ የኃይል መዋቅር ውስጥ ማጽናት አለባቸው።

ይህ ደግሞ ለብዙ አሥርተ ዓመታት ከዘለቀው ምስጢራዊነት ብቅ ማለት እና አዲስ በተሾሙ ወታደራዊ አዛዦች፣ በተፎካካሪ የፖለቲካ ቡድኖች እና አሁን ሊቀበሏቸው በማይችሉ የሃይማኖት መሪዎች ላይ ሥልጣን ማሳየት ማለት ነው።

ከዚሁ ጎን ለጎን ከሁለት የዓለም ኃያላን ጋር የገጠሙትን ጦርነት በሚመለከት ውሳኔ ማሳለፍ አለባቸው። አሜሪካም ሆነች እስራኤል በአዲሱ መሪ ላይ ጥቃት ሊሰነዝሩ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።

በሰፊው ሕዝብ መካከልም ቢሆን ሁኔታው ​​ይበልጥ እርግጠኝነት የማይታይበት ነው። በቅርቡ በተደረጉ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ለአሊ ኻሜኒ ሞት የተመኙ ሠልፈኞች አገራቸው የለውጥ ንፋስ ይዳስሳታል ብለው ተስፋ አድርገው ነበር።

ይልቁንም አሁን ሌላ ኻሜኒ መንበሩን ተቆጣጥረዋል። የአሁኑ ደግሞ ወጣት፣ ምናልባትም የበለጠ ጉልበት ያለው ነገር ግን የአባቱን አገዛዝ ለማስቀጠል ከረዱት የደህንነት ተቋማት ጋር በቅርብ የተቆራኘ ነው።

በአሁኑ ጊዜ እስላማዊ ሪፐብሊክ በጣም አስቸጋሪ በሆነ ጊዜ ውስጥም ቢሆን የተረጋጋ መሆኑን ለማሳየት እየሞከረ ነው።

ሞጅታባ ኻሜኒ ደግሞ ይህንን ወደ እውነተኛ ሥልጣን ሊለውጡት ይችላሉ ወይ የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው፣ ይህም የአሁኑን ጦርነት ውጤት ብቻ ሳይሆን የኢራንን መንግሥት የወደፊት ዕጣ ፈንታ ሊበይን ይችላል።