የእስራኤል ጦር ከ40 ዓመት በፊት የሞተ ወታደሩን አስከሬን ፍለጋ በሊባኖስ ያካሄደው ዘመቻ ያስከተለው ከባድ ጉዳት

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እስራኤል በኢራን ከሚደገፈው ሔዝቦላህ ጋር የምታደረገው የምድር እና የአየር ውጊያ ተከትሎ በሊባኖስ በርካታ ሰዎች ተገድለዋል።
የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው በምሥራቃዊ ቤካ ሸለቆ የእስራኤል ጦር አንድ ምሽት ባካሄደው ዘመቻ ቢያንስ 41 ሰዎች ሲገደሉ 40 ደግሞ ቆስለዋል።
ከሟቾቹ መካከል ሦስት የሊባኖስ ወታደሮች የሚገኙበት ሲሆን፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ሕፃናትን ጨምሮ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።
በናቢ ቺት የተደረገው ወታደራዊ ዘመቻ ዓላማ ከ40 ዓመት በፊት በሊባኖስ የጠፋውን የእስራኤል አየር ኃይል ባልደረባ አስከሬን ለማግኘት ነበር።
ቅዳሜ ዕለት በመንደሩ በሚገኝ የመቃብር ስፍራ አንድ የተቆፈረ ጉድጓድ ይታይ ነበር።
"እዚያ እንዳለ አስበው ነበር፤ ግን ምንም አልነበረም" ያሉ የአካባቢው ነዋሪ መቃብሩ ባዶውን ነበር ሲሉ ተናግረዋል።
በከተማው ውስጥ በመሣሪያ የተመታ እና የወደመ መኪና በጥይት ተበሳስቶ መቀመጫዎቹም በደም ተለውሰው ይታያሉ።
በአካባቢው ያሉ ሕንፃዎች ወደ ፍርስራሽ ክምርነት ተለውጠዋል፤ መሬቱ ላይ የደረሰውን ፍንዳታ ተከትሎ አንድ ትልቅ ጉድጓድ ተፈጥሯል።
በፍርስራሾቹ ውስጥ የሕፃናት መጽሐፍ፣ ሥዕሎች እና የማብሰያ ዕቃዎችን ጨምሮ አካባቢው የሰላማዊ ሰዎች መኖሪያ እንደነበር የሚያሳዩ ማስረጃዎች እዚህም እዚያም ይታያሉ።
በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው ሔዝቦላህ ጋዜጠኞች የውድመቱን መጠን እንዲመለከቱ ወደ መንደሩ እንዲገቡ ፈቅዷል።
ይህ ታጣቂ እና የፖለቲካ ቡድን በዩናይትድ ኪንግደም፣ በአሜሪካ እና በሌሎችም አገራት አሸባሪ ድርጅት ተብሎ ተፈርጇል።
የሊባኖስ ጦር አርብ ምሽት አራት የእስራኤል አውሮፕላኖች ሊባኖስ ከሶሪያ ጋር በምትዋሰንበት ድንበር አቅራቢያ ሲመጡ ማየቱን አስታውቋል፤ ሁለቱ ካረፉ በኋላ የጦሩን ልዩ ኃይል አባላት አውርደዋል።
"ትልቅ የአየር ድብደባ" ወዲያው መጀመሩንም ጨምረው ገልጸዋል።
በሔዝቦላህ እና በእስራኤል መካከል ከሚደረገው ጦርነት ራሱን ለማግለል የሞከረው የሊባኖስ ጦር ሠራዊት እንዳስታወቀው፣ ወታደሮቹ ያረፉበትን ቦታ ለመለየት "ፈጣን የማንቂያ እና የመከላከያ እርምጃዎችን" ወስደዋል ብለዋል።
በናቢ ቺት የእስራኤል ወታደሮች እና የሔዝቦላህ ተዋጊዎች እንዲሁም መኖሪያቸውን በሚከላከሉ ሲቪሎች መካከል ግጭት ተቀስቅሷል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አንድ ፍንዳታ በደረሰበት አካባቢ የሚገኝ ባለሥልጣን "እኩለ ሌሊት ላይ በመንደሩ አንድ በኩል እንግዳ የሆነ እንቅስቃሴ ተሰማን። ለተወሰኑ ተልዕኮዎች የተሰማራ የእስራኤል ኮማንዶ ቡድን ነበር" ሲል ተናግሯል።
"ከዚያም ድርጊቱን የሚቃወሙ ከበቧቸው እና ከባድ የተኩስ ልውውጥ ተጀመረ። ከዚያም የአየር ኃይሉ ድብደባውን በማጠናከር ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለ ጥቃት አደረሰ።"
ሔዝቦላህ እና የአካባቢው ነዋሪዎች እስራኤል ለልዩ ኃይሎች ወታደሮች ሽፋን ለመስጠት እና እንዲወጡ ለማስቻል በአካባቢው 40 የአየር ድብደባዎችን አድርጋለች ብለዋል።
የእስራኤል ወታደሮች የሊባኖስን ወታደራዊ ልብስ ለብሰው እና የሔዝቦላህ እስላማዊ የጤና ድርጅት ምልክት ያለበትን አምቡላንስ ተጠቅመው እንደመጡ የዐይን እማኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የሊባኖስ ጦር አዛዥ በኋላ ይህንን ለአካባቢው መገናኛ ብዙኃን አረጋግጠዋል፤ ነገር ግን የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት አስተያየት እንዲሰጥ ቢቢሲ ላቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።
መንደሩ እስራኤል ነዋሪዎች ለቅቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ያስተላለፈችበት ሲሆን፣ የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ዘመቻው ከመጀመሩ በፊት ዳግም ሰላማዊ ሰዎች አካባቢውን እንዲለቅቁ ትዕዛዝ ተላልፎላቸዋል።
አጎቱ እና ሌሎች ዘመዶቹ የተገደሉበት መሐመድ ቾክር እሱና ቤተሰቡ ከሔዝቦላህ ጋር ምንም የሚያገናኛቸው ነገር እንደሌለ ስለሚያውቁ በአንጻራዊ ሁኔታ ደኅንነት ተሰምቷቸው እንደነበር ተናግሯል።
"አጎቴ እና ልጁ ጡረታ የወጡ ወታደሮች ናቸው፣ ሌላኛው ልጁ ደግሞ መምህር ነው። ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ጋር ግንኙነት የለንም። እኛ ሺዓዎች ነን፤ ሔዝቦላህን እንወዳለን፤ ግን የሔዝቦላህ አባላት አይደለንም። ሁላችንም የሊባኖስ ጦር አባላት ነን" ብለዋል።
"ዛሬ ምን ሊሰማኝ ይገባል? ይህ አጎቴ፣ ልጆቹ እና ልጆቻቸው ናቸው።"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቤተሰቡን ከፍርስራሹ ሥር ለማውጣት ቡልዶዘር ይዞ የመጣ ሌላ ዘመዱ በመንገድ ላይ በተነሳ ግጭትን በጥይት ተመትቶ መሞቱን ተናግሯል።
ሌላ የአካባቢው ነዋሪ በእስራኤል ልዩ ኃይል ጥቃት ከተገደሉት ሰዎች መካከል የመሐመድ አጎት እና ሌሎች ዘመዶቹ እንደሚገኙበት አስረድቷል።
የእስራኤል ጦር ቢቢሲ ላቀረበለት ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።
በወታደራዊ ዘመቻው ወቅት በመንደሩ ውስጥ የነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች እና ወደ ሌላ ቦታ ሸሽተው የነበሩ ሰዎች ቅዳሜ ዕለት ጥቃቱ ያደረሰውን ውድመት ለመመልከት ተሰብስበው ነበር።
"ሁሉንም ነገር በቦምብ ደብድበዋል። ይህ አስከፊ ነው" ያለው አሊ ሻኩር ነው።
"እዚህ በነበረው ሰው ተገርመው ይመስለኛል ምክንያቱም በቦምብ ሲደበድቡ ሁሉም ሰው እንደለቀቀ ያስቡ ነበር።"
በመንደሩ ውስጥ ያለ ሌላ ሰው ደግሞ ሰዎች ልጆቻቸውን እንዲወጡ አድርገው ሌሎቹ ግን እዚያው ቆይተዋል፤ ምክንያቱም ማንኛውም ጥቃት ከዚህ በፊት ካጋጠማቸው ጋር ተመሳሳይ ይሆናል ብለው ነበር ያመኑት።
"ብዙውን ጊዜ ሁለት ወይም ሦስት ቤቶችን ይመቱ ነበር፤ አሁኑ ግን የተለየ ነበር። ያለማቋረጥ ነበር ድብደባው የሚፈጸመው። ምን ያህል ትልቅ እንደነበር ማየት ትችላላችሁ" ብሏል። "ግን እዚህ ያለን አንበገርም የምንል ነን እና ተገዳድረናቸዋል።"
በፈረሱ ቤቶች ዙሪያ የምትዞር አንዲት ሴት "እስራኤል ኢፍትሃዊ በሆነ መንገድ እያጠቃችን ነው። እኛ ሔዝቦላህ ነን እናም እናሸንፋለን" ስትል ትጮኻለች።
የእስራኤል ጦር በአንድ ሌሊት ባካሄደው ዘመቻ አንድም የሠራዊቱ አባል እንዳልተጎዳ አስታውቋል።
አክሎም "የሞቱትን እና የጠፉትን የእስራኤል ልጆች በሙሉ ወደ ቤታቸው ለመመለስ ባለን ጥልቅ ቁርጠኝነት ቀንም ሆነ ሌሊት ያለማቋረጥ ዘመቻችን ማካሄድ እንቀጥላለን" ብሏል።
ነገር ግን የሮን አራድ ባለቤት ታሚ የእስራኤል መሪዎች የወታደሮችን ሕይወት አደጋ ላይ እንዳይጥሉ አሳስባለች።
"እስካሁን ድረስ የምንናገረው በውሳኔ ሰጪዎቹ ከግንዛቤ አንደልገባ እንረዳለን፤ ስለዚህ ግልጽ ማድረግ አስፈላጊ ነው፤ በሮን ላይ ምን እንደደረሰ ለማወቅ ያለን ፍላጎት የእስራኤል ወታደሮችን አደጋ ላይ የሚጥል ከሆነ ወዲያውኑ ይቆማል" ስትል በፌስቡክ ገጿ ላይ ጽፋለች።
"በእኛ ዕይታ፣ የሕይወት ቅድስና የሚመጣው የተዋጊውን አስከሬን ለቀብር ለመመለስ ከመወሰን ቁርጠኝነት በፊት ነው።"
የእስራኤል ጦር ቅዳሜ ዕለት ባወጣው መግለጫ፣ ሌሊቱን በደቡባዊ ሊባኖስ እና በምሥራቃዊ ቤካ ሸለቆ የተፈጸሙት ጥቃቶች የሔዝቦላህ የጦር መሳሪያዎችን እና "የአሸባሪው ሔዝቦላህ ወታደራዊ ቦታዎችን" መምታታቸውን ጠቅሷል።
በናቢ ቺት ዙሪያ በተፈፀሙት ጥቃቶች ዒላማዎች ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ቢቢሲ ላቀረበው ጥያቄ ግን ምላሽ አልሰጠም።
የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፣ ከሰኞ ጀምሮ በእስራኤል ወታደራዊ እርምጃ ቢያንስ 294 ሰዎች ተገድለዋል።
በመንደሩ ውስጥ አንዳንዶች በደረሰው ጉዳት ሲያዝኑ ሌሎች ደግሞ እስራኤል የወታደሯን አጽም ማግኘት እንዳልቻለች ከተገነዘቡ በኋላ ድል እንደተሰማቸው ተናግረዋል።
"ቆመው መጡ ግን አጎንብሰው እንዲሄዱ አድርገናል" ሲል አንድ ሰው ተናግሯል።















