ሄዝቦላህ በሊባኖስ ያለው ሚና ምንድን ነው? ከእስራኤል ጋር ጦርነት ውስጥ ሊገባ ይችላል?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ማክሰኞ ዕለት ሌባኖስ ውስጥ ሄዝቦላህ ለመረጃ ልውውጥ የሚጠቀምባቸው ‘ፔጀሮች’ በተመሳሳይ ሰዓት መፈንዳታቸውን ተከትሎ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቆስለዋል።
ቢያንስ 12 ሰዎች ተገድለዋል፤ 3000 ያህሉ ሲቆስሉ አብዛኛዎቹ ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው ታውቋል።
ምንም እንኳን ሄዝቦላህ ባላንጣውን እስራኤልን ተጠያቂ ቢያደርግም፣ ይህ ውስብስብ ጥቃት እንዴት እንደደረሰ ግልጽ አይደለም። የእስራኤል ባለሥልጣናትም እስካሁን አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።
በእስራኤል እና በሄዝቦላ መካከል በጋዛ ጦርነት ምክንያት የተቀሰቀሰው አለመግባባት ላለፉት 11 ወራት ቀጥሏል።
ሄዝቦላህ ማን ነው?
ሄዝቦላህ የሺዓ ሙስሊም ቡድን ነው።
ሊባኖስ ውስጥ ከፍተኛ የፖለቲካ ተጽዕኖ አለው። በሊባኖስ ኃያል የሆነው ወታደራዊ ክፍል በቁጥጥሩ ሥር ነው።
እአአ በ1980ዎቹ ነው የተመሠረተው። የኢራን የሺዓ ሙስሊሞች እስራኤልን በመቃወም ነው የመሠረቱት።
በወቅቱ ሊባኖስ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ነበረች። እስራኤልም ደቡባዊ ሊባኖስን ተቆጣጥራ ነበር።
በአውሮፓውያኑ 1992 በሊባኖስ ውስጥ በተካሄደው ብሔራዊ ምርጫ ሄዝቦላህ ተወዳድሯል። ከፍተኛ የፖለቲካ ሚናም ይጫወታል።
ወታደራዊ ክንፉ በሊባኖስ ባሉ የእስራኤል እና የአሜሪካ ኃይሎች ላይ ከፍተኛ ጥቃቶች ሰንዝሯል።
እስራኤል በ2000 ከሊባኖስ ስትወጣ ሄዝቦላህ እስራኤልን ማስወጣት እንደቻለ ሲገልጽ ነበረ።
ከዚያ ወዲህ በሺዎች የሚቆጠሩ ተዋጊዎች አሉት። በደቡብ ሊባኖስ ሚሳዔል እና ሌሎችም የውጊያ መሣሪያዎች ያሉት ሲሆን፣ ውዝግብ ውስጥ ባሉ የድንበር አካባቢዎች ከእስራኤል ጋር ግብግቡን ቀጥሏል።
ምዕራባውያን አገራት፣ እስራኤል፣ የገልፍ አገራት እና አረብ ሊግ ሄዝቦላህን አሸባሪ ቡድን ብለው ፈርጀውታል።
በ2006 ሄዝቦላህ ድንበር ተሻግሮ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ በሄዝቦላህ እና በእስራኤል መካከል ጦርነት ተነስቶ ነበር።
የእስራኤል ወታደሮች በደቡባዊ የሊባኖስ ድንበር በኩል ገብተው ሄዝቦላህ ላይ ጥቃት አካሂደዋል።
ሆኖም ግን ሄዝቦላህ አሁንም ድረስ በወታደራዊ አቋሙ እየተጠናከረ ዘልቋል። የተዋጊዎቹ ቁጥርም ጨምሯል። የተሻሉ መሣሪያዎችንም ታጥቋል።

የሄዝቦላህ መሪ ሐሰን ናስረላህ ማን ናቸው?
ሼኽ ሐሰን ናስረላህ የሃይማኖት መምህር ሲሆኑ ከ1992 አንስቶ ሄዝቦላህን እየመሩ ይገኛሉ።
ሄዝቦላህ በፖለቲካ እና በወታደራዊውም ዘርፍ ሚናው እንዲጎላ አስችለውታል።
ከኢራኑ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሚኒ ጋር ቅርብ ናቸው።
ከ1981 (እአአ) ጀምሮ በሊባኖስ ልዩ ወኪል በሚል ሼኽ ሐሰን ናስረላህ፣ በአያቶላህ አሊ ኻሚኒ ተሹመዋል።
በእስራኤል ግድያ እንዳይፈጸምባቸው በመፍራትም ለዓመታት በአደባባይ ሳይታዩ ቆይተዋል። ሆኖም በየሳምንቱ በቴሌቭዥን አማካይነት ለአባሎቻቸው እና ለደጋፊዎቸቻቸው መልዕክት ያስተላልፋሉ።
ከፍተኛ ቁጥር ያላቻው የሌባኖሳውያን ድጋፍ እና የሠለጠነ እና የታጠቀ ሠራዊት ያለው ሄዝቦላህ በሊባኖስ ውስጥ ከፍተኛ ተጽእኖ ያለው ቡድን አለው።
ሄዝቦላህ ምን ያህል ኃያል ነው?
ሄዝቦላህ ከመንግሥታዊ መዋቅር ውጪ ከሆኑ እና ከፍተኛ ትጥቅ ካላቸው ኃይሎች መካከል አንደኛው ነው። ኢራን ለቡድኑ የገንዘብ እና የጦር መሣሪያም ታቀርባለች።
የቡድኑ መሪ ሐሰን ነስረላህ ሄዝቦላህ 100 ሺህ ተዋጊዎች እንዳሉ ከዚህ ቀደም ተናግረዋል።
ነገር ግን ገለልተኛ ወገኖች የቡድኑን ተዋጊዎች ቁጥር ከ20 ሺህ እስከ 50 ሺህ ይገምታሉ።
አብዛኞቹ ተዋጊዎች የሠለጠኑ እና የውጊያ ልምድ ያላቸው ናቸው። በሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ተሳትፈው ተዋግተዋል።
ሴንተር ፎር ስትራቴጂክ ኤንድ ኢንተርናሽናል ስተዲስ ባስቀመጠው ግምት መሠረት ሄዝቦላህ ከ120,000 እስከ 200,000 የሚደርሱ ሮኬቶች እና ሚሳዔሎች አሉት።
የአየር መቃወሚያ እና የመርከብ ጦር መሣሪያዎችም አሉት። ዒላማ የሚመቱ ሚሳዔሎቹ እስራኤል ውስጥ ጥቃት ማድረስ ይችላሉ።
በእነዚህም ሄዝቦላህ የፍልስጤሙ ሐማስ ካለው የጦር መሣሪያ የላቁ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ሄዝቦላህ ከእስራኤል ጋር ጦርነት ውስጥ ይገባል?
ሐማስ በእስራኤል ላይ ጥቃት ከሰነዘረ በኋላ የእስራኤል ጦር በጋዛ ላይ የከፈተውን ጦርነት ተከትሎ ሄዝቦላህ ፍልስጤማውያንን በመደገፍ በእስራኤል ላይ ጥቃት ሲፈጽም ቆይቷል።
በሰሜናዊ እስራኤል እና በጎላን ኮረብታዎች ላይ ተደጋጋሚ የሮኬት ጥቃቶችን አድርሷል። በእስራኤል ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች ላይም የሚሳዔል ጥቃት ፈጽሟል።
አጥፍተው በሚጠፉ ድሮኖችም የእስራኤልን ወታደራዊ ዒላማዎች መትቷል።
የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት በምላሹ የሄዝቦላ ይዞታዎች ላይ የአየር ጥቃት ሲፈጽም ቆይቷል። በተጨማሪም በሊባኖስ ውስጥ ቡድኑ በሚገኝባቸው አካባቢዎች ላይ በታንክ እና በተቀጣጣይ መሣሪያዎች ጥቃት ሰንዝሯል።
የተባበሩት መንግሥታት እንዳለው በእነዚህ ጥቃቶች ሳቢያ ከሊባኖስ 90,000 ሰዎች ተፈናቅለዋል።
100 ንጹሀን ዜጎች እና 366 የሄዝቦላህ ታጣቂዎች በእስራኤል ጥቃት ተገድለዋል።
የእስራኤል ባለሥልጣናት እንደሚሉት በሄዝቦላህ ጥቃት ሳቢያ 60,000 ሰዎች ሲፈናቀሉ 10 ሰላማዊ እስራኤላውያንን ጨምሮ 33 ሰዎች ተገድለዋል።
ግጭቶቹ እንዳሉ ሆነው ሁለቱም ወገኖች ወደለየለት ጦርነት የሚወስዳቸውን መስመር ላለማለፍ እየሞከሩ ይገኛሉ።
ከፍተኛ ጥቃት ሲፈጸም ግን ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ ሊወጡ ይችላሉ የሚል ስጋት አንዣቧል።












