በሞጅታባ ኻሜኒ ወደ ሥልጣን መምጣት የተከፋፈሉት ኢራናውያን

ሞጅታባ ኻሜኒ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የ56 ዓመቱ ሞጅታባ ኻሜኒ የአባታቸውን አክራሪ አቋም ያራምዳሉ ተብሎ ይጠበቃል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ሞጅታባ ኻሜኒ የኢራን አዲሱ ከፍተኛ መሪ እና ተተኪ ሆነው የተሰየሙት አባታቸው አያቶላህ አሊ ኻሜኒ አሜሪካ እና እስራኤል በአገሪቱ ላይ ጥቃት በከፈቱበት የመጀመሪያ ቀን መገደላቸውን ተከትሎ ነው።

አንዳንድ የኢራንን መንግሥት የሚደግፉ ሰዎች ለአብዮታዊ ዘቡ ቅርብ የሆነ ጠንካራ አዛዥ መሾማቸውን በማስመልከት ደስታቸውን ለመግለጽ አደባባይ ወጥተዋል።

ነገር ግን ሌሎች ኢራናውያን ለቢቢሲ እንደተናገሩት አዲሱ የበላይ መሪ ለውጥ ያመጣሉ ብለው አያምኑም።

በዋና ከተማዋ ቴህራን የሚኖር በ30ዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኝ ሰው "ከጸጉር የቀጠነ የለውጥ ዕድል እንኳ በስርዓቱ ውስጥ የለም" ሲል ለቢቢሲ አስተያየቱን ሰጥቷል።

88 አባላት ያሉት የሃይማኖት ሊቃውንት ጉባዔ ለአሊ ኻሜኒ ቅርብ ያልሆነ የበላይ መሪ መምረጥ አልቻለም ሲል የተሰማውን ቅሬታ ገልጿል።

"ስለዚህ አብዛኛው ነገር ባለበት ይቀጥላል። አዲሱም መሪያቸውን ለመደገፍ እንኳን የሚያሰሙትን መፈክር መቀየር አልፈለጉም" ሲል አክሏል።

ለዓመታት በኢራን አስተዳደር ውስጥ ሞጅታባ ኻሜኒ ከጀርባ በመሆን ተጽዕኖ እንደሚያደርጉ ሲነገር ቆይቷል።

በርካቶች አዲሱ መሪ የአባታቸውን ጠንካራ ፖሊሲዎች ያስቀጥላሉ ሲሉ ግምታቸውን ተናግረዋል።

በ20ዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የምትገኝ እና በቴህራን የምትኖር ሴት ሞጅታባ ኻሜኒ "ከአባታቸው በባሰ ጨቋኝ ይሆናሉ" ስትል ተናግራለች።

ግለሰቧ ለቢቢሲ "በጦርነቱ እንዲሞቱ [ከፍተኛ ባለሥልጣናቱ] ነው ተስፋ የማደርገው፤ አለበለዚያ በእርሱ አገዛዝ ስር ከሆንን ሁላችንም እናልቃለን" ብላለች።

ሌላ በ30ዎቹ ውስጥ የሚገኝ የቴህራን ነዋሪ "በጣም በቀለኛ ነው። አባቱን ገድለዋል፤ ስለዚህ በዋዛ አያልፋቸውም። በአሜሪካ ላይ የበቀል እርምጃ የማይወስድ ከሆነ እኛ ላይ ነው እልሁን የሚወጣው። እስራኤል እና አሜሪካ ዒላማ ያደርጉታል ብዬ ነው ተስፋ የማደርገው" ብሏል።

ከእሁድ ምሽት ጀምሮ የኢራን ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ኢሪን፣ ቴህራንን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች የሞጅታባ ኻሜኒ መመረጥን ደግፈው አደባባይ የወጡ ሠልፈኞችን እያሳየ ነው።

በእነዚህ ሠልፎች ላይ ሰዎች የኢራንን ባንዲራ ሲያውለበልቡ ይታያል።

ነገር ግን እስካሁን ድረስ ሞጅታባ ኻሜኒ አደባባይ ላይ ቀርበው ንግግር አላደረጉም ወይንም አልታዩም።

ለቴሌቪዥን ጣቢያው ቃለ ምልልስ የሰጠች አንዲት ሴት "በጣም ደስተኞች ነን። ሊቃውንት ጉባኤን አመሰግናለሁ። የፈጣሪ አጅ እየጠበቀን ነው፣ ኻሜኒ አሁንም መሪያችን ናቸው" ብላለች።

ሌላ ሴት ደግሞ "ከዚህ የተሻለ ነገር ሊመጣ አይችለም። ደስ ብሎናል" ብላለች።

ቢቢሲ ፐርዢያ እና ቢቢሲ ቬሪፋይ እሁድ ዕለት ምሽት በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተጋሩ "ሞት ለሞጅታባ" እና "ሞት ለአገልጋዩ" የሚሉ የተቃውሞ ድምጽ የተሰማባቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎችን እንዲሁም የድጋፍ ድምጻቸውን ለማሰማት "ፈጣሪ ታላቅ ነው" እያሉ የሚጮሁ ሠልፈኞችን ተመልክተዋል።

የኢራን መሪዎች ምስልን የያዙ ሠልፈኞች

የፎቶው ባለመብት, WANA/via Reuters

የምስሉ መግለጫ, የሞጅታባ ኻሜኒን መመረጥ ደግፈው አደባባይ የወጡ ሠልፈኞች የእርሳቸውን እና የአባታቸውን ምስል ይዘው ታይተዋል

በርካታ ኢራናውያን የአዲሱ መሪ መመረጥን በማስመልከት ደስታቸውን ለመግለጽ ሰኞ ዕለት በቴህራን ኤንሄላብ አደባባይ ተሰብስበው ነበር።

የኢራን የመንግሥት ቴሌቪዥን ደግሞ እሁድ ዕለት ደስታቸውን ለመግለጽ አደባባይ የወጡ ብዙ ሰዎችን አሳይቷል።

አደባባይ የወጡት ሰዎች የሞጅታባ ኻሜኒ እና የአባታቸውን ፎቶዎች ይዘው የመኪኖቻቸውን ጥሩንባ ሲያስጮሁ እና ባንዲራዎችን ሲያውለበልቡ ታይተዋል።

"አሁን መንገዱ በእሱ አመራር እንደሚቀጥል እርግጠኞች ነን" ሲል አንድ ሰው ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግሯል።

አንዲት ሴት "ጥልቅ ደስታዋን" ስትገልጽ፣ ሞጅታባ ኻሜኒ "ከአባቱ ጋር በጣም ተመሳሳይ" እንደነበር ተናግራለች።

"ከተወዳደሩት እጩዎች ሁሉ እሱ በጣም የሚገባው እና [ከቀድሞው መሪ ጋር] በጣም የሚመሳሰል ነበር።"

የሞጅታባ ኻሜኒ ሹመት የተሰማው እስራኤል እና አሜሪካ ጥቃታቸውን በቀጠሉበት ወቅት ነው

የፎቶው ባለመብት, WANA/via Reuters

የምስሉ መግለጫ, የሞጅታባ ኻሜኒ ሹመት የተሰማው እስራኤል እና አሜሪካ ጥቃታቸውን በቀጠሉበት ወቅት ነው

በቴህራን አቅራቢያ በምትገኘው ካራጅ ከተማ፣ አንድ ነዋሪ ከሹመቱ በፊት ስለ ሞጅታባ ኻሜኒ ብዙም እንዳልሰማ ተናግሯል።

በ20ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኘው ይህ ግለሰብ "አሁን ትራምፕ ከእነሱ ጋር ስምምነት ፈጽመዋል ወይስ አልፈጸሙም የሚለው ግልጽ ይሆናል። እሱን ዒላማ ማድረግ አለባቸው" ሲል ተናግሯል።

ሌላ ሰው ደግሞ "ይህ ማለት ምንም ነገር አይለወጥም ማለት ነው" ብሎ እንደሚያምን ተናግሯል።

"ያው መንገድ ነው የሚቀጥለው፣ ምናልባትም የባሰ ነው" ካለ በኋላ "ይዘልቃል ብዬ አላስብም" ሲል አክሏል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን አዲሱ ጠቅላይ መሪ ምርጫ ላይ ሚና መጫወት እንደሚፈልጉ እና ሞጅታባ ኻሜኒ "ተቀባይነት የሌላቸው" መሆናቸውን ተናግረዋል።

እናም ሹመቱ ይፋ ከመደረጉ ከጥቂት ሰዓታት በፊት ትራምፕ ያለፈቃዳቸው ሥልጣን የሚረከብ ማንኛውም ሰው "ለረጅም ጊዜ እንደማይቆይ" ተናግረዋል።

እስራኤል የአሊ ኻሜኒ ልጅ አዲሱ መሪ ከመሆኑ በፊት "እያንዳንዱን ተተኪ ማሳደዷን እንደምትቀጥል" በመግለጽ ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች።