በትግራይ ጦርነት የተሳተፉ ሴቶች የተፈጠረባቸው የአዲስ ጦርነት ስጋት

የፎቶው ባለመብት, Abeba Amdu
የ22 ዓመቷ አበባ አምዱ በጥሩ ሁኔታ ማለፍ የነበረበት ሕይወቷ በጦርነት ተውጦ ቆይቷል። በትግራይ ሌላ ግጭት ማየትም አትሻም።
በትግራይ ክልል ዳግም ጦርነት ይቀሰቀሳል ብለው በርካቶች ይሰጋሉ።
አበባ ከዚህ ቀደም በነበረው ጦርነት በትግራይ ሠራዊት ውስጥ ሆና ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ተዋግታለች። ጦርነቱ ከተቋጨ ሦስት ዓመት ቢያልፍም አሁንም ድረስ ጠባሳዋ አልሻረም።
"ሁሉንም ነገር አጣሁ" ትላለች።
ከጦርነቱ በፊት ተስፋ የተጣለባት እግር ኳስ ተጫዋች ነበረች። ከሰባት ዓመቷ ጀምሮ እግር ኳስ ተጫውታለች። የ70 እንደርታ የሴቶች እግር ኳስ ክለብ አጥቂ ሆና የተሰለፈችውም በ17 ዓመቷ ነው።
"ፌምኒስት ነኝ" የምትለው አበባ ሴቶችን ከስፖርት የሚያገለውን ዘልማዳዊ አመለካከት አትቀበልም።
አበባ ጎበዝ ተማሪም ስለነበረች በመቀለ አይቲ እያጠናች ነበር። የወደፊት ሕይወቷ ምን እንደሚመስል ዕቅዶች አስቀምጣም ነበር።
ሆኖም በድንገት ዓለሟ ተመሰቃቀሰለ። መጀመሪያ ላይ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በመነሳቱ ትምህርቷን አቋረጠች። ከዚያም ጦርነቱ ፈረዳ።
"ቤተሰቦቼ በምን ዓይነት ሁኔታ እንዳለፉ ስለማውቅ በጦርነቱ አላምንበትም ነበር" ትላለች።
እናት እና አባቷ የህወሓት ታጋዮች ነበሩ።
በትግራይ ጦርነት የኤርትራ ሠራዊት በፌደራል መንግሥት ጎን ተሰልፎ ተዋግቷል። ደም አፋሳሹ ጦርነት በፕሪቶሪያ ስምምነት አማካኝነት አክትሟል።
የአሸማጋዩ የአፍሪካ ኅብረት ልዑክ የሆኑት የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ ወደ 600 ሺህ ሰዎች በጦርነቱ መገደላቸውን ገልጸዋል።
አበባ ወደ ጦርነት የገባችው በምርጫ ሳይሆን ግዴታዋን መወጣት ስለነበረባት ነው።
ስለ ህወሓት ታሪክ እየሰማች ባደገችበት ቤት ውስጥ አባቷ ደርግን ለመጣል ከ50 ዓመታት በፊት የከፈሉት መስማዕትነት ሲነገራት ቆይቷል። ያደረችው በአገር ፍቅር እና ቆራጥነት ስሜት ተሞልታ ነው።
የትግራይን ሠራዊት ለመቀላቀል የወሰነችው አንድም መደፈርን በመፍራት ነው። ሴቶች "በጠላት ኃይል" ወሲባዊ ጥቃት እየተፈጸመባቸው እንደሆነ ሪፖርቶች እየወጡ ነበር።
"ወራሪዎቹ የመጡት ለጥቂቶች አይደለም። የሌሎቹ ተጎጂዎች ዕጣ ፈንታ ይደርሰኛል። እንድዋጋ ያስገደደኝ አጠቃላይ ሁኔታው ነው።"

የፎቶው ባለመብት, Selam Hailu
ከእግር ኳስ ታገኝ የነበረው ደስታ ላይ ጦርነት አጠላበት። ረሃብ እና የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያን ጨምሮ የመሠረታዊ አቅርቦት እጥረት ፈትኗታል።
የጦርነቱ ማብቃት አበባ የጠበቀችውን ሰላም አላመጣም። ወደ ቤተሰቧ እና ወደ እግር ኳስ መመለስ ሌላ የትግል ሜዳ ሆነባት።
"ሰውነቴም አእምሮዬም ከባድ የስሜት ቀውስ ውስጥ ነበር" ትላለች።
ከብቸኛነት ጋር መታገል ያዘች። እሷ ባለፈችበት ያላለፉ ሰዎች እንደማይረዷት ይሰማታል።
"አባቴ የታጋይ ባህሪ የሆነው ቁጣ ለምን ይታይበት እንደነበር አሁን ነው የገባኝ። እንደዚያ ይሆን የነበረው ስላላገገመ እንደሆነ አሁን አውቄያለሁ።"
አበባ የሐዘን እና ግጭት እሽክርክሪት መደጋገሙን ትናገራለች። ከሚወዱት ሰው ጋር መጣላት፣ ሥራ ማቆም እና ለብቻ ማልቀስ።
ለፕሮፌሽና እግር ኳስ ተጫዋች የሚያስፈልው ትኩረት ራቃት። ወደ ሥልጠና ለመመለስ ብትሞክርም "የተቃጠሉ ዓመታትን" ማሰብ ቀጠለች። የቀድሞ ብቃቷን መመለስ አልቻለችም።
ቁስሏን ወደ አንዳች ጠቃሚ ነገር ለማሻገር ለአጭር ጊዜ በጋዜጠኛነት ሠርታለች። 'ወጋሕታ' የተባለ ከ30 ዓመት በታች ያሉ ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾችን የሚያሠለጥን ፕሮጀክትም ጀምራለች።
ተተኪ እግር ኳስ ተጫዋቾችን ለማሠልጠን ተስፋ ብታደርግም በገንዘብ ችግር ብዙ ርቀት መጓዝ አልተቻለም።
የምታደርጋቸው ነገሮች "ሙያዋን ለመለወጥ ሳይሆን" መሸሸጊያ ፍለጋ መሆኑን ትናገራለች።
"ይሄንን ሁሉ የማደርገው መደበቂያ ፈልጌ ነው።"
የአበባ ትልቁ ፍርሃት ጦርነት ዳግመኛ ይነሳል የሚለው ነው።
ባለፈው ታኅሣሥ ላይ በመከላከያ ሠራዊት እና በጦርነቱ ወቅት በአማራ ክልል የተጠቃለሉ ቦታዎች እንዲመለሱ በሚጠይቁ የትግራይ ኃይሎች መካከል ውጊያዎች ተቀስቅሰው ነበር።
በትግራይ የድሮን ጥቃት ሲፈጸም በረራዎች ለሳምንት ተቋርጠው ነበር። የፌራል መንግሥቱ የኤርትራ መንግሥት የትግራይ ኃይሎችን እየደገፈ ነው ሲል ቢከስስም ኤርትራ ክሱን አስተባብላለች።
የፌደራል መንግሥት ሠራዊቱን በትግራይ አቅራቢያ በማሠማራት ለአዲስ ጦርነት እየተዘጋጀ ነው ሲል ህወሓት ይከስሳል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ደግሞ ህወሓት ወደ ክልሉ የሚላከውን በጀት ኃይሉን ለማደራጀት አውሎታል ብለው ይወነጅላሉ።
"አሁን በየቦታው ሌላ ግጭት ይነሳል የሚል ፍርሃት ይታየኛል። ጦርነት አስፈላጊ ነው ብዬ አላምንም። በስተመጨረሻ መፍትሔ የሚያመጣው ድርድር እንጂ ውጊያ እንዳልሆነ አይተናል" ትላለች አበባ።
ሰላም ኃይሉ 30 ዓመቷ ነው። ጠበቃ እና የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ሰላም ከዚህ ቀደም በነበረው ጦርነት ተዋግታለች።
ሰላም የአበባን ስሜት ትጋራለች።

የፎቶው ባለመብት, Rahwa Gebremedhin
የመጀመሪያ ልጇ አምስት ዓመት ሳለ ነበር ውጊያውን የተቀላቀለችው። ለዚህም የራሷ ምክንያት አላት።
ቤተሰቦቿ ጡረተኛ የመንግሥት ሠራተኞች ናቸው። ጦርነቱን ተቀላቅለው ተዳክመው እና በመጥፎ ሁኔታ ውስጥ ተመልሰዋል።
ያለፉበትን መከራ እና ያስተዋሉትን "ወሲባዊ ጥቃት እና የጅምላ ግድያ" ስትሰማ አንድ ነገር ማድረግ አለብኝ ብላ ወሰነች። ከታናሽ እህቷ ጋር የትግራይ ሠራዊትን ተቀላቀሉ።
እንደ ሌሎቹ ሴቶች አጭርም ቢሆን ወታደራዊ ሥልጠና ተሰጣቸው። ሰላም በትግራይ ተራሮች ኑሮን ፈታኝ ሆኖ ነው ያገኘችው። ፈተናው በፆተኛ አመለካከል የታጀበም ነበር።
"ጫካ ውስጥ መሽናት ከባድ ነበር። የወር አበባችን ሲመጣ እና ባህሪያችን ሲለወጥ ማንም አይረዳንም።"
በጣም ከባዱ ፈተና ግን የመጣው ከወታደራዊ አመራሩ ነው።
"በወታደሩ ውስጥ ያለው ችግር ሴቶች ችሎታ እና አቅም አላቸው ብለው አለማመናቸው ነው" ትላለች።
በአሥራዎቹ ዕድሜ ክልል የምትገኝ ሴት ተዋጊ "ጥይት ሳትፈራ የአዛዦችን ቁጣ እና ቅጣት ትፈራ ነበር" በማለትም ትናገራለች።
አብዛኞቹ የፍቅር ግንኙነት እንዲጀምሩ ሲገደዱም ከዝምታ ውጪ አማራጭ አልነበራቸውም።
በዕድሜ ከፍ ያለችው እሷ በመሆኗ እና በሙያዋም ጠበቃ ስለሆነች "መርኅን የጣሱ ግንኙነቶችን" ስትቃወም አንድ ምሽት ታስራ ተቀጥታለች።
ሰላም ጦርነት አሁንም በድጋሚ ይነሳል ብላ ትሰጋለች።
"ወጣቶች ሕጋዊም ይሁን ሕገ ወጥ ማንኛውንም አማራጭ ተጠቅመው ከከተማው እየሸሹ ነው። ሁሉም ሰው ፊት ላይ ፍርሃት ይታያል። ሰዎች ከእልቂት የሚያድናቸው የቆጠቡት ገንዘብ እንደሆነ በማሰብ የሚችሉትን ሁሉ እያከማቹ ነው።"
ሰላም "ከእኛ በላይ ሰላም የሚያስፈልገው የለም። ሌላ መስዋዕትነት ለመክፈል አቅሙ የለንም" ስትልም ታክላለች።
በመቀለ ዩኒቨርስቲ የአስተዳደር መምህርት የሆነችው የ30 ዓመቷ ራሕዋ ገብረመድኅን፤ ጦርነት ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው ሳይሆን ሕልሟን የሚያሰናክል መሆኑን ታምናለች።
ገና ሙያዊ ሕይወቷን እየጀመረች ነበር። ቤት፣ መኪና፣ ልጆች ነበሯት። ነገር ግን "በጠላት ኃይሎች" እየተፈጸመ የነበረውን ግፍ ስታይ የትግራይ ሠራዊትን መቀላቀሏን ትናገራለች።
"ግድያው አስደንግጦኝ ነበር። ሴቶች ወሲባዊ ጥቃት ስለተፈጸመባቸው ተበሳጭቻለሁ። ሁሉም ነገር ነበር የወደመው።"
መምህርቷ ራሕዋ ስለ ጦርነት የምታውቀው በፊልም ነበር። "መንገዱን ማወቅ፣ መታጠቅ፣ መሠልጠን ከባድ ነበር" ትላለች።
ጦርነቱ ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጠባሳ አሳድሮባታል። ወደ ሲቪል ሕይወት መመለስም ፈትኗታል።
ከአስደንጋጭ ሁኔታ በኋላ የሚፈጠር ጭንቀት (PTSD ወይም post-traumatic stress disorder) ምልክቶች እንደሚታዩባት የምትናገረው ራሕዋ "ሁሉም ሴቶች የስሜት ቀውስ ውስጥ ገብተዋል" በማለት ትገልጻለች።
ወደ ማስተማር ብትመለስም "እንደ ቀድሞው አይደለም። ምንም አይሰማኝም። መትረፍ ብቻ ነው የምፈልገው" ትላለች።















