በመካከለኛው ምሥራቅ የሚካሄደውን ጦርነት ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳየ

አሜሪካ እና እስራኤል ሳህራን የነዳጅ ማከማቻ ላይ አየር ድብደባ ከፈጸሙ በኋላ ከፍተኛ እሳት ተነስቷል

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በሳምንቱ መጨረሻ ውስጥ የኢራን የነዳጅ ማምረቻ ተቋማት በአየር ድብደባ ጋይተዋል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የዓለም የነዳጅ ዋጋ ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋጋው በበርሜል ከ110 ዶላር በላይ መድረሱ ተገለፀ።

አሜሪካ እና እስራኤል ከቴህራን ጋር የሚያደርጉት ጦርነት እየተባባሰ በመጣበት በአሁኑ ወቅት በሆርሙዝ የባህር ሰርጥ በኩል የሚተላለፍ የጭነት መርከቦች እንቅስቃሴ ለረዥም ጊዜ ይስተጓጎላል የሚለው ስጋት እያየለ በመምጣቱ የአክሲዮን ገበያዎች ቀንሰዋል።

ኢራን እሁድ ዕለት ሞጅታባ ኻሜኒን አባታቸውን አያቶላህ አሊ ኻሜኒን እንዲተኩ በጠቅላይ መሪነት ሾማለች። ይህም ለአንድ ሳምንት ያህል ግጭት ውስጥ የገቡት ጠንካራ አቋም ያላቸው ልሂቃን አገሪቱን በበላይነት መምራት እንደሚቀጥሉ ያሳያል።

አሜሪካ እና እስራኤል ቅዳሜና እሁድ በኢራን ላይ የሚፈጽሙትን የአየር ድብደባ አጠናክረው በመቀጠል የነዳጅ ማከማቻዎችን ጨምሮ በርካታ ዒላማዎችንም መትተዋል።

ከቀጣናው የሚመጣው የነዳጅ አቅርቦት በከፍተኛ መጠን መስተጓጎሉ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ሸማቾች እና ንግዶች ላይ የዋጋ ጭማሪን ያስከትላል።

ሰኞ ጠዋት በእስያ፣ ብሬንት አንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅን በ24 በመቶ የዋጋ ጭማሪ በ114.74 ዶላር ሲሸጥ ኒሜክስ ላይት ስዊት ደግሞ በ26 በመቶ ጭማሪ በ114.78 ዶላር ሸጧል።።

በእስያ-ፓስፊክ ቀጣና ውስጥ የአክሲዮን ገበያዎች በከፍተኛ ሁኔታ አሽቆልቁለዋል።

የጃፓን ኒኬይ 225 ኢንዴክስ ከ7 በመቶ በላይ ሲቀንስ፣ በሆንግ ኮንግ የሚገኘው ሃንግ ሴንግ ደግሞ ከ3 በመቶ በላይ ወርዷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በአውስትራሊያ የሚገኘው ኤኤስኤክስ 200 እንዲሁ ከ4 በመቶ በላይ ቀንሷል።

ግጭቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከባድ ጉዳት የደረሰበት የደቡብ ኮሪያ ኮስፒ ኢንዴክስ ከ8 በመቶ በላይ በማሽቆልቆሉ የንግድ ልውውጡ ለ20 ደቂቃ እንዲቆም ምክንያት ሆኗል።

ከዓለም የነዳጅ አቅርቦት አንድ አምስተኛ የሚሆነው አብዛኛውን ጊዜ የሚጓጓዘው በሆርሙዝ የባህር ሰርጥ በኩል ነው። ነገር ግን ከአንድ ሳምንት በፊት የጦርነቱ መጀመርን ተከትሎ ይህ ጠባብ መተላለፊያ ከእንቅስቃሴ ውጭ ሆኗል።

በገበያው ውስጥ የሚሳተፉ በርካታ ተቋማት በዚህ ሳምንት የነዳጅ ዋጋ በበርሜል 100 ዶላር እንደሚደርስ ተንብየው ነበር።

በእስያ የነዳጅ ገበያ ውስጥ የ10 በመቶ ጭማሪ ለማሳየት አንድ ደቂቃ ያህል ብቻ የፈጀ ሲሆን ቀጣዩን 10 በመቶ ለመጨመር ደግሞ ተጨማሪ15 ደቂቃ ብቻ ወስዷል።

ባለፈው ሳምንት በባህረ ሰላጤው ውስጥ ነዳጅ የሚያመላልሱ ግዙፍ መርከቦች መንቀሳቀስ ተቸግረው የነበረ ቢሆንም የድፍድፍ ነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ገዢዎች በአንፃራዊነት ዘና ብለው ነበር።

ነገር ግን በሳምንቱ መጨረሻ የተከሰተው ውጥረት እና በኢራንም ሆነ በመላው ባሕረ ሰላጤው የነዳጅ ዘይት መሠረተ ልማቶች ላይ የተፈጸመው ጥቃት ገዢዎች እንዲደናገጡ እና ገበያዎች ጭማሪ እንዲያሳዩ አድርጓል።

አንዳንድ ተንታኞች የሆርሙዝ ባህር ሰርጥ መተላለፊያ እስከ መጋቢት ወር መጨረሻ ተዘግቶ የሚቆይ ከሆነ የነዳጅ ዋጋ በአንድ በርሜል ከ150 ዶላር በላይ እንደሚጨምር ይተነብያሉ።

ከፒተርሰን ዓለም አቀፍ ኢኮኖሚክስ ተቋም የመጡት አድናን ማዛሬይ በአንዳንድ የባህረ ሰላጤ አገራት ውስጥ የነዳጅ ምርት መቆም እና በቀጣናው ውስጥ የተቀሰቀሰው ግጭት ረዘም ላለ ጊዜ ሊቀጥል እንደሚችል መገመታቸው የነዳጅ ዋጋ ላይ ጭማሪ እንዲታይ ምክንያት ናቸው ብለዋል።

የነዳጅ ዋጋ መጨመር ለማዳበሪያ አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንደሚያሳይ እና የምርቶች ዋጋ ሊጨምር እንደሚችል ተተንብይዋል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የዋጋ ጭማሪው ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆይ እንደሆነ ተናግረው የኢራንን የኒውክሌር ስጋትን ለማስወገድ "የሚከፈል ትንሽ ዋጋ" ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።