የነዳጅ ዋጋን ከፍ-ዝቅ የሚያደርገው ኦፔክ ማን ነው? ለምንስ ምርት ይቀንሳል?

የሩሲያ የባሕር ላይ ነዳጅ ማውጫ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሩሲያ በቀን ከ10 ሚሊዮን በላይ በርሜል ነዳጅ ታመርታለች

የዓለማችን ከፍተኛ የነዳጅ አምራቾች ሰሞኑን ምርት እንቀንሳለን ብለዋል። ይህን ባሉ ማግስት የነዳጅ ዋጋ በ7 እጅ አሻቅቧል።

ሳዑዲ አረቢያ፣ ኢራቅ እና ሌሎች የባሕረ ሰላጤው አገራት ዕለታዊ የነዳጅ ምርትን እየቀነሱ ያሉት በአንድ ሚሊዮን በርሜል ነው።

የኦፔክ አባል አገር የሆነችው ሩሲያም እስካለንበት የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ ድረስ ነዳጅን በግማሽ ሚሊዮን በርሜል እቀንሳለሁ ብላለች።

ይህ የኦፔክ አባል አገራት እርምጃ አሜሪካንን አስቆጥቷል።

ኦፔክ ማን ነው?

ኦፔክ+ (Opec+) 23 ነዳጅ ላኪ አገራትን ያቀፈ ነው። እነዚህ አገሮች በየጊዜው እየተገናኙ ምን ያህል ድፍድፍ ነዳጅ ለገበያ እናቅርብ እያሉ ይነጋገራሉ።

የኦፔክ ስብስብ ዋና አስኳል ተደርገው የሚታዩት ግን 13 የመካከለኛው እና የአፍሪካ አገራት ብቻ ናቸው።

ኦፔክ የተመሠረተው እንደ አውሮፓውያኑ 1960 ነበር። ዓላማውም የነዳጅ ምርት መጠን እና ዋጋን መተመን ነው።

በአሁኑ ወቅት የኦፔክ አገራት በድምሩ የዓለምን 30 ከመቶ የድፍድፍ ነዳጅ ምርት ያመርታሉ።

ከእነዚህ ውስጥ ሳዑዲን የሚያክል የለም። በቀን 10 ሚሊዮን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ብቻዋን ታቀርባለች።

እነዚህ 13 የኦፔክ አባል አገራት 10 ተጨማሪ አባላት አብረዋቸው እንዲሠሩ ያደረጉት በፈረንጆቹ 2016 ነበር።

ይህን የሆነው በዚያ ዓመት የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉን ተከትሎ ነበር።

ከዚያ ወዲህ ነው ኦፔክ የመደመር ምልክት በጨመር ኦፔክ+ ተብሎ መጠራት የጀመረው።

ከተደማሪ 10 አገራት መካከል ዋናዋ ሩሲያ ናት። ሩሲያ በቀን 10 ሚሊዮን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ታመርታለች።

የኦፔክ አስኳል እና አሥሩ ተደማሪ አገራት ተጨምረው በጥቅሉ የዓለምን የድፍድፍ ነዳጅ ምርት 40 ከመቶ ይሸፍናሉ።

እነዚህ 23 አገራት ዋጋ ላይ የሚጫወቱት ምርትን በመጨመር እና በመቀነስ ነው።

የዓለም የነዳጅ ዋጋ እንዲቀንስ ባሻቸው ጊዜ ምርታቸውን ይጨምራሉ።

የነዳጅ መቅጃ እና ገንዘብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኦፔክ+ አገራት ለምን ምርት ይቀንሳሉ?

ከሰሞኑ አገራቱ በቀን 1.16 ሚሊዮን በርሜል ምርት ለመቀነስ ተስማምተው ይህን ተፈጻሚ እያደረጉ ነው ያሉት።

ባለፈው ጥቅምት ወር በቀን 2 ሚሊዮን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ ዘይት ምርት መቀነሳቸው አይረሳም።

ያን ጊዜ የምርት ቅነሳው በአንድ ጊዜ የ5 በመቶ የዋጋ ጭማሪ አስከትሎ ነበር። የአሁኑ ደግሞ 7 በመቶ የዋጋ ጭማሪ አምጥቷል።

አሁን ጥያቄው ለምን ምርት መቀነስ ፈለጉ የሚለው ነው።

ምክንያቱም ሳዑዲ ምርቴ እስከ ዓመቱ መጨረሻ በያዘው መጠን ይቀጥላል ብላ ቃል ገብታ ነበር።

ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ ምናልባት አገራቱ በቀጣይ ጊዜያት የዓለም የነዳጅ ፍላጎት ባለበት አይቀጥልም ብለው ስለተነበዩ ይሆናል ምርት ለመቀነስ የተስማሙት ብለው ይገምታሉ።

ከሦስት ዓመት በፊት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ተከትሎ ይህ ቡድን በቀን 9 ሚሊዮን በርሜል የነዳጅ ምርት ቀንሶ ነበር።

ለዚህም ምክንያቱ አገራት በራቸውን ሲዘጉና የጉዞ ክልከላዎች ሲደረጉ ነዳጅ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ ዋጋው ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ አሽቆልቁሎ ነበር።

ሩሲያ ዩክሬን ላይ የከፍተችው ጦርነትን ተከትሎ በድጋሚ የነዳጅ ዋጋ ናረ። በበርሜል አስከ 130 ዶላር ድረስ አሻቀበ።

ይሁንና ባለፈው መጋቢት በተደረገ ፖለቲካዊ ንግግር ዋጋው መረጋጋት አሳይቶ በ15 ወራት ውስጥ ዝቅተኛ የሚባል ተመን ላይ ደረሰ።

ይህም በበርሜል 70 ዶላር እንዲሆን አስችሎ ቆይቷል።

አሁን ደግሞ ምርት እንቀንስ በማለታቸው ዋጋው ወደ 85 ዶላር ተመንድጓል።

ሩሲያ በርካሽ ዋጋ ለቻይና እና ሕንድ ነው ነዳጅ እየሸጠች ያለችው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሩሲያ በርካሽ ዋጋ ለቻይና እና ሕንድ ነው ነዳጅ እየሸጠች ያለችው።

ከሩሲያ ነዳጅ የሚገዛው ማን ነው?

ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችውን ወረራ ተከትሎ ማዕቀቦች ተጥለውባታል። የአውሮፓ አገራት በባሕር የሚጓጓዘውን የሩሲያን ነዳጅ ሙሉ በሙሉ መግዛት አቁመዋል።

አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም የሩሲያ ነዳጅ በአንፍንጫችን ይውጣ ካሉ ሰነባብተዋል።

ታዲያ ለማን ነው የምትሸጠው?

ሩሲያ አሁን ምርቷን በብዛት እየሸጠች ያለችው ለሕንድ እና ቻይና ነው። ሁለቱ አገራት በሞስኮ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ አልተቀላቀሉም።

ይሁንና የቡድን ሰባት ብልጹግ አገራት በሩሲያ ነዳጅ ላይ የዋጋ ዕቀባ በማድረጋቸው ዋጋው በበርሜል 60 ዶላር ብቻ ነው።

እነዚህ አገራት አብዛኛውን የኢንሹራንስ ኩባንያ፣ የዓለም አቀፍ ወደብ እና የመርከብ ትራንስፖርት የብድር ተቋማት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ስለሚዘውሩ ሩሲያ የገዛ ነዳጇን በስንት መሸጥ እንዳለባት የመወሰን ጉልበት አስገኝቶላቸዋል።

በዚህ የተነሳ የዓለም ቁጥር ሁለት ድፍድፍ ነዳጅ አምራቿ ሩሲያ ምርቷን ከ60 ዶላር በላይ በመሸጥ ትርፍ እንዳታገኝ ምዕራባውያን አገራት አሰናክለዋታል።

ከሰባቱ ብልጹግ አገራት በተጨማሪ የአውሮፓ ኅብረት እና ዩናይትድ ኪንግደም ይህን የዋጋ ማዕቀብ ይደግፉታል።

የሩሲያ ነዳጅ መሸጫ ዋጋ እስከ 70 ዶላር እንዲሆን ብልጹግ አገራት ሐሳብ አቅርበው የነበረ ሲሆን ፖላንድ፣ ሊቱዌኒያ እና ኢስቶኒያ ይህ ዋጋ ሩሲያን ሃብታም ያደርጋታል ብለው በመቃወማቸው ነው 60 ዶላር የተተመነው።