ነዳጅ አምራቾች ምርት ለመቀነስ ከተስማሙ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አሳየ

ነዳጅ ምርት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዓለማችን ከፍተኛ ነዳጅ አምራች አገራት ሳይጠበቅ የነዳጅ ምርትን ለመቀነስ ከተስማሙ በኋላ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ አሳየ።

በዚህም የብሬንት አንድ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ በ5 የአሜሪካ ዶላር ወይም በ7 በመቶ ጨማሪ አሳይቶ ከ85 ዶላር በላይ እየተሸጠ ነው።

የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው የመጣው ሳዑዲ አረቢያ፣ ኢራቅ እና ሌሎች በርካታ የባህረ ሰላጤው አገራት በቀን የአንድ ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ ምርት ቅነሳ እናደርጋለን ካሉ በኋላ ነው።

ቀድም ሲል ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ መክፈቷን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ ጨምሮ የነበረ ቢሆንም የነዳጅ ዋጋ ከጦርነቱ በፊት ወደነበረበት ተመልሶ ነበር።

አሜሪካ የነዳጅ ዋጋን ለማረጋገት አምራቾች ምርት እንዲጨምሩ ስትጠይቅ ቆይታለች።

ባለፉት ወራት የኢነርጂ እና የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ የዋጋ ግሽበት በመፍጠር በመላው ዓለም የኑሮ ውድነትን ፈጥሮ ነበር።

ነዳጅ አምራች አገራቱ የምርት ቅነሳ ማድረጋቸውን ካሳወቁ በኋላ የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ቃል አቀባይ፤ “የገበያ መረጋጋት በሌለበት በዚህ ወቅት የምርት ቅነሳ ማድረጉ የሚመከር አይደለም - ይህን ግልጽ አድርገናል” ብለዋል።

የምርት ቅነሳውን ያደረጉት ኦፔክ+ የሚባሉት ነዳጅ አምራች አገራት ሲሆኑ ለዓለም ገበያ ከሚቀርበው የነዳጅ መጠን 40 በመቶውን ይሸፍናሉ።

ሳዑዲ አረቢያ የቀን ምርቷን በ500ሺህ በርሜል የምትቀንስ ሲሆን ኢራቅ ደግሞ በ211ሺህ በርሜል የዕለት ምርቷን ትቀንሳለች። የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች፣ ኩዌት፣ አልጄሪያ እና ኦማን ሌሎች የምርት ቅነሳ የሚያደርጉ አገራት ናቸው።

የሳዑዲ የኢነርጂ ሚኒስቴር የነዳጅ ምርት ላይ ቅናሽ ማድረግ ያስፈለገው የነዳጅ ገበያ መረጋጋት ለመፍጥር የተወሰደ የቅድመ ጥናቃቄ እርምጃ ነው ስለማለቱ የሳዑዲ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ናታን ፓይፐር የተባሉ የዘርፉ ተንታኝ ግን ለቢቢሲ ሲናገሩ ነዳጅ አምራቾች ምርታቸውን የቀነሱት በዓለም ምጣኔ ሃብት መቀዛዝ ምክንያት የነዳጅ ዋጋ በበርሜል ከ80 ዶላር በታች እንዳይወርድ በማሰብ ነው ብለዋል።