ከአገራቸው ተሰውረው ኢትዮጵያ ውስጥ የተገኙት ኡጋንዳውያን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከሁለት ወር በፊት ነበር በመቶዎች የሚቆጠሩ ኡጋንዳውያን ንብረታቸውን ሸጠው መሰወራቸው የተሰማው እና ከሚኖሩበት አካባቢ ባሻገር በመላዋ ኡጋንዳ መነጋገሪያ የሆኑት።
እነዚህ ኡጋንዳውያን መነሻቸው በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል ከምትገኘው ሴሬሬ ወረዳ ሲሆን፣ ሁሉም በአካባቢው የሚገኝ የአንድ የክርስትና እምነት ቡድን አባላት እና በማኅበረሰብ ደረጃም የተሳሰሩ ናቸው።
የኡጋንዳ ምሥራቅ ኬዮጋ ፖሊስም መጀመሪያ ላይ ቢያንስ 100 ይሆናሉ የተባሉትን የደረሱበት ያልታወቁ የአካባቢዊ ምዕመናንን ጉዳይ በተመለከተ ምርመራ መጀመሩን ያሳወቀው በየካቲት ወር መጨረሻ ላይ ነበር።
እነዚህ መሰወራቸው የተነገረው ሰዎች ክራይስ ዲሲፕልስ ቸርች (ሲዲሲ) የተባለው ቤተ ክርስቲያን አባላት፣ ሴሬሬ ከተባለው ወረዳ ውስጥ ከሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች የተወጣጡ ሲሆን፣ ከመካከላቸውም በአካባቢው የመንግሥት ኃላፊነት ላይ የሚገኝ ግለሰብ ከነባለቤቱ እንደሚገኝ ተዘግቧል።
በድንገት ከአካባቢያቸው የተሰወሩት ኡጋንዳውያን ጉዳይ በአገሪቱ ውስጥ መነጋገሪያ ከመሆኑ ባሻገር፣ የት እንደደረሱ አለመታወቁ ደግሞ መነሻቸው በሆነው ምሥራቃዊ ኡጋንዳ ሴሬሬ አካባቢ ባሉነዋሪዎች ዘንድ ደኅንነታቸው አደጋ ላይ ወድቆ ሊሆን ይችላሉ የሚል ስጋት ተፈጥሮ ነበር።
የምጽአት ቀንን ሽሽት ወይስ ሃይኖታዊ ተልዕኮ
ከ250 በላይ ኡጋንዳውያን ያሉበት የእምነት ቡድን እንቅስቃሴ ጉዞ ወደ ኢትዮጵያ መደረጉ ከዚህ በፊት ተሰምቶ የማያውቅ ቢሆንም የአካባቢው ባለሥልጣናት ግን አዲስ ነገር እንዳልሆነ ይናገራሉ።
የኡጋንዳ መገናኛ ብዙኃን እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግሥት ግለሰቦቹ ጉዞውን ያደረጉት “የምጽአት ቀን ጥፋትን በመሸሽ ነው” ሲሉ የመጡበት እና የተቀበላቸው ማኅበረሰብ ግን “ለሃይማኖታዊ ተልዕኮ ነው” ይላሉ።
ጉዞው ሃይማኖታዊ ነው የሚሉት በደቡብ ኦሞ ዞን፣ የኛንጋቶም ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ ሎኪኛኒጋ ሙርሌ፣ ኡጋንዳውያኑ ህጻናት እና ሴቶችን የሚገኙበት 277 ናቸው። አሁን በቤተክርስቲያን የእንግዳ መቀበያ እና በግለሰቦች መኖሪያ አርፈው እንደሚገኙ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ኡጋንዳውያኑ የተነሱበት አካባቢ የጎሳዎች ማኅበር ቃል አቀባይ ለቢቢሲ የኡጋንዳ ዘጋቢ እንደተናገሩት፣ የተጓዦቹ ለቤተሰቦቻቸው ምንም ሳይናገሩ በመሰወራቸው ስጋት የፈጠረ ሲሆን እንዲሁም ንብረታቸውን ሸጠው ገንዘብ በመያዝ መጓዛቸው ደግሞ ፖሊስ የሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባ ሆነው ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ ነበረው።
የኡጋንዳውያን ምእመናን ጉዞ ወደ ኢትዮጵያ መደረጉ ከታወቀ በኋላ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ምንም ነገር ሳይባል ሳምንታት ተቆጥረዋል። በመጨረሻም ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ ዓለም ማረጋገጫ ሰጥተዋል።
በዚህም በመቶዎች የሚቆጠሩ ኡጋንዳውያን “የምጽአት ቀንን በመሸሽ” በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በኩል ወደ አገሪቱ መግባታቸውን ጠቅሰው፣ በአሁኑ ጊዜም ከኬንያ ጋር በሚዋሰነው ኛንጋቶም በሚባለው አካባቢ ይገኛሉ።
የኡጋንዳውያኑ ጉዞ “ከምጽአት ሽሽት አይደለም” የሚሉት አቶ ሎኪኛኒጋ፣ ከዚህ ቀደምም ከኬንያ ቱርካና፣ ከደቡብ ሱዳን እና ከኡጋንዳ አንድ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች መጥተው እንደነበር ይናገራሉ።
ጨምረውም “እነርሱ የመጡት በታሪክም ኛንጋቶም ማኅበረሰብ ከኡጋንዳ ነው የመጣው ብለው ስለሚያምኑ አካባቢውን ለማየት ነው” ብለዋል።

ፖሊስን ግራ ያጋባው ክስተት
የምሥራቅ ኬዮጋ የፖሊስ ቃል አቀባይ በወቅቱ አንዳሳወቁት የቤተ ክርስቲያኗ አባላት ከአካባቢው መሰወር የጀመሩት በየካቲት ወር ውስጥ ነበር።
የፖሊስ የመጀመሪያ ደረጃ የምርመራ ውጤት የቤተክርስቲያኗ አባላት የዓለም ፍጻሜ ጥፋት የሚጀምረው እነሱ ከሚኖሩበት አካባቢ እንደሚሆን በማመን፣ ስፍራውን ጥለው መሸሻቸውን የሚያመለክት መረጃ እንዳገኘ አመልክቷል።
እነዚህ የምሥራቅ ኡጋንዳ አካባቢ ነዋሪዎች እና የክራይስ ዲሲፕልስ ቸርች አባላት የእምነቱ መሪዎች በቅርቡ አካባቢው በሞት እንደሚመታ እና ሁሉም ነዋሪ እንደሚያልቅ ተነግሯቸው ነበር።
ይህንንም ተከትሎ ቀስ በቀስ ከአካባቢው የጠፉትን ሰዎች ደብዛ እና መድረሻ ለማወቅ ይረዳኛል በሚል ፖሊስ በተለይ የአካባቢው ቤተክርስቲያን መሪ የሆኑትን ቀሲስ ጄምስ ኤንያኩ እና አውጉስቲን ኦራጎ የተባሉትን ግለሰቦች ኢላማ በማድረግ ፍለጋ ሲያደርግ ቆይቷል።
ኋላ ላይ ደግሞ የቤተክርስቲያኗ መሪዎች ምዕመናኑ “ወደ ኢትዮጵያ ሄደው ወንጌልን እንዲያስፋፉ እግዚአብሔር ዕቅድ እንዳለው” በመግለጽ አሳምነዋቸዋል የሚል መረጃ ፖሊስ አግኝቷል።
ይህንንም ሃሳብ አብዛኞቹ ተቀብለውት ከአካባቢው መሰወራቸውን የፖሊስ ቃል አቀባይ ኦስካር አጌቻ ተናግረው፣ ነገር ግን በዚህ ሁኔታ ውስጥ ምን ያህል ኡጋንዳውያን ምዕመናን እንደተሳተፉ ለማወቅ ሲጥር ነበር።
ለዚህ ሃይማኖታዊ ነው ለተባለው ጉዞ እያንዳንዱ የጉዞው ተሳታፊ አባል ለሰነዶች ማዘጋጃ እና ለሌሎች ወጪዎች ሁለት ሚሊዮን የኡጋንዳ ሽልንግ (530 ዶላር ያህል) እንደሚያስፈልጋቸው መጠየቃቸውም ተነግሯል።
ይህንንም ገንዘብ ለማግኘት ተጓዥ ምዕመናኑ ከብቶቻቸውን፣ መሬታቸውን እና ሌሎች የቤት ውስጥ እቃቸውን ጨምሮ ንብረታቸውን አስከ መሸጥ እደደረሱ ፖሊስ አመልክቷል።
ቀደም ሲል የተደረጉ ጉዞዎች
ይህ በእንዲህ እንዳለ እነዚህ የደረሱበት አልታወቀም የተባሉት የክርስትና እምነት ምዕመናን የሚገኙበት አካባቢ ጎሳዎች የባህል የጋራ ማኅበር የሆነው ኢቴሶ ካልቸራል ዩኒየን ከ270 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ መሄዳቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
የማኅበሩ ቃል አቀባይ ጋብርኤል ኦፖሎት እንዳሉት ተሰወሩ የተባሉት 273 ሰዎች ዝምድና እንዳላቸው ወደሚታመኑት የኢትዮጵያ እና የኬንያ ማኅበረሰቦች ለሰላም እና ለክርስቲያናዊ ተልዕኮ መጓዛቸውን አመልክተዋል።
በደቡብ ኦሞ ዞን፣ የኛንጋቶም ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ የሆኑት ሎኪኛኒጋ ሙርሌ በበኩላቸው፣ ኡጋንዳውያኑ ወደ ወረዳቸው የመጡት “ቦታውን ለማየት እና የቤተክርስቲያን መልዕክት ለማድረስ ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በኡጋንዳ የሚገኙት የማኅበረሰቡ ቃል አቀባይ ጋብርኤል ኦፖሎትም የከብቶች ዝርፊያ እና ግድያን በጎሳዎች መካከል ለማስቀረት ተመሳሳይ በማኅበረሰብ መሪዎች መካከል ከዚህ ቀደም መደረጉን፣ ለዚህም “የባህል ልውውጥ የክርስትና እምነትን የማስፋፋት” ስብሰባዎች በኢትዮጵያ ውስጥ መደረጉን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ቃል አቀባዩ ጨምረውም ይህ ጉዞ በኡጋንዳ፣ በኬንያ፣ በደቡብ ሱዳን እና በኢትዮጵያ ባሉ እና የጎሳ ዝምድና ባላቸው ማኅበረሰቦች መካከል የከብት መዘራረፍን ለማስቆም የሚደረግ የሰላም ጥረት አካል ነው ብለዋል።
የምጽአት ቀን ስጋት እና ሕገወጥ ጉዞ
ኡጋንዳውያኑ በመቶዎች ኪሎ ሜትር የሚቆጠር ርቀትን ከማቋረጣቸው ባሻገር ከአገራቸው ጋር ወደ ማትዋሰነው ኢትዮጵያ ለመድረስ በኬንያ ወይም በደቡብ ሱዳን በኩል መሻገር ይጠበቅባቸዋል። ነገር ግን በየትኛው ድንበር በኩል በማቋረጥ አሁን ወዳሉበት የኛንጋቶም አካባቢ እንደደረሱ አልታወቀም።
በአንድ በኩል ኡጋንዳውያኑ የእምነት ቡድን አባላት ወደ ኢትዮጵያ ያደረጉት ጉዞ ለሃይማኖታዊ ተልዕኮ እንደሆነ ሲገልጽ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከአካባቢያቸው ይጀምራል ከተባለው የምጽአት ቀንን ሽሽት እንደሆነ እየተነገረ ነው።
የኛንጋቶም ወረዳ አስተዳዳሪ እና የምሥራቅ ኡጋንዳ ጎሳዎች ማኅበር ተወካይ ጉዞው ለሃይማኖታዊ አገልግሎት የታለመ ነው ቢሉም፣ ምእመናኑ ኢትዮጵያ ከደረሱ በኋላ በአካባቢያቸው ያለውን ሁኔታ ለማወቅ ጥረት እያደረጉ መሆኑ ተነግሯል።
ሞኒተር የተባለው የኡጋንዳ ጋዜጣ እንደዘገበው የቤተክርስቲያኗ መሪዎች ነግረዋቸዋል እንደተባለው ወደ ኢትዮጵያ የደረሱት አባላት በአገራቸው ካሉት ዘመዶቻቸው ጋር በመገናኘት የምጽአት ቀን መከሰት አለመከሰቱን እያጣሩ ነው ብሏል።
እነዚህ ኡጋንዳውያን የኢትዮጵያ መንግሥት በማያውቀው ሁኔታ በሕገወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ ግዛት የገቡ ሲሆን፣ በቀጣይ በምን አይነት መልኩ ጉዳያቸውን እንደሚመይዘው የታወቀ ነገር የለም።
በደቡብ ኦሞ ዞን፣ የኛንጋቶም ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ የሆኑት ሎኪኛኒጋ ሙርሌ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ኡጋንዳውያኑ ወደ አካባቢው መግባታቸውን ተከትሎ የፌደራል መንግሥቱ የደኅንነት ባለሥልጣናት ከስፍራው ዝርዝር መረጃዎችን አሰባስበዋል።












