በፓስተሮቻቸው ጸሎት ተአምራትን ለማግኘት ዕዳ ውስጥ የሚዘፈቁ ምዕመናን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
- ፀሐፊ, በሊቦ ዲሴኮ
- የሥራ ድርሻ, የሃይማኖት ጉዳዮች ዘጋቢ
“ከሐሰተኛ ነብያን ተጠንቀቁ” እንደሚለው መጽሃፉ፣ በኬንያ በርካቶች ፓስተሮች እንዲጸልዩላቸው ለመጠየቅ ዕዳ ውስጥ መዘፈቃቸው ተነግሯል።
ኤቫርሊን ኦኬሎ አንድ ፓስተር እንዲጸልይላት ለመክፈል ዕዳ ውስጥ ገብታለች።
በመቶዎች የሚቆጠር ዶላር ዕዳ እንዳለባት ስትናገር እያነባች ነው።
ነዋሪነቷ በኬንያዋ መዲና ናይሮቢ፣ ዋነኛው የድሆች መኖሪያ መንደር ኪቤራ ነው።
ኤቫርሊን በአሁኑ ወቅት አራት ልጆቿን መመገብ ተስኗታል።
ለወራት ያህል ምንም ገንዘብ እንደሌላት ለቢቢሲ ተናግራለች።
በአንድ ወቅት ነው ጸሎቱ ሕይወት ስለሚያሻሽለው ፓስተር የሰማችው።
አገኘችው፣ ፓስተሩም 15 ሺህ የኬንያ ሽልንግ (115 ዶላር) እንድታመጣ ጠየቃት።
ይህ የገንዘብ ስጦታ “የዘር መስዋዕት” በመባል ይታወቃል።
ተዓምር ለሚያደርጉ የሃይማኖት መሪዎች የሚበረከት የገንዘብ መዋጮ ነው።
ኤቫርሊን ገንዘቡን ከጓደኛዋ ተበደረች።
ጓደኛዋም ለእሷ ስትል ብድር ወስዳ ነው የሰጠቻት።
የዚህ ፓስተር ጸሎት በጣም ኃይለኛም ስለሆነ በሳምንት ውስጥ ገንዘቧ እንደሚመለስም ተነግሯታል።
የተባለው ተአምር አልደረሰም። እንዲያውም ይባስ ብሎ ጓደኛዋ የተበደረችውን ገንዘብ በጊዜ ባለመክፈሏ ወለዱ ጨመረ።
በአሁኑ ወቅት ኤቫርሊን ከ300 ዶላር በላይ ብድር አለባት። እንዴት እንደምትከፍለው ግን አታውቅም።
ጓደኛዋም አታናግራትም፤ ሥራም የላትም።
“በጣም ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ስለሆንኩ ሙሉ በሙሉ ተስፋ ቆርጫለሁ” ትላለች።

‘ተአምራዊ መፍትሄዎች’
ኬንያ በዋጋ ግሽበት ክፉኛ ተመትታለች።
የምግብ ዋጋ በአስራ ሁለት ወራት ውስጥ 16 በመቶ እንደጨመረ የኬንያ ብሔራዊ የስታቲስቲክስ ቢሮ መረጃ ያሳያል።
የዓለም ባንክ አሃዝ በበኩሉ ሥራ የሌላቸው ኬንያውያን ቁጥር ባለፉት ሰባት ዓመታት ከእጥፍ በላይ መጨመሩን አመልክቷል።
“በርካቶች ተስፋ በቆረጠ ሁኔታ ኑሯቸውን እየገፉ ነው” ሲሉም በኬንያ የመልቲሚዲያ ዩኒቨርሲቲ የሶሺዮሎጂ መምህር የሆኑት ዶክተር ግላዲስ ኒያቺዮ ይናገራሉ።
በፈተና ውስጥ እየኖሩ ያሉ ሰዎች ለችግራቸው መፍትሄ ያሉት ተዓምር እንደሆነም ዶክተሯ ይናገራሉ።
ይህ ተዓምር በሕይወታቸው እንዲገለጽ ተበድረውም ቢሆን ለመክፈል የፈቀዱ በርካቶች ናቸው።
“አምላክ በድህነት እንዲቆዩ እንዳማይፈልግ ይነገራቸዋል። ስለዚህ ዘርም እንዲዘሩ ይጠየቃሉ” ይላሉ።
ትምህርቱ የፕሮስፐሪቲ ወንጌል (የብልጽግና ወንጌል) ከሚባለው የተቀዳ ነው።
በፕሮስፐሪቲ አስተምህሮ መሠረት እምነት ያላቸውን ሰዎች አምላክ በሃብት እና በጤና ይባርካቸዋል የሚል ነው። ምዕመናንም ዕምነታቸውን ለማሳየት ገንዘብ እንዲሰጡ ይበረታታሉ።
አምላክም በእጥፍ፣ ድርብ መልሶ ይከፍላችኋልም ይባላሉ።
የዚህ ወንጌል መሠረቱ አሜሪካ ነው። ከፍተኛ መነቃቃትም የታየው በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ ነው።
በ1970ዎቹ መጨረሻ እና በ1980ዎቹ ናይጄሪያውያን ፓስተሮች ስለ አስተምህሮቱ የበለጠ ለመረዳት ወደ አሜሪካ ያቀኑ ነበር።
ይህ አስተምህሮም ከሁለት እና ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት በአፍሪካ ውስጥ መሰራጨት ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ እውቅና እያገኘ መጣ።
ለዚህም ተሰሚነት ያላቸው እንደ ሬይንሃርድ ቦንኬ ያሉ አሜሪካውያን ወንጌላውያን ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።
በዚያን ወቅት የጀመረውም ታዋቂነት ተጽእኖው እየጨመረ ዛሬም ድረስ ቀጥሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዶክተር ግላዲስ ኬንያውያንን ለዕዳ የሚፈታተነው ሌላኛው ጉዳይ በሞባይል ስልኮች ላይ የሚላኩ በርካታ የብድር አቅርቦቶች ማስተዋቂያዎች ናቸው። “ሰዎች ዝም ብለው ለብድር ሲያመለክቱ ወዲያውኑ ገንዘቡን ያገኛሉ” ይላሉ።
የ26 ዓመቱ ዴኒስ ኦፒሊ ለሦስት ዓመት ያህል እግሩ እስኪቀጥን ኳትኖ ሥራ ፈለገ።
ሥራ ሊያገኝ ባለመቻሉም ጓደኛውን እርዳታ ጠየቀ።
“የሚጸለይበት ቤተ ክርስቲያን እንድሄድ መከረኝ። መባ ከሰጠህ በኋላ ይጸልዩልሃል ከዚያም ሥራ ማግኘት ትችላለች” ሲል እንደመከረው ዴኒስ ይናገራል።
በየሳምንቱ እሁድ ለሦስት ወራት ያህል መዋጮ እንዲሰጥ ተነግሮት በድምሩ 180 ዶላር አካባቢ ሰጥቷል።
የነበረችው ቁጠባ ካለቀች በኋላ ገንዘብ ከሚያበድሩ መተግበሪያዎች እና ከጓደኞቹ 120 ዶላር ተበደረ።
“ፓስተሩ ሥራ ታገኛለህ ያለኝን አምኘው ነበር፤ ስለዚህ ስበደር በመጨረሻ ገንዘቡን መክፈል እንደምችል አስቤ ነበር” ይላል።
ነገር ግን ምንም ሥራ ሳያገኝ ሲቀር ዴኒስ እንደተታለለ መጠርጠር ጀመረ።
ብዙም ሳይቆይ ያበደሩት አነስተኛ ብርድር አቅራቢ ድርጅቶች ዕዳውን እንዲመልስ ያሳድዱት ጀመር።
“አንዳንድ ጊዜ የሆነ ቦታ ተቀምጨ እየተዝናናሁ፣ ስለሌላ ነገር እያሰብኩ ይደወልልኛል። የተበደርከውን ገንዘብ መልስ ይሉኛል። የምከፍላቸው ምንም ነገር አልነበረኝም” ይላል።
“ብድሩን ካልመለስኩ ምን ዓይነት እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ ስላማላውቅ መፍራት ጀመርኩ። መከሰስ ነው? ወይስ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋል? ምን እንደሆነ አላውቅም” ይላል።
እንደ ዕድል ሆኖ ዴኒስ በሰዓት የሚከፈልበት ሥራ ለማግኘት ችሏል።
በዚህም ላበደሩት ድርጅቶች እና ለጓደኞቹ የተበደረውን መልሶ ለመክፈል ቻለ።
“አሁንም በአምላክ አምናለሁ። ለወደፊቱ ማድረግ ያለብኝ ከእንደዚህ አይነቶች መጠንቀቅ ብቻ ነው” ብሏል።

ገንዘብ እንዲሰጡ የሚደረግ ጫና
በኬንያ ብቻ አይደለም አማኞች ተዓምርን ተስፋ አድርገው በዕዳ የሚዘፈቁት። በአሜሪካ የናይጄሪያ ቤተ ክርስቲያን ምዕመን የሆነች ግለሰብ እና ባለቤቷ ለቤተ ክርስቲያኗ መባ ስጡ በሚል ከፍተኛ የገንዘብ ቀውስ ውስጥ ገብተው እንደነበር ተናግራለች።
በቤተ ክርስቲያኒቱ ወይም በጠበቆቿ ሊደርስባት የሚችለውን አደጋ በመፍራትም ስሟን እንዳንጠቀም የነገረችንን ግለሰብ ሳራ ብለን እንጠራታለን።
ሳራ ታመልክበት በነበረው ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን እና ፓስተሮች ከወርሃዊ ገቢያቸው አስር በመቶ “አስራት” በናይጄሪያ ለሚገኙ ቤተክርስቲያን እና አመራሮች መስጠት ይጠበቅባቸው ነበር። ይህም “የመጀመሪያ ፍሬ” ተብሎ ከሚጠራው ለቤተ ክርስቲያን ከሚሰጠው በተጨማሪ ነበር።
የአካባቢው አመራሮች በየወሩ ምን ያህል መዋጣት እንዳለበት ይወስናሉ። ምዕመኑም ያ ገንዘብ እስኪሞላ ድረስ እንዲያዋጡ ጫና ይደረግባቸዋል። በዚህም የናይጄሪያ ዋና ፓስተር ይባርካችኋል ይባላሉ።
“የዘር ገንዘብ” ተብሎ የሚጠራውንም ለመክፈል ክሬዲት ካርዳቸውንም የሚጠቀሙ ሰዎች እንደነበሩ ትናገራለች።
“በአንድ ወቅት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንዲት ሴት አስራት እየከፈልኩ ነው እናም ለወሩ መጨረሻ የሚያደርሰኝ በቂ ገንዘብ የለኝም፤ ስትል ሰማኋት” ትላለች።
እናም ሳራ እንደምትለው ፓስተሩ በምላሹ ለቤተ ክርስቲያን መስጠት ከቤት ኪራይ መክፈል የበለጠ እንደሆነም ለምዕመናኑ ይናገር ነበር።
እናም ለምን ተዓምራትን እንደማያዩ ለሚጠይቁም “በበቂ አልጸለያችሁም። በቂ ዘር አልዘራችሁም [አልከፈላችሁም]፤ በቂ እምነት የላችሁም” ተብሎ ይነገራቸው እንደነበር ታስታውሳለች።
መጨረሻ ላይም ሳራ እና ባለቤቷ ከቤተ ክርስቲያኗ ራሳቸውን አገለሉ።
የመጨረሻው ተስፋ
ገንዘብ እንዲከፍሉ እንዲህ ጫና በሚደርስባቸው ሁኔታ ሌሎች ለምን የእነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ምዕመን ይሆናሉ?
በኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የዓለም ክርስትያኖች ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ዮርግ ሃውስተይን፣ ምዕመናኑ ቃል እንደተገባላቸው ተስፋዎቹ ባይፈጸሙም ገንዘብ መስጠት የሚቀጥሉበት ምክንያት አለ ይላሉ።
ወደ ሃብታሙ መደብ መግባት ለሚፈልጉት በመካከለኛው መደብ ያሉ እንደ ሳራ ያሉ ምዕመናን የፕሮስፐሪቲ ወንጌል “ኢኮኖሚያዊ ስኬት እና ሃብታም መሆን እንደሚችሉ” ስለሚያሳያቸው ይማርካቸዋል።
ለመካከለኛው መደብ ብቻ ሳይሆን፣ በድህነት ለሚማቅቁም አስተምህሮው ሊያጓጓ ይችላል ሲሉ ይናገራሉ።
“በመከራ ላይ እንደሆናችሁ እናውቃለን። ይህንንም መከራችሁን የሚቃልል መፍትሄ አለን፤ የሚል ቤተ ክርስቲያን ስለማይታይ ዓለም ወይም ለውጥ ከሚሰብክ በበለጠ የሚያጋጓ ይሆናል” ይላሉ።
ነገር ግን ሰዎች ገንዘብ በሌላቸው ሁኔታ በዕዳ ተዘፍቀው እንዴት ይከፍላሉ? ዶክተር ዮርግን ጠየቅናቸው።
“በቀላሉ ስልካቸውን ተጠቅመው መበደርም ስለሚችሉ መክፈል እንደሚችሉ ይሰማቸዋል” የሚሉት ዶክተር ዮርግ “በእርግጥም ከዚህ ጀርባ ተስፋ የመቁረጥ መንፈስም አለ። ምናልባትም ይህ የመጨረሻ ተስፋችን ነው ሊሉም ይችላሉ” ይላሉ።
ኤቫርሊን በደረሰባት ችግር ምክንያት እምነቷን አልተወችውም።
“ቤተ ክርስቲያን መጥፎ ነው አልልም፣ ቤተ ክርስቲያን ጥሩ ነች፣ አሳሳቾቹ ፓስተሮች ናቸው። ገንዘብ የሚጠይቁት እነሱ ናቸው” በማለት ታስረዳለች።












