ናይጄሪያዊው ፓስተር "ወደ መንግሥተ ሰማያት" ለመውሰድ 700 ዶላር እያስከፈሉ ነው በሚል ተከሰሱ

ፓስተር አዴ አብራሃም
የምስሉ መግለጫ, ፓስተር አዴ አብራሃም

ናይጄሪያዊው ኢቫንጀሊካን ፓስተር ተከታዮቻቸው ገንዘብ ከከፈሉ ወደ መንግሥተ ሰማያት ወደሚያደርሳቸው በር እንደሚመሯቸው ከተናገሩ በኋላ ችግር ገጥሟቸዋል።

በደቡብ ምዕራብ ናይጄሪያ ውስጥ የሚገኙት ፓስተር አዴ አብራሃም ለዚሁ ሲባል 750 ዶላር አስከፍለውኛል ያለ አንድ ግለሰብ ለፖሊስ ከከሰሳቸው በኋላ ጉዳዩ መነጋገሪያ ሆኗል።

ፓስተሩ ወደ መንግሥተ ሰማያት ስለሚያደርሰው በር መናገራቸውን ለቢቢሲ ያረጋገጡ ሲሆን፣ የቤተክሪስቲያናቸውን አባላት እምነት ለመፈተን "የማገለግለው"ያሉት ፈጣሪ የገለጠላቸው መሆኑን ገልጸዋል።

ነገር ግን የመንግሥተ ሰማያት መግቢያ በርን ለማሳየት በሚል ምንም አይነት የገንዘብ ክፍያ አለመቀበላቸውን ተናግረዋል።

ይህንን ተከትሎ የናይጄሪያ አብያተ ክርስቲያናት ማኅበር የፓስተር አዴ አብረሃምን እውቅና ያነሳ ሲሆን፣ ያሉበር ኤኪቲ ግዛት ፖሊስ ደግም ምርመራ ለማካሄድ ከቤተክርስቲያናቸው አባላት የጽሁፍ ማስረጃዎችን እያሰባሰበ መሆኑ ተነግሯል።

የፓስተሩ ቤተክርስቲያ ከአባላቱ ጋር አሁን ወዳለበት በኤኪቲ ግዛት ማዕከሉን አቋቁሞ ከመዘዋወሩ በፊት ኮጊ እና ካዱና በሚባሉ ግዛቶች ውስጥ የነበረ ነው።

ፓስተሩ ፈጽመዋል ያሉትን ድርጊት ለፖሊስ ያመለከተው የቤተክርስቲያኑ አባል ወደመጣበት የካዱና ግዛት የተመለሰ ሲሆን፣ ሚስቱ ግን በቅርቡ የሚያስደስት ታላቅ ነገር ይከሰታል በሚል ተለይታው ባለችበት ቀርታለች ተብሏል።

ነገር ግን ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱት ባልና ሚስት በየዕለቱ በስልክ እንደሚነጋገሩ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ኖህ አብረሃም በሚል ተጨማሪ ስም የሚታወቁት ፓስተር አዴ፣ በቅርቡ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት በተሰራጨ ቪዲዮ ላይ ምዕመናን በውጪ አገራት ያሉ ዘመዶቻቸው ለቤተክርስቲያናቸው ገንዘብ እንዲልኩ ሲጠይቁ ያሳያል።

በፓስተሩ ላይ የመንግሥተ ሰማያትን በር እመራለሁ በሚል ገንዘብ እየተቀበሉ ነው የሚለው ክስ የደረሰው የናይጄሪያ ፖሊስ መረጃዎችን እያሰባሰበ ሲሆን፣ ምርመራውን መሰረት አድርጎ የሚወስደው እርምጃ እየተጠበቀ ነው።