የሰባኪው ቲቢ ጆሽዋ ሚስት የ'ነብይ' የባለቤቷን ዝና አስጠብቃ ትቀጥል ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, AFP
በሙሉ ስማቸው ቴምቲዮፔ ባሎጉን ጆሽዋ ተብለው ይጠራሉ። ሚሊዮኖች የሚያውቋቸው ግን ቲቢ ጆሽዋ በሚለው ስም ነው። ሥመ ጥር ናይጄሪያዊ የሐይማኖት ሰባኪ ነበሩ።
የጆሽዋ ተከታዮች፣ ሰውየው እጅግ በርካታ መንፈሳዊ ተዓምራትን አሳክተዋል ብለው ያምናሉ።
ለዓይነ ስውራን ብርሃናቸውን መልሰዋል፣ አካል ጉዳተኞችን ቀጥ ብለው እንዲራመዱ አድርገዋል፤ ካንሰርና ኤችኤቪን ፈውሰዋል ብለውም ያምናሉ።
በርካታ ርዕሳነ ብሔራት ሳይቀሩ የቲቢ ጆሽዋ ቤተ ክርስቲያን ታማኝ ምዕመናን ነበሩ።
ፎርብስ መጽሔት ከ12 ዓመታት በፊት ባወጣው አንድ መረጃ ሰባኪ ጆሽዋ የሀብት መጠናቸው 15 ሚሊዮን ዶላር ይደርሳል ብሎ ነበር።
ይህ አሐዝ በዓመታት ውስጥ በብዙ እጥፍ እንደጨመረ ግን ጥርጥር የለውም።
'ነብይ' ጆሽዋ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1963 ላይ ነበር የተወለዱት። ዝቅተኛ ገቢ ካለው ቤተሰብ እንደተገኙ ይነገራል።
በእናታቸው ማህጸን ውስጥ ለ15 ወራት ስለመቆየታቸውም ተናግረው ያውቃሉ።
በተወለዱ በ57 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ በናይጄሪያና በብዙ የአፍሪካ አገራት ትልቅ ድንጋጤን ፈጥሮ ነበር።
ባለቤታቸው ጆሽዋን ልትተካ ትችላለች?
ራሳቸውን 'የእግዚአብሔር ሰው' ብለው የሚጠሩት ሰባኪ ጆሽዋ፣ ቲቢ ጆሽዋ ዘ ሲናጎግ፣ ቸርች ኦፍ ኦል ኔሽንስ (የሁሉም ሕዝቦች ቤተ ከርስቲያን) የተባለ ግዙፍ ማምለኪያ ማዕከል መሥርተዋል።
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሳምንታዊ የአገልግሎት ሥነ ሥርዓታቸው ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ።
ይህ በሌጎስ የሚገኘው ማምለኪያ ቤተ-ክርስቲያን በሌጎሳዊያን ብቻ የሚዘወተር አይደለም። ብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጠው የሚመጡ በሺህ የሚቆጠሩ ምዕመናንም አሉ።
አሁን አሁን ግን ይህ እየቀነሰ መጥቷል።
ቤተ ክርስቲያኑን ማን ይውረስ የሚለው ትልቁ መነጋገሪያ ሆነ።

የፎቶው ባለመብት, SCOAN
ኤቨሊን ጆሽዋ የሟቹ ነብይ ባለቤት ናት። የ52 ዓመቷ ኤቨሊን በብዙ ፈተናዎች አልፋ ይህን ቤተ ክርስቲያን እንድትመራ ተመርጣለች። ተቀባይነቷ ግን እንደ ሟች ባለቤቷ ቲቢ ጆሽዋ ሊሆን አልቻለም።
ባለፈው ሰኔ የ'ነብይ' ቲቢ ጆሽዋ ሞት ድንገተኛ ነበር። ተተኪው ማን ይሁን የሚለው እሰጥ አገባ የተከሰተው ግን በማግስቱ ነበር።
በዚህ የተነሳ ላለፉት አምስት ወራት የጆሽዋ ዝነኛ ቤተ ክርስቲያን ተዘግቶ ነበር የቆየው። አሁን ግን ለመጀመርያ ጊዜ በሩን ክፍት አድርጓል።
ቲቢ ጆሽዋን ማን ይተካቸው የሚለው ትንቅንቅ አምስት ወራትን የወሰደ ነበር።
እንደ ጆሽዋ ያለ ተአምር መሥራት የሚችል፣ ሺዎችን መፈወስ የሚችል፣ ከላቲን አሜሪካና ከአፍሪካ ታላላቅ መሪዎችን ወደ ሌጎስ ማጉረፍ የሚችል ሰው ፍለጋ ብዙ ተካሂዷል።
የጆሽዋ ባለቤት ግን ትክክለኛዋና ሕጋዊዋ ተተኪ እኔ ነኝ ስትል ቆይታለች።
በተለምዶ በእንዲህ ያሉ ሰባኪያን ሞት፣ የሟች ባለቤት ቦታውን መያዝ በናይጄሪያ የተለመደ ነው። ነገር ግን ጆሽዋ ከመሞታቸው በፊት ይህን በግልጽ ስላላመለከቱ ነው ትኩስ ተቃውሞ ሊመጣ የቻለው።
እርግጥ ነው፣ ጆሽዋ በሕይወት በነበሩ ጊዜ ደቀ መዛሙርት ነበሯቸው። ከእርሳቸው ጋር በቅርብ የሚሠሩ እነዚህ ሰዎች 'የብልህ ምዕመናን ጉባኤ' የሚል ስም ነበራቸው።
ከነዚህ ውስጥ አንዱ ጆሽዋ ተተኪያቸውን ሊያደርጉት እየመለመሉት ነበር ተብሎ ይታመናል።
የባለቤቷን ጆሽዋን ሞት ተከትሎ የባለቤታቸው ታማኞች ፈጥነው ወደ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ወሰዱት።
ባለቤታቸውንም የዚህ 'የብልህ ምዕመናን ጉባኤ' አባል እንደነበሩና የቦርድ አባልም እንደሆኑ ፍርድ ቤቱን ማሳመን ቻሉ። ይህም ለተተኪነታቸው ሕጋዊነትን የሚሰጥና መንገድ የጠረገ ሆነ።
ይህን ተከትሎም ቤተ ክርስቲያኒቱ ኤቨሊን አዲሷ መሪ እንደሆነች ይፋ አደረገ።
ይህም 'ጌታ በሰጠው አቅጣጫ' የጸደቀ መሆኑ ተበሰረ።
ይህ ግን አንዳንድ የቤተ ክርስቲያኒቱን የበላይ ጠባቂዎች አላስደሰተም።
አንዱ ቅሬታቸው የተተኪነት ሽግግሩ ግልጽነት የጎደለው መሆኑ ነው።
ኤቨሊን ባለቤቷ መሞቱን ተከትሎ ወዲያውኑ ተቃዋሚ ሊሆኑ የሚችሉት ሰዎችን ማባረር እንደጀመረች ዘገባዎች ወጥተዋል።
በተለይም የውጭ ዜጎች የነበሩና በቤተ ክርስቲያኒቱ ቅጥር ይኖሩ የነበሩ ምዕመናን ወዲያውኑ ሻንጣቸውን ሸክፈው እንዲለቁ ነበር በኤቨሊን የተነገራቸው።
ይህም በእሷ 'መቀባት' ላይ ተቃውሞ ሊያስነሱ የሚችሉ ሰዎችን ለማጥራት የተደረገ እንደሆነ ተጽፏል።
ፓትሪክ ሊዌሉንሞር የጆሽዋ የቀድሞ የሚዲያ ጉዳዮች ልዩ አማካሪ ነው። ፓትሪክ ለቢቢሲ እንደሚለው ከሆነ የነብይ ጆሽዋን ሞት ተከትሎ ደቀ መዛሙርቱ ባለቤቱን ኤቨሊንን በሚገባት ክብር አላስተናገዷትም።
ከዚህም ባሻገር ከፍተኛ የሙስና ተግባራት በቤተ ክርስቲያኒቱ ሀብት ላይ መፈጸሙ የናይጄሪያ የጸረ ሙስና ኤጀንሲ ገልጧል።
አንዳንዶች እንደሚያምኑት የነብይ ጆሽዋን ሞት ተከትሎ ለእርሳቸው ቅርብ የነበሩ ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው ምዕመናን ሚሊዮን ዶላሮችን ማሸሽ ጀምረዋል።
የናይጄሪያ ጋዜጦች ከፍተኛ ገንዘብ ያሸሹ የነብይ ጆሽዋ ባለሟሎች ለጊዜው ተሰውረዋል እያሉ እየጻፉ ነው።

የፎቶው ባለመብት, AFP
የጆሽዋ ባለቤት ቀጣይ ፈተና
አሁን ኤቨሊን ተወደደም ተጠላ መሪነቱን ተቆናጣለች።
ቀጣይ ፈተና የሚሆንባት ግን እሷ የተመረጠችው 'በፈጣሪ ቀጥተኛ ጥሪ' መሆኑን ለምዕመናኑ ማሳመን ነው።
በተለይ ሟች ባለቤቷን እጅግ አድርገው ይወዱ ለነበሩ ሚሊዮኖች እሷ 'የጌታ ምርጫ' ስለመሆኗ አሳማኝ ነገር ማሳየት አለባት።
እነዚህ ሚሊዮን ተከታዮች ወደ 'ነብይ' ጆሽዋ ይመጡ የነበሩት ይፈጽማቸው ለነበሩ ተአምራት ሲሉ ነው። ባለቤቱ ኤቨሊንም አንዳች ተአምር ልታሳያቸው ካልቻለች ቀጣዩ ጊዜ ቀላል አይሆንላትም ይላሉ ታዛቢዎች።
አንድ በሐይማኖት ጉዳይ ላይ የሚጽፍ የናይጄሪያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ስለሁኔታው ለቢቢሲ አስተያየቱን ሲሰጥ፣ "ኤቨሊን በሟቹ ባለቤቷም ሆነ በምዕመናን ዘንድ ዝቅ ተደርጋ የምትታይ ሰው ነበረች። ሆኖም ቤተ ክርስቲያኒቱን ቀጥ አድርጋ በመምራት አቅሟን ማሳየት ችላለች" ይላል።
እስከ አሁን እሷ የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ ጠባቂ አሁንም ሟቹ ባለቤቷ እንደሆነ ትናገራለች። "እኔ እሱ የጀመረውን ተአምራት ብቻ ነው እየቀጠልኩ ያለሁት" ትላለች።
በእርግጥም ነብይ ጆሽዋና ተጽእኗቸውን በቀላሉ መውረስ የሚቻል አልሆነም። አሁንም ቢሆን አብያተ ክርስቲያናት በእርሳቸው ምስሎች ያጌጡ ናቸው። ቴሌቪዥን ጣቢያዎቻቸውም የእርሳቸውን ስብከቶች ነው ደጋግመው የሚያስተላልፉት።
ኤቨሊን የሟቹን ባለቤቷን የስብከት ጥበብን ለመውረስ ሞክራለች። ለምሳሌ ከስብከት ወደ ዝማሬ የምትሸጋገርበት መንገድ፣ ልሳን የምትናገርበት መንገድ የባለቤቷን ስልት የያዘ ነው።
ይህ ግን ምን ያህል ሀቀኛ ተተኪ እንደሆነች የሚመሰክር ላይሆን ይችላል።
የጆሽዋና የኤቨሊን ፍቅር
ጆሽውና ኤቨሊን መጀመርያ የተዋወቁት በ1990 (እንደ አውሮፓውያኑ) ነበር።
ጆሽዋ ያን ጊዜ ወጣት ነበር። ስሟን ሳትነግረው በወረቀት ላይ ከመጻፉም ባሻገር ለማንም አልተናገርኩትም ነበር የምትለውን የሕይወቷን ምሥጢር ልቅም አድርጎ መልሶ ለራሷ በነገራት ጊዜ ተመሰጠችበት።
ያን ቀን ለ45 ደቂቃዎች ያህል አወሩ። ወዲያዉኑ ለጋብቻ ጠየቃት።
ኤቨሊን መንታ አለቻት። ያደገችው ከ7 ወንድምና እህቶቿ ጋር ነው። የመጣችውም ከደቡብ ምሥራቅ ናይጄሪያ ከዴልታ ግዛት ኦካላ ኦኩፑኖ ነው።
ምንም ዓይነት የፓስተርነት ልምድ አልነበራትም። በባሏ ጆሽዋ ግን የተወሰኑ ስልጠናዎችን አግኝታለች።
በ2009 ዓ.ም. "አምላክ በተለይም ቤተሰብንና ትዳርን በተመለከተ" የማስታረቅ ጸጋ እንደሰጣት ይፋ አደረገች።
በናይጄሪያ ስመ ጥር ሰባኪዎች ልክ እንደ ሐዋሪያው ጳውሎስ ከአምላክ ጥሪ እንደተደረገላቸው ይፋ ካደረጉ በኋላ ነው ወደ መንፈሳዊ ሥራ ጠቅልለው የሚገቡት።
ነብይ ጆሽዋም ያኔ ድሮ ተመሳሳይ ጥሪ ከሦስት ቀናት መመንጠቅ በኋላ እንደደረሰው ተናግሮ ነበር።
"እኔ አምላክህ ነኝ፤ መለኮታዊ ጸጋን አንተ ላይ አሳድሪያለሁ፤ ለኃያሉ እግዚአብሔር አገልግሎትህን ስጥ" የሚል ድምጽ ከሦስት ቀናቱ በመንፈስ የመሞላት ቆይታ በኋላ እንደመጣለት አብራርቶ ነበር።
ባለቤቱ ኤቨሊን ግን እስከ አሁን ይህ ዓይነት ጥሪ በቀጥታ እንደደረሳት ይፋ አላደረገችም።
ይሁንና በርካታ ምዕመናን፣ ይህ የቀጥታ መለኮታዊ ጥሪ ባይደርሳትም በሟች ባለቤቷ በኩል ተላልፎላታል ብለው ያምናሉ።
"ቲቢ ጆሽዋ ነብይ ሆኖ ነው የተወለደው። እሷ ደግሞ በእሱ ውስጥ ናት። ባልና ሚስት አንድ ናቸው። በዚህ ጥምረት መሠረት ኤቨሊን ነብይ ናት" ይላል ሉዌሉኑሞ።
እርግጥ ነው በናይጄሪያ ነብይነትን ከሟች ነብይ ባለቤቶቻቸው የወረሱ በርካታ ናቸው።
ለምሳሌ ጃኔት ኦናዎላፖ፣ ማርጋሬት ኢዳሆሳ ይጠቀሳሉ። ሆኖም እንደ ሟች ባለቤቶቻቸው ስኬታማ አልነበሩም።
ብዙዎቹ የናይጄሪያ ጴንጤ-ቆስጤ አብያተ ክርስቲያናት የተገነቡት በመሪዎቻቸው ሞገስና ዝና ነው።
እነሱ ሲሞቱ የአብያተ ክርስቲያናቱ ዝና አብሮ ይዳከማል።
የኤቨሊን ዕጣም ይኸው እንደሚሆን ይገመታል።
ሚስተር ኦሲናይኬ እንዲህ ይላል፡- "ሰዎች ቤተ ክርስቲያንን ሲያስቡ ተአምራትን ይሻሉ፣ ነገ ስለሚሆነው ማወቅን ይሻሉ፣ ትንቢትን መስማት ይሻሉ፣ ለእነሱ የሚመጥን ራእይ እንዳዩላቸው መስማትን ይሻሉ። የጆሽዋ ቤተ ክርስቲያን አሁን ይህን የሚያደርግለት ሰው የለውም፤ ስለዚህ ዝናው ማሽቆልቆሉ አይቀርም።"














