በአፍሪካ ታዋቂ የነበሩት የሐይማኖት ሰባኪው ቲቢ ጆሽዋ ማን ነበሩ?

ታዋቂው ናይጄሪያዊ የሃይማኖት ሰባኪ ቴምቲዮፔ ባሎጉን ጆሽዋ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ከናይጄሪያ ባሻገር በአፍሪካ ውስጥ ስመ ጥር የኢቫንጀሊካን ሐይማኖት ሰባኪው ቅዳሜ ዕለት ሐይማኖታዊ አገልግሎት አከናወነው ከጨረሱ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ማረፋቸው ተገልጿል።
ህልፈታቸውም ይፋ የተደረገው በእራሳቸው ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ ላይ "አምላክ አገልጋዩን ቲቢ ጆሹዋን ወደቤቱ ወስዷል" በሚል አጭር መልዕክት ነበር።

ቴምቲዮፔ ባሎጉን ጆሽዋ ወይም ቲቢ ጆሽዋ ተብለው የሚጠሩት የሐይማኖት ሰባኪ ብዙ ተዓምራትን እንደሰሩ ይናገራሉ። ለአይነ ስውራን ብርሃናቸውን ከመመለስ ጀምሮ ሰዎችን ከኤችአይቪ አስከ መፈወስ የሚድረስ ተዓምራትን እንደከወኑ ሲነገር ቆይቷል።
ቲቢ ጆሽዋ እጅግ ባለጸጋ እና ተጽእኖ ፈጣሪ ሰው ሆነው በ57 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ተለይተዋል። እአአ 2011 (እአአ) ፎርብስ መጽሔት ላይ በወጣው መረጃ መሰረት የሀብት መጠናቸው ከ10 አስከ 15 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ ተገምቷል።
ለመሆኑ ቲቢ ጆሽዋ ማን ናቸው?
'ነብይ' ጆሽዋ እአአ በ1963 ላይ ነበር የተወለዱት። ዝቅተኛ ገቢ ካለው ቤተሰብ የተገኙት ጆሽዋ፤ ከውልደታቸው በፊት በእናታቸው ማህጸን ለ15 ወራት ስለ መቆየታቸው ይናገራሉ።
ጆሽዋ ራዕይ ከታያቸው በኋላ አገልግሎታቸውን መጀመራቸውን ስብከትና ተዓምራትን በሚፈጽሙባቸው በተለያዩ የአገልግሎት መድረኮቻቸው ላይ ለተከታዮቻቸው ተናግረዋል።
'የእግዚአብሔር ሰው' ቲቪ ጆሽዋ ዘ ሲናጎግ፣ ቸርች ኦፍ ኦል ኔሽንስ (የሁሉም ህዝቦች ቤተ ከርስቲያን) የተባለ ቤተ-ክርስቲያን መሠርተዋል።
በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በሳምንታዊ የአገልግሎት ሥነ ሥርዓታቸው ላይ ተሳታፊ ይሆናሉ። በናይጄሪዋ ትልቋ ከተማ ሌጎስ በሚገኘው ቤተ-ክርስቲያናቸው የሚፈጽሙትን 'ተዓምር' ለመመልከት እና 'በረከተን ለማግኘት' አገራትን አቆራርጠው የሚገኙም በርካቶች ናቸው።

የጆሽዋ ተዓምረኛ ውሃ
ጆሽዋ ሰዎችን ከአደገኛው ኢቦላ በሽታ መፈወስ የሚችል ውሃ ወደ ምዕራብ አፍሪካ አገራት መላካቸው ተዘግቦ ነበር። ቲቢ ጆሽዋ ይህ ልዩ ውሃ፤ ተጠቃሚዎቹ "ምህረትን እንዲያገኙ፣ እንዲባረኩ፣ ስኬታማ እና ባለጸጋ እንዲሆኑ ያደርጋል" ይሉ ነበር።
በተከታዮቻቸው ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት የነበራቸው ቲቢ ጆሽዋ፤ ይህን 'ልዩ ውሃ' ለማግኘትና ተዓምራታቸው እንዲደርሳቸው በሚደረግ ጥረት ውስጥ ተረጋግጠው ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎችም ነበሩ።
እአአ 2013 ላይ በጋና መዲና አክራ ውሃውን ለማግኘት በተፈጠረ ግፊያ አራት ሰዎች ተረጋግጠው ሕይወታቸው አልፏል።
ትንቢት
ቲቢ ጆሽዋ በሚሰጡት 'ትንቢት' በተከታዮቻቸው ዘንድ እውቅናን አትርፈዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ አነጋጋሪ በሆኑ ጉዳዮች ላይ አስተያታቸውን በመስጠትም ይታወቃሉ።
የአሜሪካዊ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ማይክል ጃክሰን ሞትን እና መድረሻው ሳይታወቅ ለረዥም ጊዜ ቆይቶ የነበረው የማሌዢያ አውሮፕላን ጉዳይን ቀድመው ስለመተንበያቸው ጆሽዋ ተናግረዋል።
ማይክል ጃክሰንን በተመለከተ ጆሽዋ ለተከታዮቻቸው፤ "በተሰማራበት ዘረፍ እውቅናን ያታረፈ ነው። በየትኛው ስፍራ ታዋቂ ነው። እጅግ ታዋቂ። ይህ ኮከብ በሆነ ሰው ላይ የሆነ ነገር መከሰት እንደሚጀምር ይታየኛል ይህም መመለሻ ወደሌለው መንገድ ሲሄድ ይታየኛል። ይህ ጉዞ መቼ እንደሆነ አላወቅም" በማለት ተናግረው ነበር።
የማይክል ጃክሰን ሞት ሲሰማ ቲቢ ጆሸዋ ከስድስት ወራት በፊት የተናገሩት ስለ ማይክል ጃክሰን ነው ብለዋል።
የቲቢ ጆሽዋ ተቺዎች ግን ተንበያዎቹ ግልጽ እና ቀጥተኛ አይደሉም፤ ለተፈለገበት ዓላማ በቀላሉ መጠቀም እንዲያስችሉ ተደርገው ነው የሚነገሩት ይላሉ።

የቴሊቪዥን ስርጭት
ቲቢ ጆሽዋ የመሰረቱት ቤተ-ክርስቲያን በርካታ ተመልካቾች ያሉት 'ኢማኑኤል' የተባለ የቴሌቪዥን ጣቢያ አለው። በሚሊዮን የሚቆጠር ተመልካች ያለው የዩቲዩብ ቻናልም አላቸው። በርካታ ተከታይ ያሉት የፌስቡክ ገጽም እንዲሁ።
እነዚህ የመገናኛ ዘዴዎች በመጠቀም ቲቢ ጆሽዋ ስብከቶቻቸውን፣ የሚሰሩትን ተዓምራት እና ምስክርነቶችን ያስተላልፉበታል። በዚህም ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ተከታዮች ማፍራት ችለዋል።
የቀድሞ አገራት መሪዎች እና ተዋቂ ፖለቲከኞችን ጭምር ተከታይ አድርገው ማፍራት ችለዋል። የደቡብ አፍሪካው ፖለቲከኛው ጁሊየስ ማሌማ፣ የማላዊ የቀድሞ ፕሬዝደንት ጆይስ ባንዳ እና የቀድሞ የጋና ፕሬዝደንት ጆን አታ ሚልስ በቲቢ ጆሽዋ ቤተ-ክርስቲያን ከተገኙ ተጽእኖ ፈጣሪ ፖለቲከኞች መካከል ይገኙበታል።
የበጎ አድራጎት ተግባራት
በተከታዮቻቸው ዘንድ የነቢይነትን ማዕረግ ያገኙት ቲቢ ጆሽዋ፤ በበጎ ተግባራት ሥራዎቻቸውም እውቅናን አትርፈዋል።
ለረድኤት ሥራቸውም ከቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝደንት የአገሪቱን ትልቁ ሽልማት የሆነው 'ፌደራል ሪፐብሊክ ሽልማት' ተቀብለዋል።
ከቲቢ ጆሽዋ የበጎ አድራጎት ፕሮጀክቶች መካከል 'ማይ ፒፕል ኤፍሲ' የተሰኘው የእግር ኳስ አካዳሚ ተጠቃሽ ነው። ይህ አካዳሚ በአውሮፓ መድረኮች ተሳታፊ የሆኑ ናይጄሪያዊያን እግር ኳስ ተጫዋቾችን ማፍራት ችሏል።
ከማኅበራዊ ሚዲያ መታገድ
ከጥቂት ወራት በፊት ቲቢ ጆሽዋ ከጥላቻ ንግግር ጋር በተያያዘ ቅሬታ ቀርቦባቸዋል በማለት ዩቲዩብ የግል አካውንታቸውን ሲያግድ ፌስቡክ ደግሞ አንድ ቪዲዮአቸውን ከገጹ ላይ አንስቷል።
ቅሬታውን ያቀረበው አንድ ገለልተኛ የሰብአዊ መብት ተሟጋች የኢቫንጀሊካን ሐይማኖት ሰባኪውን ሰባት የሚሆኑ የዩቲዩብ ቪዲዮዎች ከተመለከተ በኋላ በሁሉም ላይ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያንን ለመፈወስ ጸሎት ሲያደርግ ነበር ብሏል።
ፌስቡክም የሐይማኖት ሰባኪውን የቲቢ ጆሽዋ አንድ ቪዲዮ ያለሳው በቪዲዮው ላይ ቲቢ ጆሹዋ "እርኩስ መንፈስ" ለማስወጣት በማለት አንዲት ሴትን በጥፊ ሲመታ ይታያል።
የሐይማኖት ሰባኪው በበኩላቸው የዩቲዩብን ውሳኔ በመቃወም ቅሬታቸውን አሰምተዋል። የዩቲዩብ አካውንታቸውም 1.8 ሚሊየን ተከታዮች አሉት።
የቲቢ ጆሽዋ ይፋዊ የፌስቡክ ገጽ ላይ የተቀመጠው መልዕክት "ከዩቲዩብ ጋር ለረጅም ጊዜ ጥሩ ግንኙነት ነበረን። አሁንም ቢሆን የተወሰነው ውሳኔ በችኮላ ነው" ይላል።
ቅሬታ ከቀረበባቸው ቪዲዮዎች መካከል በአንደኛው ላይ ቲቢ ጆሽዋ ስሟ ያልተጠቀሰ አንዲት ሴትን ቢያንስ 16 ጊዜ በጥፊ ሲመቷት ይታያል።
"የሚረብሽሽ መንፈስ አለ። መንፈሷ ሴት ናት። እራሷን አንቺ ውስጥ አስገብታለች" ሲሉም ይሰማሉ።
ቪዲዮው በዩቲዩብ ላይ ከ1.5 ሚሊዮን ጊዜ በላይ የታየ ሲሆን ሴትዮዋ በሕዝብ ፊት ቆማ እንደተፈወሰች ትናገራለች። "መንፈሷ ለቅቃኝ ሄዳለች" በማለት የሐይማኖት ሰባኪው ጸሎት እንደረዳት ትናገራለች።
አክላም "ከዚህ በኋላ ለሴቶች ምንም አይነት ስሜት የለኝም፤ ከዚህ በኋላ የምወደው ወንዶችን ብቻ ነው" ስትል ትሰማለች ትላለች።












