ቦሪስ ጆንሰን ክትባቱ በመላው ዓለም እንዲዳረስ ኃያላን አገራት ላይ ጫና ሊያደርጉ ነው

የፎቶው ባለመብት, PA Media
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን እስከ ቀጣዩ የአውሮፓዊያን ዓመት መጨረሻ ድረስ በመላው ዓለም የኮሮናቫይረስ ክትባት እንዲዳረስ ጫና ለማድረግ መዘጋጀታቸው ተሰማ።
በመጪው አርብ በአገራቸው በሚደረገው የቡድን ሰባት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ይህንን እቅዳቸውን ያቀርባሉ ተብሎም ይጠበቃል።
አሜሪካ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣልያን እና ጃፓን ለዓለም አቀፉ የፍትሃዊ የክትባት ማከፋፈያ ፕሮግራም ኮቫክስ ምን ያህል ክትባት እንደሚያጋሩ ይፋ አድርገዋል።
እንግሊዝ እና ካናዳ ግን ምን ያህል አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ እስካሁን ይፋ አላደረጉም።
ከኮሮናቫይረስ ጋር እየተደረገ ያለውን ፍልሚያ በስኬት ለማጠናቀቅ እስከሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ በመላው ዓለም ክትባቱን ለማዳረስ ቦሪስ ለመሪዎቹ በኮርንዌሉ ጉባኤ ላይ ጥሪ ያቀርባሉ።
እንዲህ ዓይነቱ ስኬት ‹‹በሕክምና ታሪክ ውስጥ ብቸኛና ታላቁ›› ይሆናል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ።
አገራቸው ዩናይትድ ኪንግደም ክትባቱን የማምረት ምጣኔን እንዴት ከፍ ማድረግ እንደሚቻል የሚደረጉ ውይይቶችን እንደምታበረታታም ተገልጿል።
የቡድን ሰባት የመሪዎች ጉባኤ ከወረርሺኙ መከሰት በኋላ ለመጀመሪያ ግዜ ገፅ ለገፅ የሚደረግ ሲሆን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ስልጣናቸውን ከተረከቡ በኋላ ወደ እንግሊዝ የሚያደርጉት የመጀመሪያ ጉብኝት ይሆናል ።
እንግሊዝ ምን ያህል ክትባት ለኮቫክስ እንደምታበረክት በጉባኤው ላይ ይፋ ታደርጋለች ተብሎ ይጠበቃል።
ባለፈው ሳምንት የፓርላማ አባላት ብሎም የአገራት መሪዎች እንግሊዝ የተያዘው የፈረንጆች አመት እስከሚጠናቀቅ ድረስ ቢያንስ 100 ሚሊዮን ክትባት እንድታበረክት ደብዳቤዎችን እንደፃፉላቸው ይታወሳል።
የቀድሞው የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶኒ ብሌር በበኩላቸው ‹‹እውነታው›› መንግስታት ‹‹የራሳቸውን ሰዎች የመጠበቅ ግዴታ አለባቸው››፤ ሁል ጊዜም ለራሳቸው ዜጎች ክትባት ቅድሚያ ይሰጣሉ ሲሉ መናገራቸውም ይታወሳል።
አክለውም በዚህ ጉዳይ ፍፁም መሆን አይቻልም፤ ከመዳረሱ በፊትም የተወሰነ ክትባት መለግስ ይቻላልም ብለዋል።












