ኪም ጆንግ ኡን ፊልም፣ ጂንስና አፀያፊ ቃላት ላይ ጦርነት አወጁ

ሰሜን ኮሪያ ባንዲራ

ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ አዲስ ሕግ አፅድቃለች። የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ ኡን ፊልም፣ ጂንስና አፀያፊ ቃላት ላይ ጦርነት አውጀዋል።

የሕጉ ዓላምማ የውጭ ተፅዕኖን ማስቀረት ነው። የሆሊውድ አሊያም የቦሊውድ ፊልም ሲኮመኩም የተገኘ፣ የውጭ ተፅዕኖ ያለበት ልብስ ያደረገ እንዲሁም ዘመናይ ቃላት የተጠቀመ ይቀጣል። ግን ለምን?

ዮ ሚ እንደምትለው አንድ ግለሰብ የደቡብ ኮሪያ ድራማ እየተመለከተ በመገኘቱ በሞት ሲቀጣ እሷ 11 ዓመቷ ነበር።

የሞት ቅጣቱን መላ ጎረቤቶቹ ወጥተው እንሚለከቱት ተደርጓል ትላለች መኖሪያዋን ደቡብ ኮሪያ ያደረገችው ዮ።

የሰሜን ኮሪያ ብሔራዊ ዘብ የውጭ ሃገራት ፊልሞችን በድብቅ ማስገባት ትርፉ ሞት እንደሆነ ሁሉም እንዲያውቅ ይሻሉ።

ይህንን አስቡት - የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሎባችኋል፤ ኢንተርኔት የለ፤ ፌስቡክና ትዊተር የለ፤ ማየት የምትችሉት የመንግሥትን አጀንዳ የሚያቀነቅኑ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ብቻ ነው - ሕይወት በሰሜን ኮሪያ ይህን ይመስላል።

አሁን ደግሞ የሃገሪቱ መሪ ኪም ጆንግ ኡን አዲስ ሕግ አውጥተዋል።

ከደቡብ ኮሪያ፣ ጃፖንና አሜሪካ የመጡ ፊልሞችን ቤቱ ያከማቸ ሰው ሞት ይጠብቀዋል። ሲያዩ የተገኙ ደግሞ እስከ 15 ዓመት ድረስ በእሥር ይቀጣሉ።

ይህ ብቻ አይደለም። ኪም ጁንግ ለሃገራቸው ወጣት ሊግ አንድ ደብዳቤ ፅፈዋል። "መረን የለቀቁ፣ ፀረ- ማሕበረሰባዊ" ወጣቶችን አደብ አስይዙልኝ ብለው።

የውጭ ሃገር ተፅዕኖ ያለባቸው ንግግሮች፣ የፀጉር ቁርጥ እና አለባበስ "አደገኛ መርዝ" ናቸው ብለዋል ኪም።

ሰሜን ኮሪያ ውስጥ ምንጮች እንዳሉት የሚነገርለት ዘ ደይሊ ኤንኬ የተሰኘው የደቡብ ኮሪያ ጋዜጣ ሶስት ወጣቶች እንደ ኬ ፖፕ ኮከቦች ፅጉራቸውን በመቆረጣቸው እንዲሁም ፋሽን የዞረበት ጂንስ በመልበሳቸው ወደ ትምህርት ማዕከል እንዲገቡ ተደርገዋል።

ለዚህ ሁሉ ምክንያቱ ኪም የጦር መሣሪያ የሌለበት ጦርነት ውስጥ መግባታቸው ነው።

ተንታኞች እንሚሉት ኪም የውጭ ሃገር መረጃ ሕይወት እየከበደ ወደመጣባት ሰሜን ኮሪያ ዘልቆ እንዲገባ አይሹም።

ሚሊዮኖች ረሃብ ላይ እንዳሉ እየተነገረ ነው። ኪም ዜጎቻቸው የጎረቤት ሃገር ደቡብ ኮሪያን ፊልሞች እያዩ ሆዳቸው እንዲጮህ የሻቱ አይመስልም።

የደቡብ ኮሪያ ፊልሞች በደልቃቃ ሕይወት የተሞሉ ናቸው። ሴኡል ደግሞ ከዓለማችን ውዷ ከተማ አንዷ ናት። ሁሉም ተንደላቆ የሚኖርባት።

ሰሜን ኮሪያ ከተቀረው ዓለም ይበልጥ የተቆራረጠችው ባለፈው ዓመት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ገብቶ ድንበሯን በዘጋች ወቅት ነው።

ከቻይና የሚመጡ አስፈላጊ ቁሳቁሶችና ሌሎች ሸቀጦች ሙሉ በሙሉ ቆመው ነበር። አሁን ግን አንዳንድ ዕቃዎች እየገቡ እንደሆነ ይነገራል።

ወረርሽኙ በፊትም ገንዘቧን ለኒውክሌር ጦር መሣሪያ በማዋሉ ምጣኔ ሃብቷ ለተቃወሰው ሰሜን ኮሪያ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው የሆነባት።

በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ጠቅላይ መሪው ኪም ራሳቸው "አሁን ያለንበት ወቅት በጣም አስቸጋሪው ነው፤ ልንወጣው ይገባል" ሲሉ ተናግረው ነበር።

ሕጉ ምን ይላል?

ዘ ደይሊ ኤንኬ ነው የሕጉ ግልባጭ መጀመሪያ ማግኘት የቻለው።

"አንድ ሠራተኛ ከተያዘ የኩባንያው ኃላፊ ይቀጣል። አንድ ሕፃን ካስቸገረ ቤተሰቦቹ ሊቀጡ ይችላሉ። ሁሉም እርስ በርስ እንዲጠባበቅ ተደርጎ እንደተሠራ ይንፀባረቃል" ይላሉ የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ሊ ሳንግ ዮንግ ለቢቢሲ ሲናገሩ።

ይህ የሆነው ወጣቱ ትውልድ ስለ ደቡብ ያለውን ሕልም ለመቅጨት ነው ይላሉ አዘጋጁ።

"በሌላ ቋንቋ ከሌላው ዓለም ባሕል ዘልቆ ከገባ ዜጎች እምቢታን ሊለምዱ ይችላሉ ሲል ገዢው መደብ ደምድሟል።"

ቾይ ጆንግ-ሁን ባለፈው ዓመት ከሰሜን ኮሪያ ሸሽተው ካለመጡ መካከል አንዱ ነው።

"ሆድ ጠግቦ የደቡብ ኮሪያ ፊልም ብትመለከት ችግር የለውም ለመዝናናት ነውና። ነገር ግን ሆድ ከተራበ መከራ ነው። ሕዝቡ ሊቆጣ ይችላል" ሲል ለቢቢሲ ይናገራል።

ሕጉ ይሠራ ይሆን?

ከዚህ በፊት ወጥተው የነበሩት ሕግጋት ሰዎች ምን ያክል መላ እንደማያጡ ያሳዩ ናቸው። ምክንያቱም በርካታ ፊልሞች በቻይና በኩል ሲያልፉ ነበርና።

ቾይ እንደሚለው ለበርካታ ዓመታት ፊልም በድብቅ ይጋዝ የነበረው በፍላሽ ዲስኮች ነው። እኒህ የሌባ ጣት እንኳ የማይክሉ ፊልም ተሸካሚዎች አሁን በሰሜን ኮሪያ በጣም ተለምደዋል። በይለፍ ቃልም መቆለፍም ባሕል ሆኗል።

"ሶስት ጊዜ የተሳሳተ የይለፍ ቃል ካስገባህ ዩኤስቢው ፊልሙን ያጠፋዋል። ፊልሙ አገዛዙን የሚያስቆጣ ከሆነ ደግሞ አንድ ጊዜ ስትሳሳት እንዲጠፋ ማድረግ ትችላለህ።"

"አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ፊልሙን አንድ ጊዜ ብቻ ማየት እንዲችሉ አድርገው ይቀዳሉ። ይህ ማለት ለሌላ ሰው ተላልፎ ቢሰጥ እንኳ አይሠራም ማለት ነው።"

ሚ-ሶ ጎረቤቶቿ ፊልም ለማየት የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌላ ታስታውሳለች።

በአንድ ወቅት ሰዎች ተሰባስበው "ስቴርዌይ ቱ ሄቭን" የተሰኘ የደቡብ ኮሪያ ፊልም ለማየት የመኪና ባትሪ ተበድረው ከጄኔሬተር ጋር በማጣመድ በቴሌቪዥናቸው ሲመለከቱ እንደነበር ታወሳለች።

ይህ ፊልም ከ20 ዓመታት በፊት ደቡብ ኮሪያ ውስጥ እጅግ ተወዳጅ ከነበሩ ፊልሞች መካከል ነበር።

ቾይ እንደሚለው በዚህ ወቅት ነው ለውጭ ሃገራት መገናኛ ብዙሃን ያለው ፍቅርም እየጠነከረ የመጣው። ወቅቱ ደግሞ ሲዲና ዲቪዲ እንደአሸኝ የፈላበት ጊዜ ነበር።

ነገር ግን የፒዮንግያንግ መንግሥት ይህን አስተውሎ ስለነበር በዩኒቨርሲቲዎች አካባቢ እርምጃ ይወስድ ጀመር።

በወቅቱ ከ20 ሺህ በላይ ሲዲዎች እንደተገኙ ቾይ አይዘነጋም።

ኪም ጄውም-ሂዮክ የ16 ዓመት ወጣት ሳለ ሕገ ወጥ ቪድዮ ይዘሃል ተብሎ ታሥሮ ነበር። ጠባቂዎቹ ወደ ምርመራ ቦታ ወስደውት እንቅልፍ እንዳይተኛ እንዳደረጉት ይናገራል። ለአራት ቀናት ስቃይ ደርሶብኛልም ይላል።

በርካታ ምንጮች ባለፈው ዓመት ሰሜን ኮሪያ ውስጥ ያሉ እሥር ቤቶች ሰፋ ተደርገው እንዲሠሩ መደረጋቸውን ይናገራሉ።

ሰሜን ኮሪያዊያን የተቀረው ዓለም ምን እንደሚመስል የሚያዩ በደቡብ ኮሪያ አሊያም በጃፓንና በአሜሪካ ፊልሞች አማካይነት ነው።

ብዙዎች ሃገሪቱን ጥለው የወጡ በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት የውጭ ዓለም ምን እንደሚመስል ከመውጣታቸው በፊት አይተዋል።

ነገር ግን አሁን ባለው "የግድያ" ትዕዛዝ ምክንያት ከሃገር መውጣት በፍፁም የማይችልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል።