ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ500 ቢሊዮን ብር በላይ ዓመታዊ በጀት አዘጋጀች

የኢትዮጵያ ብር

የፎቶው ባለመብት, CBE/FB

የኢትዮጵያ ዓመታዊ በጀትን ለመጀመሪያ ጊዜ ከ500 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያደርግ ረቂቅ በጀት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸደቀ።

የመጪው ዓመት የኢትዮጵያ መንግሥት በጀት ከዘንድሮው በ85 ቢሊዮን ብር ከፍ እንዲል የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያዘጋጀው ረቂቅ በጀት አመልክቷል።

ምክር ቤቱ የቀጣዩ ዓመት የፌደራል መንግሥቱ በጀት 561 ቢሊዮን ብር በላይ በላይ እንዲሆን የወሰነ ሲሆን በ2013 ካለው የ476 ቢሊዮን ብር በጀት በ18 በመቶ ከፍ ብሏል። ይህም የየ85 ቢሊዮን ብር ጭማሪ ታይቶበታል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ2014 ዓ.ምን በጀት ከማጽደቁ በፊት በቀዳሚነት ለዚህ ዓመት ባስፈለገው ተጨማሪ በጀትና የመንግሥት ወጪን ለመሸፈን ያስፈለገው ማስተካከያ ተግባራዊ እንዲሆን በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይ መክሯል።

በዚህም መሠረት ለ2013 ዓ.ም ተጨማሪ በጀት ያስፈለገው በሰሜን የአገሪቱ ክፍል ከተከሰተው ጦርነት ጋር ተያይዞ ላጋጠሙ ወጪዎች፣ በድርቅ ለተጎዱ፣ ለተፈናቀሉ እና ለተመላሾች የእለት እርዳታ አቅርቦት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል፣ ለማዳበሪያ አቅርቦት ድጎማ፣ ለጎርፍ መከላከል እንደሆነ ተገልጿል።

በተጨማሪም ለማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የአቅም ግንባታ ፕሮጀክትና "የመጠባባቂያ በጀት በማለቁ በቀጣይ ወራቶች ለሚያስፈልጉ የተለያዩ ወጪዎች የመጠባበቂያ በጀት መመደብ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው" ሲል የሚኒስትሮች ምክር ቤት መግለጫ አመልክቷል።

የተጠየቀው 26.4 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ከተለያዩ ምንጮች የሚገኝ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ምክር ቤቱም ይህንኑ ተቀብሎ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቶታል።

ከዓመት ዓመት ጭማሪ እያሳየ የመጣው የፌደራል መንግሥቱ ዓመታዊ በጀት በቀጣዩ 2014 ዓ.ም 561.67 ቢሊዮን ብር እንዲሆን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወስኗል። ይህም አስካሁን አገሪቱ ከያዘችው ዓመታዊ በጀት ሁሉ የላቀው ነው።

ለቀጣይ ዓመት የተያዘው በጀት ለመደበኛ ወጪዎች 162 ቢሊዮን ብር፣ ለካፒታል ወጪዎች 183.5 ቢሊዮን ብር፣ ለክልሎች የሚሰጥ ድጋፍ 203.95 ቢሊዮን ብር፣ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ 12 ቢሊዮን ብር መያዙ ተገልጿል።

ቅዳሜ ዕለት ግንቦት 28/2013 ዓ.ም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባደረገው ስብሰባ ላይ የተወሰነው ተጨማሪ በጀትና ረቂቅ በጀት ለተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ መጽደቅ ይኖርበታል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የነበራትን ዓመታዊ በጀት ስንመለከት በ2012፣ 386 ቢሊዮን 954 ሚሊዮን 965 ሺህ 289 የነበረ ሲሆን በ2011 ደግሞ 346 ቢሊዮን 915 ሚሊዮን 451 ሺ 948 ተመድቦ ነበር።

በ2010 የነበረው በጀት 320.8 ቢሊዮን ብር ሲሆን፤ ከ60 በመቶ የሚበልጠው ለትምህርት፣ ለግብርናና ለመሰረተ ልማትና ለጤና ማስፋፊያ እንዲሆን ተብሎ የተበጀተ ገንዘብ ነበር።

ከ300 ቢሊዮን ብር በታች የነበረው የኢትዮጵያ ዓመታዊ በጀት በ2009 ዓ.ም ላይ 274.3 ቢሊዮን በጀት መሆኑ የሚታወስ ነው።