ከመቶዎች እስከ መቶ ሺህ ብሮች የሚንቀሳቀስበት የቀብር ማስፈጸም አገልግሎት

የቀብር ሥነ ሥርዓት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከመቶዎች እስከ መቶ ሺህ ብሮች የሚንቀሳቀስበት የቀብር ማስፈጸም አገልገሎት ልክ እንደተለያዩ ግብይቶች ሁሉ የቀብር ሥርዓትም የግለሰቦች አቅም የሚታይበት እየሆነ መጥቷል።

እንደ አንዳንድ 'ቢዝነሶች' የቀብር አፈጻጸሙ ደረጃና አይነት አለው።

እጅ ያጠረው የሟች ቤተሰብ 'እንደነገሩ' ቀብር ለማከናወን ቢያንስ 7 መቶ ብር ያስፈልገዋል።

የለም 'ሞትና ሠርግ አንድ ነው' ቀብሩ ደመቅ ይበል መታሰቢያውም ይጉላ ያለ አቅም ያለው የሟች ቤተሰብ ደግሞ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ብር ከኪሱ ማውጣት ይጠበቅበታል።

ታዲያ የሥርዓቱን ደረጃ የሚለዩት ቀብሩን ለማከናወንና ለቀስተኛን ለማስተናገድ ጥቅም ላይ የሚሉ ነገሮች ናቸው።

የቀብር አፈጻጸም ደረጃና ዓይነቶች

ነጋሽ ደገፉ ጠቅላላ የቀብር አስፈጻሚ ድርጅት በአዲስ አበባ ከሚገኙ የቀብር አስፈጻሚዎች አንዱ ነው።

የድርጀቱ ሥራ አስኪያጅ ኃይሉ ነጋሽ አባታቸው የጀመሩት ይህ ሥራ አርባ ዓመታት ማስቆጠሩን ይገልጻሉ።

አባታቸው በዚህ ሥራ ቀዳሚ ከሆኑት መካከል እንደሚመደቡም ይናገራሉ።

እሳቸውም ቢሆኑ ቀብር ማስፈጸም 'ጥርሳቸውን የነቀሉበት' ነው - ከ25 ዓመታት ለሚልቅ ጊዜ በሥራው ላይ ቆይቷል።

በአራት የተለያዩ ቦታዎች ሱቆች ከፍተው እየሰሩም ይገኛሉ።

የቀብር ሥርዓትን በተሽከርካሪዎች እና በቅብር አስፈጻሚዎች 'ማጀብ' እየተለመደ ነው የሚሉት አቶ ኃይሉ ሥርዓቱ በተለያየ ደረጀና አይነት እንደሚፈጸም ያስረዳሉ።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ የአገልገሎቱን ደረጃና ዋጋ ከሚወስኑት መካከል አንዱ የቀብር ሥርዓቱ የሚታጀብበት ተሽከርካሪ አይነትና ብዛት ነው።

"አንድ ጥቁር የቀብር ቶዮታ ዶልፊን መኪና ሱፍ ለብሰው አስከሬን የሚያጅቡ ፕሮቶኮሎች ሳይኖሩ ቢፈለግ እንደቦታው ርቀት ነው፤ አንድ ሺህ ብር ወይም አንድ ሺህ ሁለት መቶ ብር ይሆናል" ሲሉ ያስረዳሉ።

ተሸከርካሪው አይነት ሃይውንዳይ ወይም መሴዲስ ቢሆን ዋጋው እንዲሁ ከፍ ይላሉ። ይህ የሬሳ ሳጥንና ሌሎች ወጪዎችን አይጨምርም።

ስለዚህ ተጠቃሚው "የሚወስደው የሳጥን ደረጃ፣ የሚጠቀመው የመኪና አይነት፣ የዲኮሬሽን [የማስጌጭያ] አበባ አይነትና መኪና ላይ የሚደረገው የሟች ፎቶ አጠቃቀም ላይ የሰው ፍላጎት ይለያያል" ሲሉ የሚያስረዱት አቶ ኃይሉ አገልገሎቱ በአማካይ ከ11 እስከ 20 ሺህ በር ሊያስወጣ እንደሚችል ገልጸዋል።

ቀብር የማስፈጸም ሥራ የሬሳ ሳጥንን ከማቅረብ ድንኳንን ጨምሮ የድግስ ዕቃዎችን እስከ ማከራየት እንደሚዘልቅ የሚያስረዱት አቶ ኃይሉ፤ የተሟላ አገልገሎት ሰጥተው "በአንድ ሥራ ላይ እስከ ሦስት መቶ እና አራት መቶ ሺህ ብር" ተከፍሏቸው የሰሩባቸው ወቅቶች እንዳሉ ተናግረዋል።

በዚህ ዋጋ የሚሰጠውን 'ሙሉ' አገልግሎት "ብዙ ጊዜ የሚውስዱት ውጭ አገር የሚኖሩና እድር የሌላቸው ሰዎች ናቸው" የሚሉት አቶ ኃይሉ ይህም የምግብ አገልግሎትን እንደሚጨምር ይጠቅሳሉ።

የሬሳ ሳጥኖች ደረጃና ዋጋ

የሬሳ ሳጥኖች በአገር ውስጥ እንደሚሰሩና ከውጭም እንደሚገቡ ያሉ ሲሆን ዋጋቸው እንደ ጥራት ደረጃቸው ይለያያል።

ከዚህም ባሻገር የሳጥኖቹ 'ዲዛይን' ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለና እየተለወጠ ይገኛል።

"ሳጥን ማለት እኮ ልክ እንደሶፋ ማለት ነው። የድሮና የአሁን የሶፋ ዲዛይን አንድ አይደለም። ሙያተኞቹም ከኢንተርኔት በማውረድና አንዱ ከአንዱ በመቀያየር ነገሩ እየሰፋ ሄዷል" ይላሉ አቶ ኃይሉ።

ታዲያ ዝቅተኛ የጥራት ደረጃ ያለው የሬሳ ሳጥን ከ700 መቶ ብር እስከ 3 ሺህ ብር ሲሸጥ ከፍተኛ ጥራት ያለውና ከውጪ አገር የገባ ሳጥን ደግሞ እስከ 150 ሺህ ብር ያወጣል።

"እኛ ማንኛውም ሰው እንደ አቅሙ የሚጠቀምበት አገልግሎት ይዘን ነው የምንንቀሳቀሰው" ሲሉም ያስረዳሉ።

በከፍተኛ የጥራት ደረጃ የተቀመጠ ሳጥን በቀለሙ፣ በግዝፈቱና 'በዲዛይኑ' የሚለይ ሲሆን ከ80 ሺህ 150 ሺህ ባለው ዋጋም ይሸጣል።

የመቃብር ስፍራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

"ቀብር የማስፈጸም ራ እንደማንኛውም ቢዝነስ ነው"

ቀብር ማስፈጸም እንደማንኛውም 'ቢዝነስ' ነው ሲል የሚያስረዱት አቶ ኃይሉ በተለያየ አጋጣሚ ወደ ሱቃቸው ሄዶ "እኔ እፈራለሁ አልጠጋም" የሚል አለ።

"ሰው ሞቱን ስለሚፈራ ነው እንጂ [የሬሳ] ሳጥኑ እኮ ማለት እንጨት ማለት ነው" ይላል።

እንደ አቶ ኃይሉ ሥራው ወጥ ባህሪ የለውም 'አንዴ ሞቅ አንዴ ቀዝቀዝ' የሚል ሲሆን "ቢያንስ ግን በቀን አንድ አበባ ሳንሸጥ አንውልም" ይላሉ። በቀን ከሦስት እስከ አምስት ቀብሮችን አስፈጽመው እንደሚያውቁም ጠቁመዋል።

"ወደ ማንኛውም የሥራ ዘርፍ ሲገባ ሁል ጊዜም ትርፍ የለም ሁል ጊዜም ገቢ የለም" ላሉ አቶ ኃይሉ፤ ሥራ "ቀዘቀዘ የምትሉት መቼ ነው?" ለሚለው ጥያቄም "ለሁለት ለሦስት ቀን ምንም ካልተንቀሳቀሰ እኮ ሰሞኑን ሥራ የለም እንላለን" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

ቢቢሲም "ታዲያ ይሄ፣ ሰው ይሙት ብላችሁ የምትመኙ አይመስልም ወይ?" የሚል ጥያቄ አስከተለ፤ "ብዙ ሰው ሊመስለው ይችላል። ግን እንደ እውነታውና እንደተፈጥሮ ሕግ ሲታሰብ የሰው ልጅ ይሙት ብንልም ሰው አይሞትም፤ ባንልም ሰው መሞቱ አይቀርም። ብንልም አናገኝማ!" በማለት አስረድተዋል።

እምነት ተቋማት ቅጥር ግቢዎች የሚፈጽሙ ቀብሮች

ቀብር ለማስፈጸም ከሚወጣ ወጪ በተጨማሪ ለቀብር ስፍራዎች የሚወጣም ወጪ አለ። ይህም ቦታውን ማዘጋጀትን ይጨምራል።

ቢቢሲ ባገኘው መረጃ መሰረት በአዲስ አበባ ኮተቤ አካባቢ የሚገኝ የኮተቤ ደብረ ልዑል ዳግማዊ ቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል እና ኆኅተ ሰማይ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ ቀብር ለማስፈጸም ከ800 ብር እስከ 65 ሺህ ብር ይከፈላል።

ቤተክርስቲያኗ ለቀብር የሚሆን ስፍራን ስታዘጋጅ የሰበካ ጉባኤ አባል ለሆነና ላልሆነ ተብሎ የተከፈለ ሲሆን ዋጋውም ይለያያል።

ዝቅተኛው የቀብር አይነት 'ድቤ' ተብሎ የሚጠራ ሲሆን መሬት ተቆፍሮ ብቻ የሚከናወን ነው። አባል ለሆነ/ች ሟች ቤተሰብ 800 ብር ላልሆነ/ች ደግሞ አንድ ሺህ ብር ይከፈላል።

አባል ለሆነ/ች 2000 ላልሆነ/ች ደግሞ 3000 የሚከፈልበት 'ሊሾ' የተባለ የቀብር አይነት ደግሞ በሲሚንቶና በአሸዋ 'የሚለሰንበት' የቀብር አይነት ነው።

ሌላኛው በድንጋይ የሚሰራ ሐውልት ያለ ሲሆን ዝቅተኛው ለአባል 5 ሺህ አባል ላልሆነ/ነች 7 ሺህ 500 ብር ይከፈላል። ሁለተኛው ደረጃ ደግሞ 8 ሺህ እና 10 ሺህ ብር ይወጣል።

በእምነበረድ የሚሰሩ ሐውልቶችም ደረጃ እንዳላቸው የቤተክርስትያኒቱ መረጃ ያሳያል። ዝቅተኛው በ20 ሴንቲ ሜትር ከፍታ የሚሰራ ሲሆን አባል ለሆነም ላልሆንም 27 ሺህ ብር ይከፈልበታል።

ከፍተኛው ሐውልት ደግሞ 60 ሴንቲ ሜትር ከፍታ ያለው ሲሆን ያለምንም ወጪ ተጨማሪ ቀብርን ለማከናወን የሚያስችል ቦታም ይኖረዋል።

በሌላ በኩል ኮልፌ አካባቢ የሚገኘው የእስልምና እምነት ተከታዮች የመቃብር ስፍራ ላይ ሥርዓተ ቀብር በተመሳሳይ ደረጃ የሚፈፀም ሲሆን 1500 ብር ይጠየቅበታል።

ሌሎች የእምነት ተቋማትም በተለያየ ደረጃና ክፍያ የቀብር ስፍራን ያዘጋጃሉ።

አቶ ኃይሉ 'እንደማንኛውም ቢዝነስ ነው' ያሉት ቀብር የማስፈጸም ሥራ በርካታ ኢትዮጵያውያን ተሰማርተዋል።

በምድር በብዙ ውጣ ውረድ የሚያልፈው የሰው ልጅ ህልፈቱም ለብዙዎች የገቢ ምንጭ ይሆናል።