ሰባኪው የአንድ ቢሊዮን ብር አውሮፕላን ግዙልኝ አለ

በሰሜን አሜሪካ የግል ጄት ያላቸው ሰባኪዎች በርካታ ናቸው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በሰሜን አሜሪካ የግል ጄት ያላቸው ሰባኪዎች ቁጥር በርካታ ነው

በአሜሪካ እውቅ ከሆኑ የቲቪ ሰባኪዎች (ቴሌቫንጀሊስት) አንዱ የሆነው ነብይ ጀሴ ዱፕላንቲስ ተከታዮቹን የግል ጄት እንዲገዙለት በይፋ ጠየቀ። ምክንያቱም "ኢየሱስ አህያ ሊጋልብ አይችልም" ብሏል።

አስገራሚ የሆነው ታዲያ ይህ ሰባኪ ሦስት የግል አውሮፕላኖች ያሉት ሲሆን ምዕመኑን መዋጮ እየጠየቀ ያለው ለ4ኛ አውሮፕላን (ጄት) ግዢ ነው።

ሰባኪ ዱፕላንቲስ እንደሚለው ከሆነ ጌታ ግዛ ያለው ጄት ፋልኮን 7X የተባለውን ሲሆን ዋጋው ደግሞ 54 ሚሊዮን ዶላር ነው። ይህ ገንዘብ በብር ሲመነዘር 1.5 ቢሊዮን ብር ይጠጋል።

ነብይ ዱፕላንቲስ ጨምሮ እንዳለው መጀመርያ ጌታ ይህን የግል ጄት ግዛ ሲለው "ትዕዛዙን ለመቀበል አቅማምቼ ነበር" ካለ በኋላ ጌታም ማቅማማቴን አይቶ "'አንተን ክፈል አላልኩህም፤ ይኖረኛል ብለህ እመን ነው ያልኩህ ሲል ጌታ ገሰጸኝ" ብሏል።

ምንም እንኳ የግል አውሮፕላን ያላቸው ሰባኪዎች በአሜሪካን ምድር ማየት አዲስ ባይሆኑም ይህ የሰባኪ ዱፕላንቲስ ለ4ኛ ጊዜ "የጄት ግዙልኝ" ጥያቄ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃንን በስፋት እያነጋገረ ነው።

በተለይ የትዊተር ተጠቃሚዎች የሰባኪውን ድርጊት ማመን ተስኗቸዋል። አንዳንዶቹም የመጽሐፍ ቅዱስ አንቀጾችን እየጠቀሱ እየሞገቱት ይገኛሉ። "ሐሳዊ ነብይ" ያሉትም አልጠፉም።

"ምናለ ይህን የሚያህል ገንዘብ ለእርሱ መንደላቀቂያ ከሚሆን ለድሆች እርዳታ ቢውል" ያሉም አሉ።

የ68 ዓመቱ እውቅ ሰባኪ ነብይ ዱፕላንቲስ በቪዲዮ ባስተላለፈው መልእክት እንዲህ ብሏል፦

"እንደምታውቁት ጄት ለኔ ብርቅ አይደለም። ከዚህ በፊት ሦስት የግል ጄቶች ነበሩኝ። ተጠቅሜባቸው ለኢየሱስ ክርስቶስ ስል አቃጥያቸዋለሁ።"

ነብይ ዱፕላንቲስ እንደሚለው የጌታን ቃል ለዓለም ለማድረስ በተራ መኪና ወይም በባቡር ወይም በመርከብ የማይሆን ነገር ነው። ይህን ለማድረግ የቀረኝ ዕድሜ በቂ ካለመሆኑም በላይ አሰልቺም ነው።

አንድ ጊዜ ነዳጅ ተሞልቶ ውቅያኖስ የሚያሻግርና ያለ ዕረፍት ረዥም ርቀት የሚጓዝ ዘመናዊ ጄት ያስፈልገኛል ብሏል።

በ2015 ሰባኪ ዱፕላንቲስ ኬኔት ኮፕላንድ ከሚባል ሌላ ሰባኪ ጋር ሆኖ በቪዲዮ ባስተላለፈው አንድ መልዕክት እንደርሱ ያለ ትልቅ ሰባኪ ከሕዝብ ጋር በአውሮፕላን መሳፈር አሳፋሪ መሆኑን ለመግለጽ "በሕዝብ አውሮፕላን መጓዝ በትቦ ውስጥ ከአጋንንት ጋር እንደመሳፈር ያለ ነው" ብሎ ነበር።