መቃብሮችን የምታፀዳው የ12 ዓመቷ አውስትራሊያዊት

ታዳጊዋ ከማጽጃ ብሩሽዋ ጋር መቃብር ላይ ተቀምጣ

የፎቶው ባለመብት, Tabetha Whitby Kleeman

አውስትራሊያዊቷ ቲጄ ክሌማን አራት አመት ሲሆናት ነበር የመቃብር ሥፍራዎቹ አቅራቢያ ወደሚገኘው የመኖሪያ ቤታቸው ከቤተሰቦቿ ጋር የመጣችው።

የመቃብር ስፍራዎቹ ከቤታቸው ጀርባ እንደመገኘታቸው የተለያዩ ፍርሃቶች የልጅነት አእምሮዋን ያስጨንቁት ነበር።

ከፍርሃቶቹ ሁሉ አእምሮዋን በብርቱ የተቆጣጠረው ግን የሙታን መናፍስት ቢመጡስ የሚለው ነው።

የልጃቸውን ፍርሃት የተመለከቱት እናቷ ወደ መቃብር ሥፍራዎቹ በመውሰድ እንድትጎበኝ አደረጓት።

የልጃቸውን ፍርሃት ለማስወገድ በተጨማሪ ሌላ መላም ዘየዱ።

'መቃብሮቹን ለምን አናፀዳቸውም' አሏት። እርሷም መቃብሮቹን በማጽዳት ስትጠመድ የሙታን መናፍስት ሃሳብ ከአእምሮዋ እየጠፋ መጣ።

ገና በአራት ዓመቷ የጀመረችውን መቃብሮችን የማጽዳት ተግባሯን ዛሬ ድረስ ቀጥላበታለች።

ከስምንት ዓመት በኋላም ለዚሁ ተግባሯ በአካባቢዋ ላበረከተችው የማህበረሰብ አገልግሎት ከአውስትራሊያ መንግሥት ሽልማትን አግኝታለች።

ሽልማቱ የተለየ ስሜት እንደፈጠረባት የምትናገረው ቲጄ,፣ በወቅቱ እናቷም ማልቀሳቸውን ታስታውሳለች።

"ሽልማቱን ስላገኘው የደስታ ስሜት ተሰምቶኛል፤ ምክንያቱም ለሌሎች እናንተም ይህንን ማድረግ ትችላላችሁ ብዬ መናገር አስችሎኛል" የምትለው ቲጄ፣ እርሷ በ12 ዓመቷ ይህንን ለማህበረሰቡ ማድረግ ከቻለች፤ ሌሎች በሳምንት የአንድ ወይንም ሁለት ሰዓት ብቻ በመውሰድ ለማህበረሰቡ በርካታ አስተዋጽኦ እንዲሁም የደስተኝነት ስሜት እንዲሰማቸው ማድረግ እንደሚችሉ ትገልጻለች።

ቲጄ ወደ መቃብር ስፍራዎቹ በሳምንት አንዴ ወይንም ሁለቴ በመሄድ የጽዳት ስራዋን ታከናውናለች።

በሥፍራው በመቶዎች የሚቆጠሩ መቃብሮች የእርሷን እጅ ይጠብቃሉ።

ሁሉንም ለማጽዳት ዓመታት ሊወስድ እንደሚችል የምትናገረው ታዳጊዋ፣ ከዓመት በኋላ ዳግመኛ ሁለተኛ ዙር ማጽዳት እንደምትጀምር ትገልጻለች።

ለራሷም "አጃሂብ፤ እኔ ነኝ ይህንን ሁሉ ያፀዳሁት" እንደምትልም ታክላለች።

ቲጄ በቅርቡ በእጇ ላይ የቀዶ ጥገና ብታካሂድም፣ ከዚህ ተግባሯ ግን ምንም የሚያግዳት ነገር እንደሌለ ገልጻለች።

ሰዎች ሲመለከቱኝ ደስ እንዲላቸው ካደረግሁ፣ እርሱ ያኮራኛል ስትልም ትናገራለች።

የአካባቢው ነዋሪዎች የሚወዷቸው ሰዎች አስከሬን ያረፈበት ስፍራ ፀድቶ ሲመለከቱት እርሷን ስለመልካም ድርጊቷ እነደሚያመሰግኗትም ታክላለች።

ያ ደግሞ የሚፈጥረውን ስሜት በቃላት ለመግለጽ እንደሚከብዳት አልሸሸገችም።

ቲጄ አሁን የቀድሞ ፍርሃቷን አታስታውሰውም።

በዚያ የመቃብር ስፍራ ነጻ መሆን ይሰማኛል የምትለው ቲጄ፣ "ልክ ቤት እንዳለሁ ያህል ይሰማኛል፤ ደግሞም እወደዋለሁ" ብላለች።

ቲጄ በየወሩ የንጽህና ቀን ለማዘጋጀትና በርካቶች ለሚኖሩበት ማህበረሰብ የበጎ ፈቃደኝነት የማህበረሰብ ግልጋሎት እንዲሰጡ ለማነሳሳት እቅዱ አላት።

እስካሁን ድረስ ይህንን በማድረጌ ደስተኛ ነኝ፤ በቀሪው የሕይወት ዘመኔ ሁሉ ይህንን ተግባር መቀጠል እፈልጋለሁ ስትልም ገልፃለች።