እንቅልፍ በመቀነስ የሥራ ጫናን ‘የመበቀል’ ልማድ

ማ ራዎ ከጠዋቱ 3 ሰዓት እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት፤ በሳምንት ለስድስት ቀናት ትሠራ ነበር።
ቻይና፣ ሻንጋይ ውስጥ ለሚገኝ መድኃኒት አምራች ትሠራ የነበረው ማ፤ በአጭር ጊዜ ነበር ሕይወቷ በሥራ የተዋጠው። ለመመገብ አጭር ሰዓት ብቻ ነበራት። ለመተኛትም እንዲሁ።
"ከሥራ ውጪ ምንም የግል ሕይወት አልነበረኝም። ድብርት ይዞኝ ነበር" ትላለች።
ሥራዋ ለግል ሕይወት ጊዜ ስላሳጥት እንቅልፏን መስዋዕት እያደረገች ለራሷ ጊዜ ለመስጠት ትሞክር ነበር። ካላት አጭር የመኝታ ጊዜ ቀንሳ ዜና ማንበብ፣ ቪድዮ ማየት ጀመረች።
ብዙዎች እንደ ማ እንቅልፍ ትተው የተለያየ ተግባር ያከናውናሉ። ቀናቸው በሥራ ስለሚዋጥ ከምሽት ውጪ ክፍተት አያገኙም። ምሽት ላይ ከመተኛት ይልቅ ጊዜ በማጣት ሳቢያ ያልሠሩትን ነገር ያገባድዳሉ።
ጋዜጠኛዋ ዳፊን ኪ ሊ "ቀናቸውን ባሻቸው መንገድ ማሳለፍ ያልቻሉ ሰዎች ማታ ከመጠን በላይ በማምሸት ለማካካስ ይሞክራሉ" ስትል ትዊተር ላይ ጽፋ ነበር።
ጽሑፉን ከ4,500 በላይ ሰዎች ወደውታል።
አንድ ሌላ ሰው ደግሞ "ቀኖቼ በኔ ሳይሆን በሌሎች ቁጥጥር ሥር ናቸው። ምሽቱ ግን የእኔ ነው" ሲል ጽፏል።
በእንግሊዘኛ 'revenge bedtime procrastination' ይባላል። የሥራ ጫና የሚበዛባቸው ሰዎች ለእንቅልፍ ጊዜ ሲያገኙ ከመተኛት ይልቅ የተለያየ ሥራ ይሠራሉ። መጽሐፍ ያነባሉ፣ ቲቪ ያያሉ፣ ከሰዎች ጋር ያወራሉ ወዘተ. . .
እንቅልፍን መበቀል እንደማለት ነው።
እንቅልፍ ለምን እምቢ ይለናል?
በቂ እንቅልፍ አለማግኘት የጤና ቀውስ ነው። እአአ 2019 ላይ በ12 አገሮች የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው ከ11,000 በላይ ሰዎች መተኛት ከሚገባቸው ሰዓት ባነሰ 6.8 ሰዓት ብቻ ይተኛሉ።
በየቀኑ በአማካይ ስምንት ሰዓት መተኛት ይመከራል።
አንዳንዶች መተኛት የማይችሉት ስለሚጨነቁ ወይም በዙሪያቸው ያሉ ነገሮች ስለሚረብሿቸው ነው። አብላጫውን ቁጥር የሚይዙ ሰዎች የማይተኙት ግን በሥራ ጫና ወይም በትምህርት ምክንያት ነው።
ቻይና የተሠራ ጥናት ከ1990ዎቹ ወዲህ የተወለዱ ሰዎች በአግባቡ እንደማይተኙ ያሳያል።
በተለይም በግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋሞች የሚሠሩ እምብዛም አይተኙም።
የ33 ዓመቷ ጉ ቢንግ የምትሠራው ዲጂታል ኤጀንሲ ውስጥ ነው። ከሌሊት ስምንት ሰዓት በፊት አትተኛም። እሷ ብቻ ሳትሆንም ጓደኞቿም ከእኩለ ሌሊት በኋላ ነው የሚተኙት።
ጉ ልተኛ ብትል እንኳን አምሽታ መሥራት ስላለባት መተኛት አትችልም። ለእንቅልፍ ጊዜ ስታገኝ ደግሞ የራሷን ሥራ መሥራት ስለምትጀምር ሳትተኛ ትቀራለች።
"ጊዜዬን መሥሪያ ቤቱ ቀምቶኛል። ያለኝ ጊዜ ከሥራ ውጪ ያለው ሰዓት ብቻ ነው። ስለዚህ እንቅልፍ ትቼ የተሰረቅኩትን ሰዓት አካክሳለሁ" ትላለች።
በሥራና በግል ሕይወት መካከል መስመር ጠፍቷል
በሼፈልድ ዩኒቨርስቲ የሥነ ልቦና መምህርቷ ሲያራ ኬሊ፤ በሥራ እና በግል ሕይወት መካከል ያለው መስመር እየጠፋ ነው ይላሉ።
አንድ ሰው ከሥራ ባልደረባው ጋር በማንኛውም ጊዜ ይነጋገራል። ይህ ግንኙነት ደግሞ ሥራና የግል ሕይወትን እያደበላለቀ ነው።
ሥራ ሲበዛ የመዝናኛ ጊዜን እንደሚቀንስ እሙን ነው። መዝናኛ ጊዜ ለማግኘት ብሎ እንቅልፍን መስዋዕት ማድረግ ግን ጤናማ እንዳልሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ዘለግ ላለ ጊዜ እንቅልፍ ማጣት ለተለያየ የአዕምሮ ህመም ያጋልጣል።
የሥነ ልቦና መምህርቷ ሲያራ ሰዎች መዝናኛ ሰዓት የግድ ማግኘት አለባቸው። የሥራ ጫና መዝናኛ ሰዓት ሲያሳጣቸው እንቅልፍ ትተው የሚዝናኑትም ለዚያ ነው።
"ሠራተኞች መንፈሳቸውን የሚያዝናኑበት መንገድ ሊያገኙ ይገባል" ሲሉ አሠሪዎች ጉዳዩን እንዲያስቡበት ይመክራሉ።
የሠራተኞች መብት ላይ የሚሠሩት የማኅበረሰብ ባለሙያ ሂውንግ ቹንግ፤ ሠራተኞች የእንቅልፍ እንዲሁም የመዝናኛ ሰዓት በሚያሳጣቸው መንገድ ሥራ ሊደራረብባቸው አይገባም ይላሉ።
ይህንን ማድረግም የቀጣሪዎች ኃላፊነት ነው።













