ኮሮናቫይረስ፡ የኦክስፎርድ-አስትራዜኔካ ክትባት በህጻናት ላይ ሊሞከር ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኦክስፎርድ-አስትራዜኔካ ክትባት በህጻናት ላይ ምን ያህል ውጤታማ ይሆናል የሚለውን ለማጣራት አዲስ የክትባት ሙከራ መጀመሩ ተገልጿል።
የመጀመሪያዎቹ ዙር የክትባት ሙከራዎች በያዝነው ወር መጨረሻ አካባቢ የሚጀመሩ ሲሆን በነዚህ ሙከራዎችም እስከ 300 የሚደርሱ በጎ ፈቃደኛ ህጻናት ይሳተፋሉ ተብሏል።
ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት ይህ ሙከራ እድሜያቸው ከ6 እስከ 17 የሆኑ ህጻናት የኦክስፎርድ-አስትራዜኔካ ክትባትን ከወሰዱ በኋላ ምን ያህል የመከላከል አቅማቸው ይጠነክራል የሚለውን ለማወቅ ወሳኝ ነው።
ይህ ክትባት ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በኮሮረናቫይረስ ምክንያት የሚከሰት ከፍተኛ ህመምን አልያም ሞትን ለመቀነስ ጥቅም ላይ እየዋለ ሲሆን የፋይዘር-ባዮንቴክ ክትባትም ቢሆን ለተመሳሳይ አገልግሎት ጥቅም ላይ እየዋለ ነው።
በህጻናቱ ላይ በሚደረገው ሙከራ እስከ 240 የሚደርሱት ተሳታፉዎች የኦክስፎርድ-አስትራዜኔካ ክትባትን እንዲወስዱ የሚደረግ ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ የማጅራት ገትር መድሀኒት በተመጠነ መልኩ እንዲወስዱ ይደረጋሉ ተብሏል።
የክትባት ሙከራው በሚደረግባቸው አራት ማዕከላት፤ ዩኒርሲቲ ኦፈ ኦክስፎርድ፣ ሴንት ጆርጅ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል፣ ለንደን፣ ሳውዝሀም[ፕተን ዩኒቨርሲቲተ ሆስፒታል እና ብሪስቶል የህጻናት ሆስፒታል አቅራቢያ የሚኖሩ በጎ ፈቃደኞች በቶሎ እንዲመዘገቡ ተጠይቀዋል።
ለመሳተፍ በጎ ፈቃደኛ የሆኑት ህጻናት ሙከራው ከመጀመሩ በፊት ግን ለይቶ ማቆያ መግባት ግዴታ እንደሆነ ተነግሯል።
በዩናይትድ ኪንግደም እስካሁን የኦክስፎርድ-አስትራዜኔካ ክትባትን ለህጻናት ለመስጠት ምንም የታሰበ ነገር እንደሌለ የተገለጸ ሲሆን ለጊዜው ግን እድሜያቸው ከ28 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች ብቻ ናቸው ክትባቱን እየወሰዱ የሚገኙት።
የፋይዘር-ባዮንቴክ ክትባት ደግሞ እድሜያቸው ከ16 ዓመት በላይ ለሆኑ ሰዎች ተፈቅዷል። በክትባቱ አሰጣጥ ስርአት መሰረት እድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎችና ህጻናት በጠና ቢታመሙ እንኳን ክትባቱ አይሰጣቸውም።
የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ እድሜያቸው ከ6 እስከ 17 ለሆኑ ህጻናት ክትባቱን መስጠት ምን አይነት አሉታዊና አዎንታዊ ተጽዕኖዎች እንደሚኖሩት ለማወቅ የሚደረገው ይህ ሙከራ የመጀመሪያው ይሁን እንጂ ከዚህ በኋላ በርካታ ሙከራዎች እንደሚደረጉ አስታውቋል።












