ሰዎችን ለማሰቃየት የተቀጠሩት የናዚ ዘመን ሴት ጥበቃዎች

ውሾቻቸውን ይዘው ደን ውስጥ ሲንሸራሸሩ ይታያል

የፎቶው ባለመብት, GEDENKSTÄTTE RAVENSBRÜCK

የምስሉ መግለጫ, ውሾቻቸውን ይዘው ደን ውስጥ ሲንሸራሸሩ ይታያል

እአአ በ1944 በጀርመን ጋዜጣ የወጣ ማስታወቂያ እንዲህ ይነበባል. . .

"በወታደራዊ ማዕከሉ የሚቀጠሩ ከ20 እስከ 40 እድሜ ክልል ያሉ ጤናማ ሴት ሠራተኞች እንፈልጋለን። ጥሩ ደመወዝ እንከፍላለን። በነጻ ማረፊያና ልብስ እናቀርባለን።"

ማስታወቂያው በግልጽ ያላስቀመጣቸው ሁለት ነጥቦች አሉ። አንደኛው ሠራተኞቹ የሚለብሱት የአዶልፍ ሒትለር የናዚ ፓርቲ የደንብ ልብስ መሆኑን ነው። ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ 'ወታደራዊ ማዕከል' የተባለው ሴቶች የታገቱበት የግዳጅ ማቆያ እንደሆነ ነው።

እነዚህ በሰሜን በርሊን የሚገኙ እስር ቤቶች ከተዘጉ ዓመታት ተቆጥረዋል። በአቅራቢያቸው የሚገኙ ስምንት ቅንጡ ቤቶች ግን አሁንም ድረስ አሉ።

እነዚህ ቤቶች የሴት ጥበቃዎች መኖሪያ ነበሩ። አንዳንዶቹ ጥበቃዎች ከልጆቻቸው ጋር ይኖሩ ነበር።

በዛ ዘመን ጥበቃ ከነበሩት አንዷ ከቤቱ ማዶ ያለውን ደን በማስታወስ "በሕይወቴ ጥሩ ጊዜ ያሳለፍኩበት ወቅት ነበር" ይላሉ።

በእርግጥ ከመኝታ ቤታቸው አሻግረው ሲመለከቱ እስረኞችን እና በጭስ ታፍነው የሚገደሉበትን የሰቆቃ ክፍል ይመለከታሉ።

ራቨንስበርክ የሚባለው ይህ ቦታ አሁን መታሰቢያ ሙዝየም ሆኗል። የሙዝየሙ ዳይሬክተር ዶ/ር አንድራ ገንሰት እንደሚሉትም፤ አብዛኞቹ ጎብኚዎች የሚጠይቁት ከወንዶች ይልቅ ስለ ሴት ሠራተኞች ነው።

"በርካታ ሰዎች ሴቶች ጨካኝ ሊሆኑ እንደሚችሉ አያስቡም" ይላሉ ዳይሬክተሯ።

አብዛኞቹ የተቀጠሩት ሴቶች ከድሀ ቤተሰብ የተገኙ፣ በልጅነታቸው ትምህርት ያቋረጡና ሌላ ሥራ መያዝ የማይችሉ ናቸው።

በግዳጅ ማቆያው ጥሩ ገንዘብ ይከፈላቸዋል። ማረፊያም ያገኛሉ።

ዶ/ር አንድራ እንደሚያስረዱት በዘመኑ በዚህ እስር ቤት መቀጠር የፋብሪካ ሠራተኛ ከመሆን የተሻለ ነበር።

አብዛኞቹ ሴቶች በናዚ የወጣት ሊግ የተመለመሉና በሒትለር ሐሳብ የሚያምኑ ናቸው።

"ማኅበረሰቡን ከጠላቶቹ በመከላከል በጎ ተግባር እንደፈጸሙ ያምኑ ነበር" ይላሉ ዳይሬክተሯ።

"እርጉም ሰዎች ናቸው"

አሁን ሙዝየም በሆነው ክፍል የሚታዩ ፎቶዎች የያኔ ወጣት ሴቶች በዘመነኛ ልብስና የጸጉር አሠራር ተውበው ያሳያሉ።

ብዙዎቹ በ20ዎቹ እድሜ ክልል ሲሆኑ፤ ቤታቸው ውስጥ እየሳቁና ተቃቅፈው ቡና ሲጠጡ፣ ኬክ ሲበሉ እንዲሁም ውሾቻቸውን ይዘው ደን ውስጥ ሲንሸራሸሩ ይታያል።

እነዚህ ሴቶች የናዚ ፓርቲ መለያ ልብስ ማድረጋቸውን ሲያስተውሉ የያዟቸው ውሾች ሰዎችን ለማሰቃየት ይውሉ እንደነበር ያስታውሳሉ።

በናዚ እስር ቤቶች ወደ 3,500 የሚጠጉ ሴት ጥበቃዎች ነበሩ።

ሥራቸውን በራቨንስበርክ ጀምረው ኋላ ላይ ግድያ ይፈጸምባቸው ወደነበሩት ካምፖች የተዘዋወሩ አሉ።

ጀርመናዊት የአይሁድ እምነት ተከታይ ሰልማ ቫን ደ ፔሬ 98 ዓመታቸው ነው። በናዚ እስር ቤት ታስረው ከነበሩ አንዷ ናቸው።

አሁን ለንደን የሚኖሩት አዛውንት ያንን ዘመንና የናዚ ሰዎችን ሲገልጹ "እርጉም ሰዎች ናቸው" ይላሉ።

"ሥራቸውን ይወዱት የነበረው ምናልባትም ኃያል እንደሆኑ ስለተሰማቸው ይሆናል። እስረኞቹ ላይ ጉልበታቸውን ያሳዩ ነበር። የተንገላቱ፣ የተደበደቡ እስረኞች ነበሩ" ሲሉ ሰቆቃውን ያስታውሳሉ።

ውሾቻቸውን ይዘው ደን ውስጥ ሲንሸራሸሩ ይታያል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሰልማ ያኔ በናዚ ተይዞ በነበረው ኔዘርላንድስ ስውር እንቅስቃሴ በማድረግ አይሁዳውያን ቤተሰቦችን ነጻ ለማውጣት ይለፉ ነበር።

በያዝነው ዓመት መባቻ ላይ ስለ ሕይወት ተሞክሯቸው የሚያትት "ማይ ኔም ኢዝ ሰልማ" የተባለ መጽሐፍ አሳትመዋል።

የሰልማ ወላጆችና እህታቸው የተገደሉት የናዚ ካምፕ ውስጥ ነው። በየዓመቱ ወደ ካምፑ እየሄዱ ቤተሰቦቻቸውን ይዘክራሉ። የተፈጸመው ግፍ እንደማይዘነጋም ያስባሉ።

ራቨንስበርክ የሴቶች ብቻ ከሆኑ የናዚ ካምፓች ትልቁ ነው። ከመላው አውሮፓ ወደ 120,000 ሴቶች ታስረውበታል።

አብዛኞቹ ናዚን የሚቃወሙ የንቅናቄ መሪዎች ነበሩ። አይሁዳውያን፣ የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪዎችና በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩም ይገኙበታል።

ቢያንስ 30,000 ሴቶች በካምፑ ተገድለዋል። በረሀብ የተቀጡ፣ በበሽታ የሞቱ፣ በሥራ እንግልት ሕይወታቸው ያለፈም ብዙ ናቸው።

እስረኞቹ በሴት ጥበቃዎች ስቃይ ይደርስባቸው፣ ይገደሉም ነበር። ጥበቃዎቹ ታሳሪዎቹን በሚያንቋሽሹ ቅጽል ስሞች ይጠሯቸዋልም።

"ምንም ስህተት አልሠራሁም"

እአአ በ1945 የናዚ የጦር ወንጀል ለፍርድ ቀርቦ ሳለ ኢርማ ግሬስ የተባለች ሴት በሰው ግድያ ተፈርዶባት በስቅላት ተቀጥታለች።

እንደሷ አይነት ሴቶች ጭካኔያቸውን በሚያጎላ ሁኔታ የፊልም ገጸ ባህሪ ሲሆኑ ተስተውሏል።

በሺዎች ከሚቆጠሩ የናዚ ጥበቃ ሴቶች በአግባቡ ለፍርድ የቀረቡት 77 ብቻ ነው። የተፈረደባቸው ደግሞ ጥቂቶች።

አንዳንዶቹ ስማቸውን ቀይረው፣ ከአካባቢው ርቀው፣ ትዳር መስርተው ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለዋል።

ሀርታ ቦቴ የተባለች ሰዎችን በማሰቃየት ተከስሳ ታስራ የነበረች ሴት በአደባባይ ንግግር አድርጋ በእንግሊዞች ይቅርታ ተደርጎላት ተለቅቃለች።

የታሰረችው ለውስን ጊዜ ነው። ከመሞቷ በፊት በተደረገላት ቃለ ምልልስ አንዳችም ጸጸት አላሳየችም ነበር።

"ምንም ስህተት አልሠራሁም። ችግሩ ቦታው የግዳጅ ማቆያ መሆኑ ነው። ባልቀጠርበት ኖሮ እኔ ራሴ እገባበት ነበር። ያ ደግሞ የኔ ስህተት አይደለም" ብላለች።

ቀድሞ የናዚ ካምፖች ጥበቃ የነበሩ ሰዎች ተመሳሳይ አመለካከት አላቸው።

ሆኖም ግን አማራጭ ስለሌላቸው የካምፑ ጥበቃ እንደሆኑ መናገራቸው ትክክለኛ መረጃ አይደለም። በካምፑ ሊቀጡ ካመለከቱ በኋላ ሥራው ምን እንደሆነ ሲነገራቸው ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው ሌላ ሥራ ለመፈለግ የወሰኑ አሉ።

ሥራውን አንቀጠርም ያሉ ሰዎች አንዳችም ቅጣት እንዳልተጣለባቸውም ታሪካዊ ሰነዶች ይጠቁማሉ።

ሰልማ ስለ ጥበቃዎቹ ሲጠየቁ "ክፉ ድርጊት የሚፈጽሙ ነገር ግን እንደማንኛውም ሰው ተራ ናቸው፤ እዚህ እንግሊዝ ውስጥ ወይም ሌላ ቦታም እንዲያ ያለ ድርጊት ቢፈቀድ ብዙ ሰዎች ሊሳተፉ ይችላሉ" ይላሉ።

ያኔ የተፈጸመው አሰቃቂ ድርጊት አሁን ላለንበት ዘመን ትምህርት እንደሚሆን ተስፋ ያደርጋሉ።

አንዳንድ ፊልሞች የናዚ የግዳጅ ማቆያ ጥበቃ ሴቶችን እንደ አውሬ ሲስሉ፤ ሌሎች ደግሞ እንደ ተጠቂ ያቀርቧቸዋል። እውነታው ግን እንደማንኛውም ሰው ያሉና የጭካኔ ተግባር የፈጸሙ ሴቶች መሆናቸው ነው።