ጀርመን 'በገዛ ፈቃድ ራስን የማጥፋት' ሕጓን አላላች

የፎቶው ባለመብት, EPA
ጀርመን ዛሬ ራስን በሐኪም ድጋፍና በገዛ ፈቃድ ማጥፋት የሚከለክለውን ሕጓን ሽራለች።
ሕጉ ላለፉት አምስት ዓመታት ሲሠራበት ቆይቷል።
የጀርመን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሰዎች ፈቃዳቸውን መከልከል ሕገ መንግሥታዊ አይደለም ሲል ውሳኔ አስተላልፏል።
በጀርመን በርካታ ሰዎች ተደራጅተው "በገዛ ፈቃድና በሐኪም እርዳታ ራስን ማጥፋት የሚከለክለው ሕግ ሊቀለበስ ይገባል ሲሉ ነበር። ፍርድ ቤትም ቅሬታቸውን ሰምቷል።
ጀርመን ይህን ከልካይ ሕግ ከአምስት ዓመት ከማውጣቷ በፊት በሐኪም የሚደገፍ ሕይወትን የማቋረጥ ውሳኔን ትፈቅድ ነበር። የንግድ መልክ ያለውና ራስን በሐኪም እርዳታ የማጥፋቱን ነገር ቆየት ብላ ነው ሕገ ወጥ ያደረገችው።
ይህን ተከትሎ በርካታ ጀርመናዊያን ከዚች ዓለም 'በሰላምና በጤና' ለመሰናበት ሲቆርጡ ወደ ጎረቤት ስዊዘርላንድና ኔዘርላንድ ለመጓዝ ይገደዱ ነበር።
በጀርመን ሕይወትን በማጥፋት ጉዳይ አማካሪ የነበሩ ማዕከሎች እስር በመፍራት ተዘግተው ቆይተዋል።
ቀደም ያለው ሕግ በቀጥታ ራስን በሐኪም እርዳታ ማጥፋትን ባይከለክልም በይበልጥ የሕይወት ጉዳይ የንግድ መልክ እንዳይዝ በሚል ራስን ከማጥፋት ጋር የሚያግዙ ተቋማትን የሚቀጣ አንቀጽ እንደነበር ተዘግቧል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"ራስን በሰላም ከዚች ምድር ለማሰናበት ሲፈልጉ እናግዝዎታለን" የሚል ንግዶችና የሕክምና ማዕከላትን በቀጥታ የሚከለክለው ሕግ በተዘዋዋሪ ራስን በሐኪም እርዳታም ቢሆን ማጥፋትን ወንጀል አድርጎት ቆይቷል።
በዚህ አሁን በተሻረው የወንጀለኛ ሕግ አንቀጽ ላይ "ማንኛውንም እገዛ ገንዘብ ለማግኘት ሲባል ማድረግ..." የሚል ስለተካተተበት ባለፉት አምስት ዓመታት ሐኪሞች ደንበኞቻቸውን ራሳቸውን እንዲያጠፉ ለማገዝ ሳያስችላቸው ቆይቷል።
በ80ዎቹ ተመሳሳይ ሕይወትን በሰላም የማሰናበት እርዳታ ሲሰጡ የቆዩት የሕክምና ሥነምግባር ጉዳዮች ተንታኝ ጊታ ኒውማን ለቢቢሲ እንደተናገሩት
በሐኪም እርዳታ የገዛ ነፍስን ማጥፋት ተባባሪዎችን በ5 ዓመት ያስቀጣ ነበር።
በሕክምና ስሙ 'ዩቴኒዚያ' የሚል ስም ያለው ይህ በሐኪም እርዳታና በገዛ ፈቃድ ንፍስን የማሰናበት ሂደት በብዙ የዓለም አገራት ወንጀል ነው። ሆኖም በአውሮፓ እነ ኔዜርላንድስ፣ ቤልጂየም፣ ሉክዘምበርግና ስዊዘርላንድ ሕጋዊ አድርገውታል።
ኔዘርላንድስ ቤልጂየምና ሉክዘምበርግ ድርጊቱን የፈቀዱ ቢሆንም ጥብቅ ክትትል ያደርጉበታል።
ስዊዘርላንድ በበኩሏ ራሱን የሚያጠፋው ሰው ያን እንዲፈጽም የሚያደርገው ሐኪም ከራስ ወዳድነት ባልመነጨ ሁኔታ እስካገዘው ድረስ የሟችን መብት ታከብራለች።
ፖርቹጋል በቅርቡ ራስን በሐኪም እርዳታ የማሰናበትን ሁኔታ ትፈቅዳለች ተብሎ ይጠበቃል።
ጀርመን ራስን በሐኪም እርዳታ የማጥፋት ጉዳይ አነጋጋሪ የሆነው ከናዚ ታሪክ ጋር በመተሳሰሩ ነው። ናዚ የአካልና የአእምሮ ጉድለት የነበረባቸውን ሦስት መቶ ሺ ሰዎችን በተመሳሳይ መንገድ አሰናብቷል።












