ኮሮናቫይረስ ከአውሮፓ አገራት አልፎ አፍሪካዊት አገር አልጄሪያ ደረሰ

የፎቶው ባለመብት, AFP
ከጣሊያን ሳይዛመት አልቀረም የተባለው ኮረናቫይረስ በበርካታ አውሮፓውያን አገራት ሪፖርት እየተደረገ ነው።
ኦስትሪያ፣ ክሮኤሺያ፣ ስዊትዘርላንድ፣ ስፔን፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን ኮሮናቫይረስን ሪፖርት ያደረጉ አገራት ሲሆኑ፤ 'ወደ አገራችን የገባው ከጣሊያን በመጡ ሰዎች ነው' ብለዋል።
አፍሪካዊቷ አገር አልጄሪያም ከጣሊያን ኮሮናቫይረስ መዛመቱን አሳውቃለች።
ኑሮውን በብራዚል ያደረገው ግለሰብም ቫይረሱን ከጣሊያን ወደ መኖሪያ አገሩ በመውሰድ በላቲን አሜሪካ የመጀመሪያው ኮሮናቫይረስ ሊመዘገብ ችሏል።
በጣሊያን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 300 የደረሱ ሲሆን 11 ሰዎች በቫይረሱ ሞተዋል።
የጣሊያን ጎረቤት አገራት ከጣሊያን ጋር የሚያዋስናቸውን ድንበር ሊዘጉ ይችላሉ የሚል መላ ምት በስፋት ቢነገርም፤ የፈረንሳይ፣ ጀርመን እና የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ድንበርን ክፍት በማድረግ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ጥረት እንደሚያደርግ አሳውቀዋል።
በቁጥር ከፍ ያሉ የአውሮፓ አገራት ወደ ጣሊያን ሲጓዙ መውሰድ ስላለባቸው ቅድመ ጥንቃቄዎች ዜጎቻቸውን እያስጠነቀቁ ይገኛሉ።
በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሊካሄዱ ቀጠሮ ተይዞላቸው የነበሩ የጣሊያን እግር ኳስ ጨዋታዎች በዝግ ስታድየም እንዲካሄዱ ተወስኗል።

ከጣሊያን ወደ ብራዚል የተጓዘው የ61 ዓመት አዛውንት ቫይረሱ እንደተገኘበት ተረጋግጧል።
የሳኦ ፖሎ ነዋሪ የሆነው ግለሰብ፤ ወደ ብራዚል የተመለሰው ታዋቂው የብራዚል ካርኒቫል ዝግጅት እየተከናወነ በነበረበት ወቅት ነበር። ለካርኒቫል በዓል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ብራዚል እና ሳኦ ፖሎ ይተማሉ በዚህም ቫይረሱ ተሰራጭቶ ከሆነ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት እጅግ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ተነግሯል።
እስካሁን በአጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 78064 ሲሆን በቻይና ብቻ ወደ 2715 ሰዎች በቫይረሱ ሞተዋል።














