ኮሮናቫይረስ፡ደቡብ አፍሪካ በኮሮና ምክንያት ዘግታቸው የነበሩ ድንበሮቿን ልትከፍት ነው

በደቡብ አፍሪካና ሌሴቶ ያለች የድንበር ከተማ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

በኮሮና ክፉኛ ከተጠቁ የአፍሪካ አገራት መካከል ቀዳሚ ስፍራ የምትይዘው ደቡብ አፍሪካ ስርጭቱን ለመግታት ከወር በፊት ዘግታቸው የነበሩ ድንበሯቿን ልትከፍት መሆኑን አስታውቃለች።

በመጪው ሰኞም 20 የሚሆኑ የድንበር መስመሮቿን እንደምትከፍት ገልፃለች።

ይህ ውሳኔ የተላለፈው በትናንትናው ዕለት፣ የካቲት 6/ 2013 ዓ.ም በነበረ የምክር ቤቱ ስብሰባ ነው።

በዚህም መሰረት አገሪቷ ከዚምባብዌ፣ ቦትስዋና፣ ሞዛምቢክ፣ ናሚቢያ፣ ሌሴቶና እስዋቲኒ የሚያዋስኗትን የድንበር መስመሮች ክፍት ታደርጋለች።

ምንም እንኳን ድንበር ማቋረጥ የሚፈልጉ ሰዎች መስመሩ ክፍት እንደሆነ ቢነገራቸውም ነፃ የኮቪድ-19 ሰርቲፊኬት ማሳየት እንደ ቅድመ ሁኔታ መቀመጡን የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር አሮን ሞቶሳሌዲ ተናግረዋል።

ምርመራውም በቅርብ የተደረገ መሆን አለበት ተብሏል።

ሚኒስትሩ ራሳቸው እንቅስቃሴ የሚበዛባቸውን አራቱን መስመሮች እንደሚጎበኙና መንገደኞች እየተስተናገዱበት ያለውን ሂደት እከታተላለሁ ማለታቸው ተዘግቧል።

ደቡብ አፍሪካ ድንበሮቿን ለመዝጋት የተገደደችው አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ መገኘቱን ተከትሎ ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ በርካታ አገራት የደቡብ አፍሪካ ጉዞዎችን አግደዋል።

በደቡብ አፍሪካ አዲሱ የኮሮናቫይረስ ዝርያ ሁለተኛ ዙር አገርሽቶ ወረርሽኙ በከፍተኛ ሁኔታ ተዛምቷል።

በአገሪቷ እስካሁን ድረስ በወረርሽኙ 1.5 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ የ47 ሺህ ዜጎቿን ህይወት ደግሞ ተነጥቃለች። ይህም ከአፍሪካ በአንደኝነት ስፍራ ያስቀምጣታል።

በአሜሪካው የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ መረጃ መሰረት እስካሁን ድረስ በአለማችን 108 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 2.3 ሚሊዮኖች ደግሞ ሞተዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ

  • በፖላንድ በእንስሳት ቆዳ ላይ የኮሮናቫይረስ ዝርያ የተገኘ ሲሆን ወደ ሰውም እንዳይተላለፍ ተፈርቷል፤ ይህ ሁኔታ በቅርቡ በዴንማርክ እንደተከሰተ ተገልጿል።
  • ቻይና የኮሮናቫይረስን አመጣጥ እየመረመረ ላለው የአለም አቀፉ ጤና ድርጅት ቡድን ቁልፍ የሆኑ መረጃዎችን አሳልፌ አልሰጥም ማለቷን አንድ አባል ተናግረዋል።
  • በምጣኔ ኃብት ደከም ያሉ አገራት የኮሮናቫይረስ ክትባት የማያገኙ ከሆነ ወረርሽኙ ማብቂያ እንደሌለው ሳይንቲስቶች አስጠንቅቀዋል።