"ጀዋር መሐመድ እናቱ ሊጠይቁት ሄደው ሊያውቃቸው አልቻለም" ኦፌኮ

ጀዋር መሐመድ

የፎቶው ባለመብት, MAHEDER HAILESELASSIE TADESE

የምስሉ መግለጫ, ጀዋር መሐመድ

የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) በረሀብ አድማ ላይ የሚገኙት እነ አቶ ጀዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ አሐምዛ አዳነ እና አቶ ሸምሰዲን ጠሃ የጤና ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ ገልጾ መንግሥት "በአስቸኳይ ሕይወታቸውን አድኖ ግዴታውን ይወጣ" ሲል መግለጫ አውጥቷል።

"ለሚጠፋው የዜጎቻችንና አባሎቻችን ሕይወት መንግሥት ኃላፊነቱን ይወስዳል" በማለት ሕዝቡ እንዲሁም ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም መንግሥት ላይ ጫና እንዲያሳድርም ፓርቲው አሳስቧል።

የኦፌኮ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥሩነህ ገምታ የረሀብ አድማ ላይ የሚገኙት እስረኞች "ታመዋል። ከዚያም በላይ ሰው መለየት አይችሉም። መቆም አይችሉም። ሕይወታቸው አስጊ ደረጃ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ፊርማ በማሰባሰብ፣ አቤቱታ በማሰማት፣ ሰልፍ በማድረግ ወይም መንግሥታቸው በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና እንዲያሳድር በማድረግ የእስረኞቹን ሕይወት እንዲያድን ጠይቀዋል።

ያሳለፍነው ሰኞ፣ የካቲት 1/2013 ዓ.ም እስረኞቹን እንደጎበኟቸው የጠቀሱት አቶ ጥሩነህ፤ "ምንም ቃል ማውጣት አይችሉም። የሕክምና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል" ብለዋል።

አያይዘውም አቶ ጀዋር መሐመድን ሊጠይቋቸው የሄዱ እናታቸውን መለየት እንዳልቻሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

"ሰኞ እለት አይቻቸዋለሁ። ቃል ማውጣት አይችሉም። መቆም አይችሉም። ጀዋር መሐመድን እናቱ ሊጠይቁት ሄደው ሊለያቸው አልቻለም። ጀዋር መሬት ይዞ እየዳኸ ነው ወደ እስር ክፍሉ የሄደው። አልቅሼ ነው የተለየሁት" በማለት ሁኔታውን ገልጸዋል።

አቶ ጥሩነህ ዐቃቤ ሕግ፣ የሲቪል ማኅበራት፣ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶችና ሌሎችም አካላት እስር ቤት ሄደው እነ አቶ ጀዋርን እንዲያዩና መንግሥት ላይ ጫና እንዲያሳድሩም ጠይቀዋል።

"በኢትዮጵያ ታሪክም ጥቁር ነጥብ መሆኑን በመገንዘብ ለመንግሥት አስፈላጊውን ማስጠንቀቂያ ምክርም መስጠት ይችላሉ" ብለዋል።

የኦፌኮ አባላት በጅማ፣ በምዕራብ አርሲ ዞን፣ በምዕራብ ወለጋ፣ በምሥራቅ ወለጋ እና በሌሎችም የኦሮሚያ አካባቢዎች በተደጋጋሚ እንደሚታሰሩ፣ ታስረውም ፍርድ ቤት ያልቀረቡ እንዲሁም እንግልት የደረሰባቸው እንዳሉ ተናግረዋል።

"ከሕግ አግባብ ውጪ የታሰሩ አባሎቻችንና ሌላው ሕዝብም መታሰሩ ያሳስበናል። ነገሮች ካልተሻሻሉ በሚደርስብን ጫና፣በግድያና በማስፈራሪያው ሳቢያ ኦፌኮ ሊዳረከም ሊፈርስም ይችላል" ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

እነ አቶ ጀዋር በረሃብ አድማ ላይ ለረዥም ቀናት በመቆየታቸው የተነሳ የጤና ችግር እየተስተዋለባቸው መሆኑን የጤና ክትትል ከሚያደርጉላቸው ሐኪሞች መካከል አንዷ የሆኑት ዶ/ር ኢሊሊ ጀማል ለቢቢሲ መግለጻቸው አይዘነጋም።

የረሃብ አድማውን እያደረጉ ያሉት በፖለቲከኞች ላይ የሚደርሰውን እንግልት እና እስር፣ እነሱን ለመጠየቅና የችሎት ሂደታቸውን ለመከታተል ወደ ፍርድ ቤት በሚሄዱ ሰዎች ላይ የሚፈጸም እስር እና ወከባ እንዲቆም ለመጠየቅ እንደሆነና ከ15 ቀናት በላይ እንዳለፋቸው ቢቢሲ ከጠበቆቻቸው ለመረዳት ችሏል።

እነ አቶ ጃዋር እና አቶ በቀለን ጨምሮ በርካታ ፖለቲከኞች የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ ከተፈጠረው ሁከት ጋር ተያይዞ እጃችሁ አለበት ተብለው ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የሚታወስ ነው።

ከቀረቡባቸው ተደራራቢ አስር ክሶች መካከል ስድስቱ እንዲቋረጡ ፍርድ ቤት ጥር ወር ላይ መወሰኑ ይታወሳል።

የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ፣ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል አዋጅ፣ የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ የመተላለፍ ክሶች ከተመሰረቱባቸው ክሶች መካከል ሲሆኑ፤ እንዲቋረጡ የተደረጉት ክሶች የጦር መሣሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ 1177/2021 የተያያዙ ሲሆኑ በወቅቱ ውሳኔ እንዲቋረጡ የተደረጉት ክሶች የጦር መሳሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ 1177/2021 የተያያዙ መሆናቸውም የሚታወስ ነው።

የቀሩት አራት ክሶች "በ1996 የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀፅ 240 በመተላለፍ ብሔርን እና ሐይማኖትን መሰረት ያደረገ የእርስ በርስ ግጭት በመቀስቀስ አንዱ ወገን በሌላው ወገን ላይ እንዲነሳሳ በማድረግ"፣ የፀረ ሽብር አዋጅ 1176/2012 እና የቴሌኮም ማጭበርበር አዋጅን 7061/2004 የሚመለከቱ ናቸው።