ጃዋር መሐመድ፡ በቢጫ ለባሾቹ ምክንያት የእነ ጃዋር ችሎት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠበት

ጀዋር መሐመድ

የፎቶው ባለመብት, MAHEDER HAILESELASSIE TADESE

የምስሉ መግለጫ, ጀዋር መሐመድ

ቢጫ ቀለም ልብስ በለበሱ ግለሰቦች ምክንያት የእነ አቶ ጃዋር መሐመድ የዛሬ ችሎት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠበት።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የፀረ ሽብርና ሕገመንግሥታዊ አንደኛ ችሎት ዛሬ ማለዳ የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሊቀበል ቀጠሮ ይዞ ነበር።

ይህን ተከትሎ አቶ ጃዋር መሐመድ እና በቀለ ገርባን ጨምሮ በዚህ የክስ መዝገብ የተከሰሱ ተከሳሾች ፍርድ ቤትየቀረቡ ቢሆንም ችሎቱ ግን ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት አሰናብቷቸዋል።

ይሀህ ሊሆን ቻለው የፍርድ ሂደቱን ለመከታተል ቢጫ ልብስ ለብሰው በፍርድ ቤት የተገኙ ሰዎች ወደ ፍርድ ቤቱ እንዳይገቡ በፖሊስ መከልከላቸውን ተከትሎ ተከሳሾች እና ጠበቆች ባሰሙት አቤቱታ ነው።

ከተከሳሾች መካከል አቶ ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ እና ሐምዛ አዳነ ሰዎች ቢጫ ቀለም ያለው ልብስ በመልበሳቸው ወደ ፍርድ ቤት እንዳይገቡ መደረጉ አግባብ አይደለም፤ ቢጫ ልብስ በመልበሳቸው ብቻ ለእስር የተዳረጉ አሉ ሲሉ ቅሬታቸውን ለፍርድ ቤት አቅርበዋል።

ባለ ቢጫ ቀለም ልብስ የመልበስ ዘመቻ

ከሰሞኑ በማሕበራዊ ሚዲያዎች ላይ በርካቶች ቢጫ ልብስ የመልበስ ዘመቻ ሲያከናውኑ ቆይተዋል። ይህም ተከሳሾች በማረሚያ ቤት እና ፍርድ ቤት ሲቀርቡ የሚለብሱትን ባለ ቢጫ ቀለም ቱታ ለመወከል ነው።

ተከሳሾች ፍርድ ቤት ሲቀርቡ፤ ለተከሳሾች የሞራል ድጋፍ ለመስጠት ቢጫ ቀለም ያላቸውን ልብሶች በመልበስ በፍርድ ቤት እንደሚገኙ የዘመቻው አካል የሆኑት ይናገራሉ።

ባለፉት ሁለት ቀጠሮዎች በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ የክስ መዝገብ ሥራ የተከሰሱ ተከሳሾች ፍርድ ቤት በቀረቡብት ወቅት ቢጫ ቀለም ያለው ልብስ ለብሳ ከፍርድ ቤት የተገኘችው መሠረት ዳባ፤ ይህ ዘመቻችንን ለተከሳሾች የሞራል ብርታትን ለመስጠት ነው ትላለች።

"እነሱ ከሚለብሱት የልብስ ቀለም ጋር ተመሳሳይ ልብስ በመልበስ 'እኛም ከእናንተ ጋር ነን'፣ 'ከእናንተ ጋር ታስረናል' የሚል መልዕክት ማስተላለፍ ፈልገን ነው" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

ባለ ቢጫ ቀለም ልብስ የመልበስ ዘመቻ አስተባባሪ የሆነው ወቢ ቡርቃሳ የጀመሩት ዘመቻ በርካቶችን በማሳተፍ ከታሰበው በላይ ብዙ ሰዎች ጋር መድረሱን ይናገራል።

በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ #oromoyellowmovement የሚል መሪ ቃል ሲጠቀሙ ቆይተዋል።

ቢጫ ቀለም ያለው ልብስ የለበሱ ወጣቶች

የፎቶው ባለመብት, WABI BURKA

1px transparent line

በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ ላይ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ የቤተሰብ አባላቶቻቸው እና ሌሎች ሰዎች በለበሱት የልብስ ቀለም ሳቢያ ወደ ፍርድ ቤት እንዳይገቡ መደረጋቸውን እና ለእስር መዳረጋቸውን በመጥቀስ፤ በዚህ ምክንያት ሰዎች ወደ ፍርድ ቤት እንዳይገቡ ተደርጎ ባሉበት ሁኔታ ምንም ዓይነት አስተያየት መስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል።

አቶ በቀለ ገርባ እና አቶ ሐመዛ አዳነ ሰዎች ወደ ፍርድ ቤት እንዳይገቡ መከልከላቸው እንዳሳዘናቸው እና ቢጫ በመልበሳቸው የታሰሩት ይፈቱ ሲሉ ጠይቀዋል።

የተከሳሾች ጠበቆችም ችሎቱ ለሕዝብ ክፍት ሆኖ ሳለ ሰዎች በለበሱት የልብስ ቀለም ሳቢያ ወደ ችሎት እንዳይገቡ መከልከላቸው አግባብ አይደለም በማለት የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጥ ፍርድ ቤቱን ጠይዋል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ሌላ ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠት የፍርድ ሂደቱን ያጓትታል ሲል ተከራክሯል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ለመስማት ለጥር 27፣ 2013 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ ሰዎች በለበሱት የልብስ ቀለም ፍርድ ቤት እንዳይገቡ መደረጉ አግባብ አይደለም ያለ ሲሆን፤ ታዳሚዎች በሙሉ ግን ቢጫ ቀለም ያለው ልብስ ለብሰው በፍርድ ቤት የሚገኙ ከሆነ በችሎቱ ላይ ጫና ሊፈጥር እንደሚችል ከግምት ማስገባት አለበት ብሏል።

በሰኔ ወር፣ 2012 ዓ.ም ከሙዚቀኛው ሃጫሉ ግድያ በኋላ በቁጥጥር ሥር የዋሉት አቶ ጃዋር መሐመድና በክስ መዝገባቸው ውስጥ የሚገኙ ሌሎች 24 ሰዎች ተደራራቢ አስር ክሶች እንደተመሰረተባቸው ይታወሳል።

በእነ አቶ ጃዋር መሃመድ ከቀረቡ ተደራራቢ አስር ክሶች ስድስቱ እንዲቋረጡ ፍርድ ቤት ጥር 14/2013 ዓ.ም ውሳኔ አስተላልፏል።

አቶ ደጀኔ ጉተማ፣ ዶ/ር ብርሃነ መስቀል አበበና ፀጋዬ ረጋሳ አገር ውስጥ የሌሉና በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ መዝገብ ውስጥ ከተከሰሱት መካከል ናቸው።

የድምጻዊ ሃጫሉ ግድያን ተከትሎ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ተከስቶ ከነበረ ሁከት ጋር ተያይዞ ነበር እነ አቶ ጃዋር መሐመድ በቁጥጥር ሥር የዋሉት።