በትግራይ ክልል ዳግም የስልክ ግንኙነት ለምን ተቋረጠ?

የፎቶው ባለመብት, Ethiotelecom
በመቀሌ እና አዲሽሁ ከተማ መካከል የሚገኝ ፋይበር በመቆረጡ ምክንያት ከትናንት ተሲያት ጀምሮ በትግራይ ክልል የስልክ አገልግሎት መቋረጡን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጸዓሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ ለቢቢሲ አረጋገጡ።
ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ የስልክ አገልግሎት የተቋረጠው ከትናንትና ማምሻ ጀምሮ መሆኑን ገልፀው ወደ ሥፍራው ባለሙያዎችን መላካቸውንና የጥገና ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል።
የፋይበር መቋረጡ ያጋጠመው በመቀሌ እና አዲሽሁ ከተማ መካከል የሚገኝ መሆኑን ገለልፀው፣ በአሁኑ ሰዓት በመቀሌ እንዲሁም ሌሎች አቅራብያ አካባቢዎች ያሉ ቡድኖች ገብተው ጥገና እያደረጉ መሆኑን ገልፀዋል።
"በአሁኑ ሰዓት ሶስት ቡድን በጥገናው ላይ ተሰማርቷል" ያሉት ኃላፊዋ በትግራይ ክልል በደረሰው ውድመት የተጎዱ የስልክ መስመሮች ላይ በሚካሄደው ጥገና "ፕሮቴክሽን እና ሪስቶሬሸን ሲስተም ላይ ያሉት በሙሉ ተጠግነው ባለማለቃቸው" አሁን ይህ ጉዳት ሲደርስ በፍጥነት ማገናኘት አለመቻሉን አስታውቀዋል።
ፋይበሩ የተቆረጠው በተፈጥሮ ምክንያት አልያም ሆን ተብሎ በሰው መሆኑን ገና አለማወቃቸውን የገለፁት ኃላፊዋ በቦታው የሚገኘው የባለሙያዎች ቡድን ጥገና እያካሄደ መሆኑን ጨምረው አክለዋል።
በመቀሌ ከተማ ከትናንት ማምሻውን ጀምሮ የስልክ አገልግሎት ተቋርጦ የነበረ ሲሆን የድርጅቱ ኃላፊ ለቢቢሲ እንዳረጋገጡት ዛሬ ረቡዕ በሰዓታት ውስጥ ጥገና ተደርጎ ይመለሳል ብለዋል።
በትግራይ ክልል የሕወሓት ኃይሎች በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መክፈታቸው ከተገለፀ በኋላ መንግሥት "የሕግ የማስከበር" እርምጃ መውሰዱን ተከትሎ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጦ መቆየቱ ይታወሳል።
ከሁለት ወራት በፊት በክልሉ በተከሰተው ወታደራዊ ግጭት ሳቢያ ተቋርጠው የነበሩት የመብራት፣ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎቶች በከፊል የተመለሱባቸው አካባቢዎች ቢኖሩም፤ በበርካታ ከተሞች ውስጥ እስካሁን ስልክም ሆነ ኢንተርኔት አለመመለሳቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ በአንድ ወቅት ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
አገልግሎቶቹን መልሶ በቶሎ ለማስጀመር ያልተቻለው በመሠረተ ልማቶቹ ላይ "የደረሰው ውድመት በጣም ከፍተኛ" የሚባል በመሆኑ እንደሆነ በወቅቱ አስረድተዋል።
በመቀሌ የብሮድባንድና የድምፅ አገልግሎት መጀመሩን፣ ከጥር 10 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ውቅሮ፣ እደጋ ሐሙስ፣ አዲግራትና ነጃሺ አካባቢ የድምፅ አገልግሎት በተወሰነ ደረጃ ማግኘት መጀመራቸው ድርጅቱ ገልጾ እንደነበር ይታወሳል።
ነገር ግን በስልክ መስመሮች ላይ የደረሰውን ውድመት ምትክ መሣሪያዎችን አግኝቶና በየከተሞቹ በነፃነት ተንቀሳቅሶ ጥገናዎችን ማድረግ እንደተለመደው ቀላል አለመሆኑን በወቅቱ ለቢቢሲ ገልፀው ነበር።
በትግራይ ክልል የተፈጠረው የአገልግሎት መቋረጥ በድርጅቱ ችግር አለመሆኑን ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት የገለፁት ኃላፊዋ፣ በክልሉ ውድመቱ በማን፣ መቼና እንዴት እንደ ደረሰ በጉዳዩ ላይ ምርመራ ያደረገው የፌዴራል ወንጀል ምርመራ ቡድን በቅርቡ ውጤቱን ለሕዝብ ይፋ ያደርጓል ብለው ነበር።
ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ በትግራይ ክልል የደረሰው የቴሌኮም ውድመት ጥገና በአጭር ጊዜ እንደማይጠናቀቅ በድጋሚ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።












