የእነ አቶ ጃዋር መሐመድ የጤና ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ሃኪማቸው ገለፁ

በቀለ ገርባ፣ ጃዋር መሐመድ

የፎቶው ባለመብት, Yadi Pictures, BBC, Hamza Borena FAcebook

እነ ጃዋር መሐመድ በረሃብ አድማ ላይ ለረዥም ቀናት በመቆየታቸው የተነሳ የጤና ችግር እየተስተዋለባቸው መሆኑን የጤና ክትትል ከሚያደርጉላቸው ሐኪሞች መካከል አንዷ የሆኑት ዶ/ር ኢሊሊ ጀማል ለቢቢሲ ገለፁ።

ከድምጻዊ ሃጫሉ ግድያ በኋላ በቁጥጥር ስር የዋሉት እና ክስ ተመስርቶባቸው በእስር የሚገኙት እነ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ፣ ሸምሰዲን ጠሃ እና ሃምዛ አዳነ በፖለቲከኞች እና በቤተሰብ አባላቶቻቸው ላይ የሚደርሰውን እስር እና ወከባ በመቃወም የረሃብ አድማ ማድረግ ከጀመሩ ከ13ት ቀናት በላይ እንዳስቆጠሩ ጠበቆቻቸው ይናገራሉ።

ጃዋር እና ሌሎች በረሃብ አድማ ላይ የሚገኙ እስረኞችን የጤና ሁኔታ የሚከታተሉት ዶ/ር ኢሊሊ ጀማል፣ እስከ ማክሰኞ ድረስ ክትትል ሲያደርጉላቸው እንደነበር ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ነገር ግን ረቡዕ ዕለት የተለመደውን ሕክምና ለመስጠት ወደ ማረሚያ ቤቱ ቢያመሩም "ባላወቅኩት መንገድ በር ላይ ማዘግየቶችና ማመላለሶች ሲኖሩ ማግኘት አቅቶን ወጥተናል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እነ አቶ ጃዋር መሐመድ የረሃብ አድማውን እያደረጉ ያሉት በፖለቲከኞች ላይ የሚደርሰውን እንግልት እና እስር፣ እነሱን ለመጠየቅና የችሎት ሂደታቸውን ለመከታተል ወደ ፍርድ ቤት በሚመጡ ሰዎች ላይ የሚፈጸም እስር እና ወከባ እንዲቆም ለመጠየቅ እንደሆነም ቢቢሲ ከጠበቆቻቸው ለመረዳት ችሏል።

እነ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ፣ ሸምሰዲን ጠሃ እና ሃምዛ አዳነ በተጨማሪ በአቶ ጃዋር መሐመድ የክስ መዝገብ ሥር የሚገኙት የአቶ ጃዋር መሐመድ ጠባቂዎች እና የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋዜጠኛ መለሰ ዲሪብሳ የረሃብ አድማውን መቀላቀላቸው ይታወሳል።

እነ አቶ ጃዋር መሐመድ እና በቀለ ገርባን ጨምሮ በርካታ ፖለቲከኞች የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ ከተፈጠረው ሁከት ጋር ተያይዞ እጃችሁ አለበት ተብለው ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የሚታወስ ነው።

ከእነ አቶ ጃዋር በተጨማሪ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከፍተኛ አመራሮች በተመሳሳይ የረሃብ አድማ ላይ እንደሚገኙ የተገለፀ ሲሆን አቶ ሚካኤል ቦረን እና ኬነሳ አያና ፍርድ ቤት የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ጉዳያቸው ከውጪ ሆነው እንዲከታተሉ ቢፈቅድላቸውም ፖሊስ እስረኞቹን አልለቅም በማለቱ የረሃብ አድማ ላይ እንደሚገኙ ጠበቃቸው አቶ ቱሊ ባይሳ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የጤንነታቸው ሁኔታ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?

ዶ/ር ኢሊሊ እነ አቶ ጃዋር ያሉበትን የጤና ሁኔታ ለቢቢሲ ሲያስረዱ "የመድከም፣ አቅም የማጣት. . . ሰውነታቸው ላይ መጎሳቆል" በጉልህ ይታያል ብለዋል።

በየዕለቱ ደም በመውሰድ ምርመራዎችን እንደሚያደርጉ የገለፁት ዶ/ር ኢሊሊ የስኳር መጠናቸው ከሚገባው በታች መውረዱን ማረጋገጣቸውን ይገልጻሉ።

አቶ ሸምሰዲን ጠሃ ከሁሉም በተለየ የስኳር መጠናቸው በጣም በመውረዱ፣ ሆስፒታል ገብተው የህክምና ክትትል እንዲያደርጉ መደረጉንም ጨምረው አስረድተዋል።

እነ አቶ በቀለ ገርባም ሆኑ ሌሎች ደም ግፊት ስላለባቸው የኩላሊታቸው ሁኔታ ላይ ምርመራ መደረጉን የገለፁት ዶ/ር ኢሊሊ በዚህም ከረሃብ አድማው በኋላ የተፈጠሩ የኩላሊት መጎዳቶች መስተዋላቸውን ገልፀዋል።

በረሃብ አድማ ውስጥ ያሉት ታሳሪዎች በአጠቃላይ ለረዥም ቀናት ምግብ ባለመመገብ የተነሳ የሚመጡ ችግሮች በሽንታቸው እና በደማቸው ውስጥ መስተዋሉን ዶ/ር ኢሊሊ ጨምረው አስረድተዋል።

አቶ ጃዋር በረሃብ አድማው የመጀመሪያ ቀናት ላይ ውሃ ሳይወስድ በመቅረቱ ኩላሊቱ ላይ ጉዳት መስተዋሉን ገልፀዋል።

ዶ/ር ኢሊሊ በየዕለቱ በረሃብ አድማ ላይ ከሚገኙት በሙሉ ደምና ሽንት ናሙና በመውሰድና በመመርመር ውጤታቸውን በማየት ሰውነታቸው ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ምን እንደሆነ እንደሚነግሯቸው ገልፀው፣ እነርሱ 'የሚመጣውን ነገር እናውቃለን፤ ነገር ግን ወስነን ነው እያደረግን ያለነው' ማለታቸውን ገልፀዋል።

ሰውነታቸው ላይ ከደረሰው ጉዳት አንጻር ሆስፒታል ተኝቶ መታከም ያስፈልጋቸው ነበር ያሉት ዶ/ር ኢሊሊ፣ ነገር ግን ተከሳሾቹ 'አንፈልግም' ማለታቸውን ተናግረዋል።

እነ አቶ ጃዋር አሁን እያደረጉ ያሉት ሙሉ የረሃብ አድማ መሆኑን የገለፁት ዶ/ር ኢሊሊ፣ ምግብ ሳይወስዱ በመቅረታቸው ውሃ የመውሰድ ፍላጎታቸውም መቀነሱንና ይህም የተለያዩ የጤና እክሎች እንዲታይ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል።

ከ13 ቀናት በላይ በረሃብ አድማ ላይ የሚገኙት እነ አቶ ጃዋር መሐመድ የረሃብ አድማውን እንዲያቆሙ በትናንትናው ዕለት በሃይማኖት አባቶች እና ፖለቲከኞች ቢጠየቁም ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የረሃብ አድማው ተከሳሾችን የከፋ አደጋ ላይ እንዳይጥል የቅርብ ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ መግለጻቸውን ኮሚሽኑ ባሳለፍነው አርብ ባወጣው መግለጫ አስነብቧል።

"ለታሳሪዎች ምክንያታዊ የሆኑ ጥያቄዎች ተገቢውን አፋጣኝ ምላሽ መስጠትና የእስረኞችን ጠያቂዎች በማረሚያ ቤቱም ሆነ በፍርድ ቤቶች በአግባቡ ማስተናገድ ይገባል" ስለማለታቸው በመግለጫው ሰፍሯል።

የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በቁጥጥር ሥር የዋሉት እነ አቶ ጃዋር ከቀረቡባቸው ተደራራቢ አስር ክሶች ስድስቱ እንዲቋረጡ ፍርድ መወሰኑ ይታወሳል።

የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ፤ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል አዋጅ፤ የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ የመተላለፍ ክሶች ከተመሰረቱባቸው ክሶች መካከል ሲሆኑ፤ እንዲቋረጡ የተደረጉት ክሶች የጦር መሳሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ 1177/2021 ጋር የተያያዙ ናቸው።