እነ አቶ ጃዋር መሐመድ የረሃብ አድማ ማድረግ ከጀመሩ ስድስት ቀናት እንዳለፋቸው ተነገረ

ጀዋር መሐመድ

የፎቶው ባለመብት, MAHEDER HAILESELASSIE TADESE

የምስሉ መግለጫ, ጀዋር መሐመድ

ፖለቲከኞቹ አቶ ጀዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ሐምዛ አዳነ እና አቶ ሸምሰዲን ጠሃ የረሃብ አድማ ማድረግ ከጀመሩ 6 ቀናት እንዳለፋቸው ከጠበቆቻቸው መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ቱሊ ባይሳ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

እንደ አቶ ቱሊ ከሆነ ደንበኞቻቸው የረሃብ አድማ እያደረጉ ያሉት የፖለቲከኞችን እስር እና በመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚደርሰውን ጫና በመቃወም ነው።

ጠበቃው ቱሊ ባይሳ ፖለቲከኞቹ እያደረጉት ያሉት የረሃብ አድማ እንዳደከማቸው ገልጸው፤ ደንበኞቻቸው ለማነጋገር በሄዱበት ወቅት ወጥተው ሊያነጋግሯቸው ስላልቻሉ "ተኝተው ባሉበት" ለማነጋገር ተገድደናል ሲሉ ለቢቢሲ ደንበኞቻቸው ያሉበትን ሁኔታ አብራርተዋል።

ትናንት (ማክሰኞ ጥር 25) ደንበኞቻቸውን ሄደው ማነጋገራቸውን የሚያስረዱት አቶ ቱሊ፤ "የረሃብ አድማ ከጀመሩ ስድስተኛ ቀናቸው ነው። ከዚህ ቀደም ልንጠይቃቸው ስንሄድ መጠየቂያ ስፍራ ጋር መጥተው ነበር የሚያነጋግሩን። አሁን ግን ወደ እዛ እንኳን መጥተው ሊያነጋግሩን ስላልቻሉ በተኙበት ቦታ ሄደን ነው ያነጋገርናቸው። ድምጻቸውም፤ ሰውነታቸውም ተዳክሟል" ሲሉ ተናግረዋል።

የታሰሪ ቤተሰቦችም ተከሳሾቹ እያካሄዱ ባሉት የረሃብ አድማ መዳከማቸውን ይናገራሉ።

የአቶ ጃዋር መሐመድ እህት የሆነችው ራቢያ ሲራጅ፤ ትናንት እነ አቶ ጃዋርን ለመጎብኘት መሄዷን እና ያሉበትን ሁኔታ ከተመለከተች በኋላ መረበሿን ተናግራለች።

"በጣም ተዳክመዋል። 'ትግል ላይ ነው ያለነው አንበላም' አሉኝ። መቆም እንኳን አይችሉም። ያሉበትን ሁኔታ ማየት አቅቶኝ ወጣሁኝ" ስትል ተናግራለች።

አቶ ቱሊ እንደሚሉት ደንበኞቻቸው የሕክምና አገልግሎት ካስፈለገን በመረጥነው የሕክምና ስፍራ አገልግሎት ይሰጠን ማለታቸውን ተከትሎ የደንበኞቻቸውን አቤቱታ ተቀብለው ለማረሚያ ቤቱ አስተዳደር ማመልከቻ አስገብተው መውጣታቸውን ተናግረዋል።

ይህንን የጠበቃውን መረጃ በተመለከተ የማረሚያ ቤቶች አስተዳደርን ተጨማሪ መረጃ እንዲሰጠን ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፡፡

የረሃብ አድማ ለምን?

እንደ ጠበቆቻቸው ገለፃ ከሆነ እን አቶ ጃዋር የረሃብ አድማ እያደረጉ ያሉት የፖለቲከኞችን እስር እና በመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚደርሰውን ጫና በመቃወም ነው።

እነ አቶ ጃዋር መሐመድ እና በቀለ ገርባን ጨምሮ በርካታ ፖለቲከኞች የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ ከተፈጠረው ሁከት ጋር ተያይዞ እጃችሁ አለበት ተብለው ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የሚታወስ ነው።

"የዝነኛ ሰዎች ግድያን ተከትሎ ፖለቲከኞች ወደ እስር ቤት ተወረወሩ። መገናኛ ብዙኃኑም ተዘጉ። በርካታ የኦሮሞ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተሰረዙ። የቀሩት ደግሞ አመራሮቻቸው እንዲታሰሩ ተደርጓል" የሚል ቅሬታ ደንበኞቻቸው እንደሚያሰሙ ጠበቃው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ "በወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር የዋሉ ሰዎች በዋስ እንዲወጡ ፍርድ ቤት ቢያዝም፤ አይለቀቁም። ቢለቀቁም ተመልሰው ይታሰራሉ። ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ቢሮ ከፍተው ለምርጫ እንዲዘጋጁ ይደረጋል። በእኛ ላይ ግን ተቃራኒው ነው የሚፈጸመው" በሚል ምክንያት የረሃብ አድማ እያደረጉ እንደሆነ ጠበቃው ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ጠበቃው አቶ ቱሊ ባይሳ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በገላን ከተማ ታስረው የሚገኙት እና ደንበኞቻቸው የሆኑት የኦነግ ከፍተኛ አመራሮች በተመሳሳይ የረሃብ አድማ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

አቶ ሚካኤል ቦረን እና ኬነሳ አያና ፍርድ ቤት የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ጉዳያቸው ከውጪ ሆነው እንዲከታተሉ ቢፈቅድላቸውም ፖሊስ እስረኞቹን አልለቅም በማለቱ የረሃብ አድማ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፤ አቶ ቱሊ ባይሳ።

የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በቁጥጥር ሥር የዋሉት እነ አቶ ጃዋር ከቀረቡባቸው ተደራራቢ አስር ክሶች ስድስቱ እንዲቋረጡ ፍርድ መወሰኑ ይታወሳል።

የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ፤ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል አዋጅ ፤ የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ የመተላለፍ ክሶች ከተመሰረቱባቸው ክሶች መካከል ሲሆኑ፤ እንዲቋረጡ የተደረጉት ክሶች የጦር መሳሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ 1177/2021 ጋር የተያያዙ ናቸው።

የዛሬ ሳምንት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የፀረ ሽብርና ሕገመንግሥታዊ አንደኛ ችሎት የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃላቸውን ሊቀበል ቀጠሮ ይዞ የነበረ ቢሆንም ቢጫ ቀለም ልብስ በለበሱ ግለሰቦች ምክንያት ችሎት ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱ ይታወሳል።

የፍርድ ሂደቱን ለመከታተል ቢጫ ልብስ ለብሰው በፍርድ ቤት የተገኙ ሰዎች ወደ ፍርድ ቤቱ እንዳይገቡ በፖሊስ መከልከላቸውን ተከትሎ ተከሳሾች እና ጠበቆች ባሰሙት አቤቱታ ነው ተለዋጭ ቀጠሮ የተሰጠው።

በማሕበራዊ ሚዲያዎች ላይ በርካቶች ቢጫ ልብስ የመልበስ ዘመቻ ሲያከናውኑ ቆይተዋል። ይህም ተከሳሾች በማረሚያ ቤት እና ፍርድ ቤት ሲቀርቡ የሚለብሱትን ባለ ቢጫ ቀለም ቱታ ለመወከል ነው።

የእምነት ክህደት ቃል ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ የተሰጠባቸው ተከሳሾች ነገ ጥር 27፣ 2013 ፍርድ ቤት ይቀርባሉ።