እነ አቶ ጃዋር በረሃብ አድማ 11 ቀናት አስቆጥረዋል ፤ የረሃብ አድማ ምን ያሳካል?

በቀለ ገርባ፣ ጃዋር መሐመድ

የፎቶው ባለመብት, Yadi Pictures, BBC, Hamza Borena FAcebook

እነ አቶ ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ፣ ሐምዛ አዳነ እና ሸምሰዲን ጠሃ የረሃብ አድማ ማድረግ ከጀመሩ 11 ቀናት ማለፋቸውን የቤተሰብ አባላት እና ጠበቆቻቸው ለቢቢሲ ተናገሩ።

ከአራቱ ተከሳሾች በተጨማሪ በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ የክስ መዝገብ ሥር የሚገኙ ተከሳሾችም የረሃብ አድማውን እንደተቀላቀሉ ከእነ አቶ ጃዋር መሐመድ ጠበቆች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ምስጋኑ ሙለታ ተናግረዋል።

እነ አቶ ጃዋር መሐመድን ትናንት ጠዋት መጎብኘታቸውን የሚያስረዱት ጠበቃው፤ "ትናንት 11ኛ ቀናቸው ነበር። በጣም ተዳክመዋል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የአቶ በቀለ ገርባ ባለቤት ወ/ሮ ሃና ረጋሳ፤ እነ አቶ በቀለ አሁንም በረሃብ አድማ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ጠበቃው አቶ ሙለታ እንዳሉት ከአራቱ ተከሳሾች በተጨማሪም የረሃብ አድማውን በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ የክስ መዝገብ ሥር የሚገኙት የአቶ ጃዋር መሐመድ ጠባቂዎች እና የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋዜጠኛ መለሰ ዲሪብሳ ከተቀላቀሉ 6 ቀናት ማለፋቸውን ጨምረው ገልጸዋል።

የጋዜጠኛ መለሰ ዲሪብሳ ባለቤት ታደለች መርጋ ባለቤቷ የረሃብ አድማውን መቀላቀሉን እና ለመጠየቅ ይዛለት የምትሄደውን ምግብ አልቀበልም እያላት መሆኑን ገልጻለች።

"አንዳንዶቹ በሰው ድጋፍ ነው ከክፍላቸው የሚወጡት። በተለየ ደግሞ ዘግይተው የረሃብ አድማውን የተቀላቀሉት በጣም ከብዷቸዋል" ሲሉ ጠበቃው አቶ ሙለታ ተናግረዋል።

የእነ አቶ ጃዋር መሐመድ ሃኪሞች "ምርመራ ካደረጉላቸው በኋላ ውሃ ካልወሰዱ አንዳንድ የሰውነት አካላቸው ሥራ ሊያቆም እንደሚችል ከነገሯቸው በኋላ ነው በግድ ውሃ እየወሰዱ ያሉት። ምግብ የሚባል ነገር አፋቸው ጋር እየደረሰ አይደለም" ሲሉ ጠበቃው ለቢቢሲ አስረድተዋል።

የረሃብ አድማ ለምን?

እነ አቶ ጃዋር መሐመድ የረሃብ አድማውን እያደረጉ ያሉት በፖለቲከኞች ላይ የሚደርሰውን እንግልት እና እስር፣ እነሱን ለመጠየቅና የችሎት ሂደታቸውን ለመከታተል ወደ ፍርድ ቤት በሚመጡ ሰዎች ላይ የሚፈጸም እስር እና ወከባ እንዲቆም ለመጠየቅ ነው።

እነ አቶ ጃዋር መሐመድ እና በቀለ ገርባን ጨምሮ በርካታ ፖለቲከኞች የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ ከተፈጠረው ሁከት ጋር ተያይዞ እጃችሁ አለበት ተብለው ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የሚታወስ ነው።

ከእነ አቶ ጃዋር በተጨማሪ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከፍተኛ አመራሮች በተመሳሳይ የረሃብ አድማ ላይ ይገኛሉ። አቶ ሚካኤል ቦረን እና ኬነሳ አያና ፍርድ ቤት የዋስትና መብታቸው ተከብሮ ጉዳያቸው ከውጪ ሆነው እንዲከታተሉ ቢፈቅድላቸውም ፖሊስ እስረኞቹን አልለቅም በማለቱ የረሃብ አድማ ላይ እንደሚገኙ ጠበቃቸው አቶ ቱሊ ባይሳ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የረሃብ አድማው ተከሳሾችን የከፋ አደጋ ላይ እንዳይጥል የቅርብ ክትትል ማድረግ እንደሚያስፈልግ መግለጻቸውን ኮሚሽኑ ባሳለፍነው አርብ ባወጣው መግለጫ አስነብቧል።

"ለታሳሪዎች ምክንያታዊ የሆኑ ጥያቄዎች ተገቢውን አፋጣኝ ምላሽ መስጠትና የእስረኞችን ጠያቂዎች በማረሚያ ቤቱም ሆነ በፍርድ ቤቶች በአግባቡ ማስተናገድ ይገባል" ስለማለታቸው በመግለጫው ሰፍሯል።

ለመሆኑ የረሀብ አድማ ምን ያህል ውጤታማ ነው?

የረሀብ አድማ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞ ከሚገለጽባቸው መንገዶች አንዱ ነው። በተለያየ ምክንያት የረሀብ አድማ ያደረጉ ታዋቂ ግለሰቦች በታሪክ ውስጥ ስማቸው ተመዝግቧል።

ከአንድ የሕንድ ግዛት የተባረረ ንጉሥ ወንድሙን ለማስመለስ የረሀብ አድማ ስለማድረጉ በጥንታዊ የሕንድ ታሪክ መዛግብት ሰፍሯል።

አየርላንድ ክርስትናን ከመቀበሏ በፊት ረሀብ አንድ የሕግ ሥርዓቷ አካል ነበር። አንድ ሰው በደል ፈጽሞ፤ ተበዳዩ የበዳዩ ቤት በር ላይ ራሱን በረሀብ ከገደለ፤ በዳዩ ባለ እዳ ይሆናል።

የረሃብ አድማ የሚያደርጉ ሰዎች ለጥያቄያቸው መልስ የሚሰጣቸው አካል ላይ የሥነ ልቦና ጫና ለማሳደር ይሞክራሉ።

አንድ ሰው እየተራበ ነው የሚለው ዜና ሕዝብ ላይ የሚፈጥረው ስሜትም ለጥያቄዎች መልስ ለማግኘት አማራጭ መንገድ ነው።

እንግሊዝ ውስጥ ሴቶች በምርጫ እንዲሳተፉ የሚጠይቁ የመብት ተሟጋቾች የረሀብ አድማ ያደርጉ ነበር። በተለይም ማርዮን ደንሉፕ የተባለች ተሟጋች እአአ በ1909 ባደረገችው የረሀብ አድማ ትታወቃለች።

እራት ምን ትበያለሽ? ተብላ ስትጠየቅ "ቆራጥነቴን" ብላ የሰጠችው ምላሽ በታሪክ ታዋቂ ነው።

በረሀብ አድማ ከሚታወቁ መካከል በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱት ጋንዲ ናቸው። ስለ ረሀብ አድማ መጽሐፍ ያሳተሙት ፕ/ር ሻርማን አፕት ራሰል፤ የፓለቲካ ጥያቄን ለማስተጋባት የረሀብ አድማ ማድረግ ተቃውሞ ቢገጥመውም በ20ኛው ክፍለ ዘመን እንደ አዲስ አንሰራርቷል።

"በ20ኛው ክፍለ ዘመን ፍትሕን ለመጠየቅ ተመራጩ መንገድ የረሀብ አድማ ሆኗል" ይላሉ ፕ/ር ሻርማን።

የረሀብ አድማ ሰላማዊ ተቃውሞ በሚያሰሙ እንዲሁም ነውጥ የቀላቀለ ተቃውሞ በሚያካሂዱም ሰዎች ተተግብሯል።

ውጤታማ የሆነባቸው ወቅቶች እንዳሉ ሁሉ ሳይሳካ የቀረበትም ጊዜ አለ።

የረሀብ አድማ በማረሚያ ቤት

በኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ የማኅበረሰብ አጥኚው ማይክል ቢግስ እንደሚሉት፤ የረሀብ አድማ ውጤት ከታየባቸው የታሪክ ሁነቶች አንዱ አየርላንዶች የእንግሊዝን አገዛዝ የተቃወሙበት ወቅት ነው።

በወቅቱ አንድ ተቃዋሚ ምግብ እንዲበላ ሲገደድ ሞቷል። በረሀብ አድማው ሳቢያ የሞቱ ተቃዋሚዎችም ነበሩ።

የረሀብ አድማው በፍጥነት የመንግሥትን አቋም ማስለወጥ ባይችልም በሕዝቡ ዘንድ ንቅናቄ መፍጠር ችሏል።

በሰላማዊ ተቃውሞ የሚታወቀው ጋንዲ፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕንዳውያን የሱን የተቃውሞ መንገድ መከተላቸው ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት እንዲላቀቁ እንዳደረገ ያምናል።

የማኅበረሰብ አጥኚው እንደሚሉት፤ ማረሚያ ቤት ያሉ ሰዎች ተቃውሟቸውን መግለጽ የሚችሉት በረሀብ አድማ ነው።

"እስር ቤት ውስጥ ከረሀብ አድማ ውጪ መቃወሚያ መንገድ የለም። አንድ ሰው እስር ቤት ሳለ ለመኖሩም ይሁን ለመሞቱ ተጠያቂ መንግሥት ነው" ሲሉ ያብራራሉ።

በረሀብ አድማ ተቃውሞ ከገለጹ አንዱ የሆነው ቶሚ መኬርኒ እስረኞች ድምጻቸውን ለማሰማት የረሀብ አድማ ከማድረግ ውጪ አማራጭ እንደማይኖራቸው ያስረዳል።

የረሀብ አድማ ላይ ያለ ሰው ምን ያህል ጊዜ መቆየት ይችላል?

በአብዛኛው የረሀብ አድማ የሚያደርጉ ሰዎች ምግብ አቁመው ፈሳሽ እንደሚወስዱ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በመጀመሪያዎቹ ሦስት ቀናት ሰውነት ካለው ጉሉኮስ ኃይል በማግኘት ይንቀሳቀሳል። ከዚያም ኩላሊት የሰውነትን ስብ ማብላላት (ኬቶሲስ) እንደሚጀምር ሳይንሱ ይጠቁማል።

ሰውነት ከጥቂት ቀናት በኋላ ሙሉ በሙሉ ስለሚራብ ከጡንቻ፣ የአጥንት መቅኔና ከሌሎች የሰውነት ህዋሳት ኃይል ለማግኘት ይጣጣራል።

ይህ ደረጃ ለሕይወት አስጊ ነው።

ሳይንቲፊክ አሜሪካን በድረ ገጹ ባወጣው መረጃ መሠረት አንድ ሰው ያለ ምግብ ምን ያህል ጊዜ ይቆያል የሚለው በሰውነት ክብደት፣ በጤና ሁኔታ፣ በዘረ መል መዋቅር፣ ሰውየው/ሴትየዋ በሚያገኙት የፈሳሽ መጠን ይወሰናል።

ጋንዲ በ74 ዓመታቸው ለ21 ቀናት የረሀብ አድማ ሲያደርጉ ውሃ ብቻ ነበር የሚቀምሱት።

የብሪትሽ ሜዲካል ጆርናል ባለሙያዎችን ጠቅሶ እንዳስነበበው በረሀብ አድማ ለ28፣ ለ36፣ ለ38 እና ለ40 ቀን የቆዩ ሰዎችም አሉ።

እአአ በ1981 እንግሊዝን ይቃወሙ የነበሩ 10 የአየርላንድ እስረኞች ከ46 እስከ 73 ቀን የረሀብ አድማ ካደረጉ በኋላ ሕይወታቸው አልፏል።

በተለያየ ሁኔታ ውስጥ የረሀብ አድማ ያደረጉ ሰዎች ለተለያየ ጊዜ መቆየት እንደሚችሉ የሚጠቅሱት ባለሙያዎች፤ በአማካይ ያስቀመጡት 21 ቀናት መቆየት እንደሚቻል ነው።

በታሪክ ረዥም የተባለው የረሀብ አድማ 16 ዓመታት የወሰደ ነው። ሕንዳዊቷ ኢራም ሻሚላ ለሕንድ ወታደሮች ከፍተኛ ኃይል የሚሰጥ ሕግ በመቃወም ለ16 ዓመታት የረሀብ አድማ አድርጋ እአአ 2016 ላይ ነው ያቆመችው።

ሕንዳዊቷ ማረሚያ ቤት ሳለችና ሆስፒታል ገብታም በግዳጅ ምግብ እንድትወስድ እንደምትደረግ ተዘግቧል።