አፍሪካ በ2020 ኢንተርኔትን በማቋረጧ ብቻ 237.4 ሚሊዮን ዶላር አጥታለች

የፎቶው ባለመብት, AHS Photography - Alex Schregardus
ኢትዮጵያ በፈረንጆቹ 2020 ለ1536 ሰዓታት ወይም በቀናት ሲሰላ ለ64 ቀናት ያህል ኢንተርኔት ማቋረጧንና በዚህም የተነሳ 11̄1.3 ሚሊዮን ዶላር ማጣቷን አንድ ጥናት አመለከተ።
ጥናቱ የተሰራው የአገራትን ኢንተርኔት ፍሰትን በሚከታተለው ኔት ብሎክስ በተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት እንዲሁም የኢንተርኔት መብትን በሚያቀነቅነው 'ዘ ኢንተርኔት ሶሳይቲ' ጥምረት ነው።
ሪፖርቱ በዓለማችን ላይ የተከሰቱ የኢንተርኔት መዘጋትና እና የማህበራዊ ሚዲያ መቋረጦች ያስከተሏቸውን የምጣኔ ኃብት ቀውሶች የሚገመግም ነው ተብሏል።
ይህ ጥናት ኢትዮጵያ፤ የፖለቲካ ትኩሳት በጋለባቸውና አለመረጋጋቶች በተከሰተባቸው ወቅቶች ኢንተርኔት መዝጋቷን ገልጿል።
የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳን መገደል ተከትሎ በተቀሰቀሰ ሕዝባዊ ተቃውሞ የተነሳ፣ ከሰኔ እስከ ሐምሌ ባሉት ወራቶች ውስጥ፣ ከሶስት ሳምንት በላይ ኢንተርኔት ተቋርጦ እንደነበር ጥናቱ አመልክቷል።
እንደ ተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት ከሆነ በዚህ ግጭት 166 ሰዎች ሲገደሉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ጨምሮ 2ሺህ ያህል ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
በወቅቱ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት 9ሺህ ያህል ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጾ ነበር።
ጥቅምት 24 2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል የሕወሓት ኃይሎች በክልሉ በሚገው የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መክፈታቸው ከተገለፀ በኋላ መንግሥት ሕግ የማስከበር ዘመቻ ያለውን እርምጃ ተከትሎ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጦ መቆየቱ ይታወሳል።
ከሁለት ወራት በፊት በክልሉ በተከሰተው ወታደራዊ ግጭት ሳቢያ ተቋርጠው የነበሩት የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎቶች በከፊል የተመለሱባቸው አካባቢዎች ቢኖሩም፤ በበርካታ ከተሞች ውስጥ እስካሁን ስልክም ሆነ ኢንተርኔት አለመመለሳቸውን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ ፍሬሕይወት ታምሩ በአንድ ወቅት ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ አረጋግጠዋል።
የአገልግሎቱ መቋረጥ የሰብዓዊ እርዳታ የሚሰጡ ድርጅቶችም ሆነ የክልሉ ነዋሪዎች ላይ ያለውን የመረጃ ፍሰት ማደናቀፉን በተለያየ ጊዜ የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።
ሂውማን ራይትስ ዎች ይህንን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ላይ በክልሉ ያለው የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጥ ለሰብዓዊ ድርጅቶችና ለጋዜጠኞች የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎችን ለመከታተል እና ለመዘገብ አዳጋች ማድረጉን አመልክቷል።
ከክልሉ ውጪ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆችም ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመገናኘትና መረጃ ለመለዋወጥ በዚህ ምክንያት መቸገራቸውን ገልጾ ነበር።

በቀሪው የዓለማችን ክፍል የኢንተርኔት መቋረጥ ምን ይመስላል?
በፈረንጆቹ 2020 ዓ.ም ዓለማችን ለ27 ሺህ ሰዓታት ያህል ኢንተርኔት ማቋረጥ አጋጥሟት በአጠቃላይ 4.01 ቢሊየን ዶላር አክስሯታል ሲል ይኸው ጥናት አመልክቷል።
ይህ ቁጥር በ2019 ከነበረው የ8.05 ቢሊየን ዶላር ኪሳራ ጋር ሲነጻጸር በግማሽ ቀንሶ ታይቷል።
በአፍሪካ በ2020 ብቻ ለ6ሺህ 929 ሰዓታት ኢንተርኔት መቋረጡን ይፋ ያደረገው ይህ ጥናት፣ በዚህም የተነሳ አህጉሪቱ 237.4 ሚሊዮን ዶላር አጥታለች ሲል አትቷል።
በአፍሪካ በነበረው የኢንተርኔት ማቋረጥ ምክንያት 56.3 ሚሊዮን ያህል ሰዎች አገልግሎት ሳያገኙ መቅረታቸውን ጥናቱ ይፋ አድርጓል።
ጥናቱ እንደሚያሳው ከሆነ ይህ የምጣኔ ኃብት ቀውስ ኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ካስከተለው ቀውስ ጋር ተደምሮ አገራቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል።
በ2020 በመላው ዓለም በ21 አገራት 93 የኢንተርኔት መቋረጦች ማጋጠማቸውንም ይኸው ሪፖርት አመልክቷል።
በመላው ዓለም ኢንተርኔት ለ27 ሺህ 165 ሰዓታት መቋረጡን የዘገበው ይኸው ሪፖርት ኢንተርኔት ማቋረጥ ለ10 ሺህ 693 ሰዓታት፣ ማህበራዊ መገናኛ ብዙኀንን መዝጋት ደግሞ ለ5 ሺህ 552 ሰዓታት፣ እንዲሁም ኢንተርኔት ፍጥነትን እንዲዘገይ ማድረግ ለ10 ሺህ 920 ሰዓታት ተመዝግቧል።
በዚህም የተነሳ በዓለማችን ላይ በዚህ ምክንያት 268 ሚሊዮን ያህል ሰዎች የኢንተርኔት አገልግሎት ሳያገኙ መቅረታቸውን አስታውቋል።
በዓለማችን ላይ በኢንተርኔት መቋረጥ ክፉኛ ከተጎዱ የዓለማችን አገራት መካከል ሕንድ ቀዳሚውን ስፍራ ትይዛለች ተብሏል።
ሕንድ እና ምያንማር ለተከታታይ ሁለት ዓመታት ኢንተርኔትን በማቋረጥ ስማቸው በቀዳሚነት ተጠቅሷል።
ቻድ በበኩሏ ዋትስአፕን ከ2018/19 ጀምሮ በግዛቷ ላይ መጠቀም እንዳይቻል ያደረገች ሲሆን፣ ይህንንም ውሳኔዋን በ2020 መቀጠሏ ተመልክቷል።
በዓለማችን ላይ የኢንተርኔት መቋረጥ የተከሰተባቸው ምክንያቶች ሲዘረዘርም፣ ምርጫን በማስመልከት 15 በመቶ፣ የፕሬስ ነጻነትን ለማፈን 12 በመቶ፣ 29 በመቶ ደግሞ የመሰብሰብ ነጻነትን ለማስተጓጎል እንደሆነ በሪፖርቱ ላይ ተመልክቷል።
ይህ ሪፖርት በዓለማችን ላይ የተከሰቱ የኢንተርኔት እና የማህበራዊ መገናኛ ብዙኀን መቋረጦች ያስከተሏቸውን የምጣኔ ኃብት ቀውሶች የሚገመግም ነው።
የኢንተርኔት ማቋረጥ ማለት ይኹነኝ (ሆን) ተብሎ የመረጃ ፍሰትን በአንድ የተወሰነ አካባቢ ለመግታት በሚል ኢንርኔትን ወይንም የኤሌክትሮኒክስ ግንኙነትን ማቋረጥ፣ ፍጥነቱ እንዲዘገይ ማድረግ መሆኑን አክሰስ ናው የተሰኘው ድርጅት ይገልጻል።
አምባገነን መንግሥታት የተቃውሞ ሰልፍን ለማደናቀፍ፣ በይበልጥ ደግሞ በምርጫ በሚካሄድበት ወቅት የሚኖሩ ሰልፎችን ላይ ቁጥጥር ለማጥበቅ ኢንተርኔትን እንደሚዘጉ ተገልጿል።
ይህ ሪፖርት በ2021 ኢንተርኔት መቋረጥ በእነዚህ መንግሥታት ሊቀጥል ይችላል ሲሉ ተንብየዋል።












