የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ በአስቸኳይ እንዲወጡ የጆ ባይደን አስተዳደር ጠየቀ

የትግራይ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Byron Smith

የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ክልል በአስቸኳይ እንዲወጡ አሜሪካ ጠየቀች።

በትግራይ ካለው ግጭት ጋር ተያያዞ ዝርፊያዎች፣ መደፈሮችና በስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ ጥቃቶችና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየደረሱ መሆናቸውን የሚታመኑ ሪፖርቶች እንዳሉ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት (ስቴት ዲፓርትመንት) አስታውቋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ በቃለ አቀባዩ በኩል በተለይ ለቢቢሲ በገለፀው መሰረት የተለያዩ ኃይሎች ብሎ የጠራቸው አካላት ጥሰቶቹን እየፈፀሙት ነው ብሏል።

አገራቸው የኤርትራን ወታደሮች በተመለከተ ግልፅ አቋም እንዳላት ያስታወቀው መስሪያ ቤቱ የኤርትራ ወታደሮች በሙሉ ከክልሉ በአስቸኳይ እንዲወጡ በማለት አፅንኦት ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ በተደጋጋሚ በትግራዩ ግጭት የኤርትራ ጦር አለመሳተፉን አስታውቋል።

ወታደሮቹ ዝርፊያ፣ ወሲባዊ ጥቃት፣ በስደተኞች መጠለያ ካምፕ ላይ ጥቃትና ሌሎች ጥሰቶች እያደረሱ እንደሆነ የሚታመኑ ሪፖርቶች አግኝቻለሁ ብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ በትግራይ ክልል የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞችን የኤርትራ ወታደሮች በግድ እየመለሷቸው እንደሆነ ማስረጃ እንዳገኘም ጠቁሟል።

ምን ያህል የኤርትራ ወታደሮችና የት እንዳሉ ግልፅ አይደለም ያለው የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ነገር ግን የኤርትራ ኃይሎች በከፍተኛ የጦር መሳሪያ የታገዘ ጥቃት እያደረሱ እንደሆነና ይህም በትግራይ በሚያዋስነው ድንበር በኩል ሊሆን እንደሚችል ጠቁሟል።

ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ኤርትራና ትግራይን በሚያዋስነው ድንበር በኩል ወደ ትግራይ መግባታቸውን እንዲሁ ቃለ አቀባዩ አስፍረዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ ትግራይ ላይ በተደረገው ወታደራዊ ግጭት የኤርትራ ሰራዊት ተሳትፏል ስለመባሉ "ፕሮፓንዳና መሰረተ ቢስ ነው" ብለውታል።

ከኤርትራም በተጨማሪ የሶማሊያ ሰራዊት ተሳትፏል መባሉን ሃሰት ነው ማለታቸው የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የአገሩን ዳር ድንበር ማስጠበቅ ብቻ ሳይሆን በሶማሊያ፣ በሩዋንዳ፣ በብሩንዲና፣ ኮንጎ "ትልቅ ገድል የሰራ ኃይል ነው" በማለትም የሰራዊቱን ጥንካሬ አስረድተዋል።

ቃለ አቀባዩ ጥር 12/2013 ዓ. ም በሰጡት መግለጫ "የውስጥ የህግ በላይነትን ለማስከበር ማንንም አገር የሚጠራ አይደለም፤ የሚጠራም አገር የለም፤ ሊጠራም አይችልም፤ አይገባም፤ አይፈልግምም፤ አስፈላጊም አልነበረም" በማለት አፅንኦት በመስጠትም ነው የተናገሩት።

የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ክልል በአስቸኳይ እንዲወጡ አሜሪካ ጠየቀች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ በተጨማሪ በክልሉ ውስጥ እየተፈፀሙ ናቸው የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ነፃና ገለልተኛ በሆነ አካል ምርመራዎች እንዲካሄድና ይህንን የፈፀሙ አካላት ተጠያቂ መሆን ሊኖርባቸው እንደሚገባ አሳስቧል።

ከዚህም በተጨማሪ ውጊያዎች ሙሉ በሙሉ እንዲቆሙና በግጭቱ ለተጎዱ የክልሉ ነዋሪዎች ደህንነቱ በተጠበቀ መልኩ፣ ምንም አይነት እክል በሌለበት ሁኔታ የሰብዓዊ እርዳታዎች የሚደርሱበት መንገድ በአፋጣኝ ሊመቻች እንደሚገባ አሜሪካ ጥሪ አድርጋለች።

"እነዚህን ተግባራት በአፋጣኝ ማከናወን ሰላምን ለመመለስና የእርቁን ሂደት ለማረጋገጥ ቁልፍ የመጀመሪያ ሂደቶች ናቸው። በመንግሥትና በተጋሩ መካከልም ውይይት አስፈላጊ ነው" ይላል።

ከዚህም በተጨማሪ ከግጭቱ ጋር ተያይዞ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የክልሉ ነዋሪዎች በረሃብ ሊሞቱ ይችላሉ የሚለው ሪፖርት "ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮብናል" ያለው መስሪያ ቤቱ የህይወት አድን እርዳታ አስፈላጊነትን አስምሮበታል።

በትግራይ ክልል ውስጥ "በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ ምክንያት ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉ" አንድ የመንግሥት ባለስልጣን መናገራቸውን ከእርዳታ ሠራተኞች ጋር ከተደረገ ስብሰባ ላይ ሾልኮ የወጣ ማስታወሻ ላይ የሰፈረ ጽሁፍ ማመልከቱ የሚታወስ ነው።

ከሰሞኑ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በግጭት ወቅት የሚከሰት ወሲባዊ ጥቃት ላይ አተኩሮ የሚሠራው ቡድን በትግራይ ክልል እየደረሰ ያለው ወሲባዊ ጥቃት እንዲገታ ያሳሰበ ሲሆን ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ "በመቀለ ከተማ በርካታ ቁጥር ያለው ሰው የመደፈሩ ክስና በአጠቃላይ ከትግራይ ክልል የተሰሙት የወሲባዊ ጥቃት ክሶች እጅግ አሳስበውኛል" በማለት ገልጿል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በተመሳሳይ በከልሉ ውስጥ እንዲሁ ወሲባዊ ጥቃት እየደረሰ እንደሆነ የሚታመን ሪፖርት ማግኘቱን ያሳወቀ ሲሆን መስሪያ ቤቱ እንዲህ አይነት "አስነዋሪ ተግባርን መንግስታችን ያወግዛል" በማለት አትቷል።

መደፈርን ጨምሮ ደርሰዋል የተባሉ ሌሎች ጥሰቶችን የኢትዮጵያ መንግሥት ነፃና ገለልተኛ በሆነ መልኩ አጣርቶ ወደ ፍርድ እንዲያቀርብ ጥሪ አድርጓል መስሪያ ቤቱ በቃለ አቀባዩ በኩል።

በቅርቡም የአውሮፓ ሕብረት በከፍተኛ ዲፕሎማቱ ጆሴፕ ቦሬል በኩል ባወጣው መግለጫ "ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ ግድያዎች፣ ዘረፋዎች፣ አስገድዶ የመድፈር ድርጊቶችና ስደተኞችን በግዴታ ወደ አገራቸው መመለስና የጦር ወንጀል ድርጊቶች ሊሆኑ የሚችሉ ክስተቶችን በተመለከተ በተከታታይ መረጃ ይደርሰናል" ማለቱ የሚታወስ ነው።

በተደጋጋሚ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በክልሉ ያለው የሰብዓዊ ሁኔታ የፈጠረበትን ስጋትም መንግሥታቸው እንደሚጋራ ገልፆ ስደተኞችን ጨምሮ በነፃ ዜጎች ላይ የሚፈጠረውን "የጭካኔ ተግባር እናወግዛለን" ብለዋል ቃለ አቀባዩ።

ሁሉም ወገኖች ቢሆኑ አለም አቀፉን የሰብዓዊ መብት ህግጋት ማክበር እንዳለባቸው አስታውሰዋል በመልዕክታቸው።

በክልሉ የተገደሉና ማስፈራራት የደረሰባቸውን የሰብዓዊ እርዳታ ሰራተኞች እንዲሁም የእርዳታ ቁሳቁሶች መዘረፍ፣ የዜጎች ልማት መውደምን አገራቸው "ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በመሆን ታወግዘዋለች" የሚል መልእከትም የአሜሪካ መንግሥት አስተላልፏል።

የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት በኅዳር ወር አጋማሽ ላይ መቀለን ከተቆጣጠረ በኋላ በትግራይ ያካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ መጠናቀቁን መግለጹ ይታወሳል። ነገር ግን አልፎ አልፎ ውጊያ እንደሚካሄድ የተነገረ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በክልሉ ያለውን የሰብአዊ ሁኔታ "የከፋ" ሲል ገልጾታል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ውጊያው መቀጠሉን በጠቆመበት መግለጫ፤ የቀጠለው ውጊያ በቀጣይነት በክልሉ ረዘም ላለ ጊዜ የሽምቅ ውጊያ ሊያስከትል እንደሚችል ጠቅሶ ይህም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል አለመረጋጋት እንደሚፈጥርና በአገሪቱ ውስጥ ያለውን የብሔር ውጥረት እንደሚያባብሰው ጠቁሟል።

"ይህ ሁኔታ በአሜሪካ ተቀባይነት ባገኙት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የተሰሩ የዲሞክራሲ እንዲሁም ሌሎች ማሻሻያዎችን ስጋት ውስጥ ከመክተት በተጨማሪ በሶማሊያ እንዲሁም በሽግግር መንግሥት ያለችውና በከባድ ችግሮች እየተናወጠች ያለችው ሱዳን ላይ አለመረጋጋት ይፈጥራል" በማለት አስምሯል።

ቢሮው ኢትዮጵያ በሶማሊያ ያሏትን ሰላም አስከባሪዎች ማውጣቷን ጠቅሷል።

በፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል ለረዥም ጊዜ የዘለቀው መቃቃርና አለመግባባት ተካሮ የህወሓት ኃይሎች የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል በማለት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የፌደራሉን ጦር ወደ ትግራይ ማዝመታቸው ይታወሳል።