"ባለቤቴ ጫካ ውስጥ መንታ ተገላግላ አረፈች" የትግራዩ ተፈናቃይ በሱዳን

የአብርሃ መንታ ልጆች
የምስሉ መግለጫ, የአብርሃ መንታ ልጆች

በትግራይ ክልል ባለው ግጭት ምክንያት በቤቷ ልጆቿን መገላገል ያልቻለችው ነፍሰ ጡር፤ ግጭቱን ሽሽት በጫካ ውስጥ ተደብቃ ሳለ መንታ ልጆቿን ብትገላገልም፤ በህይወት የቆየችው ለጥቂት ቀናት ብቻ ነበር።

እናቲቱ ይህችን አለም ላታያት ለመጨረሻ ጊዜ መሰናበቷን ባለቤቷ ይናገራል።

ልጆቿን ማየት የቻለችው ለአስር ቀናት ብቻ ነበር። ባለቤቷም ልጆቹን በቅርጫት አድርጎ የእርሱ እና የልጆቹን ነፍስ ለማዳን ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን ተሰደደ።

ከመንታ ጨቅላዎቹ በተጨማሪ፣ የአምስት ዓመት ወንድ ልጁን፣ የ14 ዓመቱን የባለቤቱን ወንድም ይዞ ሱዳን ገብቷል፤ በአሁኑ ወቅት በስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ ይገኛል። መንታ ህፃናቱን አንዲት አሜሪካዊት ዶክተር ለመርዳት እየሞከረች ነው።

በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰው ግጭት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ነዋሪን አፈናቅሏል። 60 ሺህ የሚሆኑት ጨርቄን፣ ማቄን ሳይሉ ወደ ሱዳን ሸሽተዋል።

እያንዳንዱ ተፈናቃይ የሚናገረው ታሪክ አለው፤ መጀመሪያ ጥይት ሲተኮስ የተሰማቸው ስሜት፣ በአየር ድብደባው ወቅት ዋሾች ውስጥ መደበቅ፣ ጥይት የተተኮሰባቸው፣ የተደፈሩ እንዲሁም ሌሎች ታሪኮችን በውስጣቸው አምቀው ይዘዋል።

በርካቶቹ ለቀናት ያህል ያለ ምግብና ውሃ በእግራቸው ተጉዘው በፅናት የደረሱበትንም ያወሳሉ።

ባለቤቱን ያጣው አብርሃ ክንፈ

ዕድሜየ አርባ ነው። የቀድሞ ባለቤቴ ደግሞ 29። ከባለቤቴ ጋር የተጋባነው ከ13 አመታት በፊት ነው፤ በትዳራችን ሶስት ልጆች አፍርተናል።

መኖሪያችን በምዕራብ ትግራይ ማይካድራ ከተማ አቅራቢያ አካባቢ ባለ የእርሻ መሬት ነው።

በግጭቱ ክፉኛ የተጎዳው የምዕራብ ትግራይ አካባቢ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በግጭቱ ክፉኛ የተጎዳው የምዕራብ ትግራይ አካባቢ

እለቱ ማክሰኞ ህዳር 1፣ 2013 ዓ.ም ነበር፤ የፌደራሉ ሠራዊት በአካባቢያችን የመጡበት እለት። ወታደሮቹን የኛን ቤት አለፉት። አላዩንም ነበር። ትልቅ እፎይታ ተሰማን።

በዚህ አጋጣሚ ከቤታችን ወጥተን በቤታችን አካባቢ በሚገኝ ጫካ ውስጥ ከአራት ጎረቤቶቻችን ጋር ተደበቅን። ባለቤቴ በምጥ ተያዘች፤ ነፍስ ውጭ ነፍስ ግቢ ከፍተኛ ህመም ይሰማት ጀመር።

ማይካድራ የሚገኘው ክሊኒክ ለመውሰድ ፈራሁ። አምላክ የተመሰገነ ይሁንና ባለቤቴ አብራን ተደብቃ በነበረች ሴትዮ እርዳታ መንታ ሴት ልጆችን ተገላለለች።

በዚያኑ ቀን ወደ ቤት ተመለስን። ያለመታደል ሆኖ ባለቤቴ ለታይ፤ ከወሊድ በኋላ ህክምና ማግኘት አልቻለችም። የሚፈሳትን ደም ለማስቆም የሚያስፈልጋትን መርፌም ባለመወጋቷ ሁኔታዋ እየከፋ መጣ። ከአስር ቀናት ስቃይ በኋላ አረፈች። ኃዘኑ ልቤን እንዴት እንደሰበረው በቃላት መግለፅ አልችልም። በአራት ጎረቤቶቼ እርዳታ እዛው እርሻ ቦታችን ላይ ቀበርናት።

ክሊኒክ ምነው በወሰድኳት ብዬ እመኛለሁ ነገር ግን በወቅቱ ከተማዋ ግልብጥብጧ የወጣበት ነዋሪዎች ነፍሳቸውን ለማትረፍ እግሬ አውጭኝ የሚሉበት ወቅት ነበር። እስካሁን ድረስ ከተማዋ ምድረ በዳ እንደሆነች ነው።

ከአምስት አመታት በፊት ከቤተሰቦቼ ጋር ከአማራ ክልል፣ መተማ ከተማ በብሔር ግጭት ምክንያት ነው ተፈናቅለን ወደ ማይካድራ የመጣነው። ማይካድራ ከመጣን በኋላ ህይወትን ከዜሮ ጀመርን። በአካባቢው መስተዳድር ለእርሻ የሚሆን መሬት ተሰጠን። በመሬታችን ላይ አነስ ያለች የጭቃ ቤት ገነባን። ለኔም ለባለቤቴም ምቹ ነበር። ህይወትን መምራት ጀመርን። ወንድ ልጃችን እዚሁ ተወልዶ ነው ያደገው። መንታ ልጆቼ ቢሆኑ እዚህ ነው የተወለዱት፤ ምንም እንኳን የኖሩባት ለሃያ ቀናት ነው እንጂ

ባለቤቴ ስትሞት ሰማይና ምድሩ ተገለባበጠብኝ። አቅፌያት አነባሁ፤ አለቀስኩ። ይሄንን ደም አፋሳሽ ጦርነት ጠላሁት፤ ረገምኩት፤ ይህ ነው የማይባል ስቃይ ነው ያመጣብን።

የምወዳት ባለቤቴ፣ የልጆቼ እናት የሞተችው ህክምና በማጣቷ ነው።

የአማራ ክልል ሚሊሻ ባማይካድራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአማራ ክልል ሚሊሻ ባማይካድራ

ሁኔታው አደገኛ ስለነበር፤ ጎረቤቶቼ ወደ ሱዳን ቀድመውኝ ሸሹ። እኔ ከልጆቼና ከባለቤቴ ወንድም ጋር ወደ ኋላ ቀረሁ። ወታደሮቹን ባየናቸው ቁጥር ጫካ ውስጥ እንደበቃለን። ያለ ጎረቤቶቼ እርዳታ መንታዎቹን መንከባከብ ፈተና ሆነብኝ።

አራሶች ደግሞ የእናታቸው የጡት ወተት ያስፈልጋቸዋል። በቻልኩት መጠን ውሃ፣ ስኳር በጥብጬ በእጄ እየነከርኩ እንዲጠቡት አደርጋለሁ። እንዲሁ ሾርባ ሲኖር በዚያው መንገድ እየነከርኩ እንዲጠቡት እያደረግኩ በህይወት ለማቆየት ቻልኩኝ። በጣም ሲከብደኝ ከሃያ ቀናት በኋላ በአካባቢው ወደሚገኝ የፌደራል ሰራዊቱ ወደሰፈረበት ቦታ አቀናሁ። ልጆቼን ወደ አቅራቢያው ከተማ ሁመራ ወደሚገኝ ክሊኒክ መውሰድ እችል እንደሆነ ጠየቅኳቸው።

የተከዜ ወንዝ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ስደተኞች ሱዳን ለመግባት የሚሻገሩት የተከዜ ወንዝ

እንደ እድል ሆኖ እንዳልፍ ፈቀዱልኝ፤ ነገር ግን ወደ መተማ ክሊኒክ አልሄድኩም። በእግሬ ወደ ተከዜ ወንዝ ተጓዝኩኝ፤ ከተከዜ በጀልባ ተሳፍሬ ወደ ሱዳኗ ሃምዳይት ተሻገርኩ። መንታዎቹን በቅርጫት ውስጥ ይዤ ነበር። አንደኛው ልጄና የባለቤቴ ወንድም አብሮኝ ነበር።

በሃምዳያት የስደተኞች ካምፕ ውስጥ መጠለያ አግኝተናል። በቀይ መስቀል ውስጥ የምትሰራ አንዲት አሜሪካዊት ዶክተር መንታዎቹን እየተንከባከበቻቸው ነው። የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ ታደርጋለች፤ ዕድገታቸውን በየሶስት ቀኑ ትከታተላለች። መቼም ለኔም ሆነ ለሌሎች ስደተኞች ለሰጠችን ድጋፍና ላሳየችን ደግነት አምላክ ይባርካት።

የመንታዎቹ ክርስትና

አሁን መንታዎቹ ሁለት ወር ሆኗቸዋል። አሁን ስጋ ለበስ እያደረጉ ነው። ነገር ግን የአምስት አመት ልጄ እናቱን በጣም ነው የሚናፍቃት፤ በተደጋጋሚ የት ናት እያለ ይጠይቃል። ልብ ይሰብራል። መዋሸቴን ብጠላውም አንድ ቀን አብራን ትሆናለች እለዋለሁ።

ለታይ አብራን እንዴት እንዳልሆነች መረዳት ይከብደኛል፤ ይጨልምብኛል። እውነት ነው ህይወት ጨካኝ ናት። እውነቱን ተናገር ከተባልኩ መንታዎቹ ልጆቼ በእቅፌ የሞተችው ባለቤቴን በየጊዜው ያስታውሱኛል።

አብረውኝ ያሉት ስደተኞች ሁኔታየን ስለሚያሳዝናቸው ሊያፅናኑኝ ይሞክራሉ። ለመንታዎቹ ልጆቼም ስም አውጥተውላቸዋል። አንደኛዋን ኤደን ብለዋታል፤ ያው የመፅሃፍ ቅዱስን ታሪክ በማጣቀስ እንዴት አዳምና ሔዋን ከኤደን እንደተባረሩ ለማሳየት። ሌላኛዋን ደግሞ ትረፊ ብለዋታል። መትረፏ ያው የአምላክ ተአምር ነው። በትግርኛ ደግሞ ቆይ (ኑሪ) እንደማለት ነው።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት መሰረት ሴት ልጆች በ80 ቀናቸው ክርስትና ይነሳሉ። አሁን የክርስትና ቀናቸው እየተቃረበ ነው። በስደተኞቹ ካምፕ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የለም።

ሃዘኔ፣ ህመሜ ጥልቅ ነው። ለአምላኬ በየጊዜው የምፀልየው ዋነኛ ጉዳይ ጥንካሬ ሰጥቶኝ ልጆቼን ደህንነቱ በተጠበቀ ሁኔታ እንዳሳድግ ነው። ይሄ አሰቃቂ ጦርነት ባለቀና ህይወትን ካቆምንበት ብንቀጥል እያልኩ ተስፋ አደርጋለሁ።

ለምንድን ነው ሰላምና ደህንነታችን እንዲህ የተነጠቅነው እያልኩ ከራሴ ጋር እታገላለሁ። ለምንስ እንዲህ እንሰቃያለን?

ሃዘኑና ስቃዩን ያስከተሉብን ሰዎች በምቾትና ተረጋግተው እየኖሩ እኛ ለምን በደህና እንዳንኖር ተፈረደብን? ለምን ተካድን? እነሱ ያለምንም ችግርና ውጣ ውረድ ልጆቻቸውን እያሳደጉ ነው። ልጆቻቸው በሞቀ ቤታቸው እየተደሰቱ ነው። ቤተሰቦቻቸው ይንከባከቧቸዋል፤ ትምህርት ቤት ይሄዳሉ፤ ሰፈር ይጫወታሉ።

ጥልቅ ኃዘን ነው የሚሰማኝ

ከመተማ ተፈናቅዬ ወደ ማይካድራ የመጣሁበትን በሃሳብ አምስት አመት ወደ ኋላ እሄዳለሁ።

በማህበረሰቡ ውስጥ ተቀባይነትን ለማግኘት፤ ኑሮን ለማሸነፍ ከጥዋት እስከ ማታ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳልል ነበር የጣርኩት። ይሄ ሁሉ ቤተሰቦቼን ለመደገፍ ነው። የተሰጠኝን የእርሻ መሬት ብቻ ሳይሆን የበለጠ ጉርስ ለማግኘት ሌሎች መሬቶች ተከራይቼ አርስ ነበር። ጥሩ ሰሊጥና ማሽላ አመርት ነበር። በስደት ይኸው አለው ምንም የምሰራው ነገር ሳይኖር፤ ያለ መሬት፣ ያለ ባለቤቴ፣ ያለ ማህበረሰቤ እንዲሁም የምሄድበት ቤተ ክርስቲያን በሌለበት፤ ተነቅዬ አለሁ።

በትግራይ ግጭት ወደ ሱዳን ከተሰደዱ ተፈናቃዮች መካከል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በትግራይ ግጭት ወደ ሱዳን ከተሰደዱ ተፈናቃዮች መካከል

ስለ ምርቴ፤ እሰበስበው ስለነበረው እህል አስባለሁ። ምርቴን የመሰብሰቢያ ወቅት ነበር። ምን ማድረግ እችላለሁ? በትዝታና በሃሳብ መኖር እንጂ፤ የነበረንን ንብረት፣ ህይወት እንዴት እንደነበር፣ልጆቼ እንዴት በደስታ ይቦርቁና ይጫወቱ እንደነበር አስብና ከስደተኝነት ህይወቴ ለመላመድ እታገላለሁ። ኃዘኔ ጥልቅ ነው፤ ልጆቼ ይኸ አይገባቸውም።

የነበረኝ ሁሉ ተወሰደብኝ፤ አጣሁ! ትርጉም በሌለው የብሔር ግጭት ምክንያት። በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በሱዳን ካምፖች ይገኛሉ፤ ሁላችንም ከትግራይ ነን። በግጭቱ ምን ያህል ክፉኛ እንደተጎዳን ማሳያ ነው። ተስፋዬ ጦርነቱ በቅርቡ እንዲጠናቀቅና ሰላም እንዲሰፍን ነው። ቤታችን ለመመለስ እንናፍቃለን። ወደቀደመ ህይወታችን፤ ወደ አባት፣ አያቶቻችንና ዘሮቻችን መሬት መመለስን እንሻለን።

line

በፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል ለረዥም ጊዜ የዘለቀው አለመግባባት ተካሮ የህወሓት ኃይሎች የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል በማለት ጠቅላይ ሚንሰትር ዐብይ የፌደራሉን ጦር ወደ ትግራይ ማዝመታቸው ይታወሳል።

መንግሥት ሕግ የማስከበር በሚለው ወታደራዊ ዘመቻ ቁጥሩ በትክክል ባይታወቅም በርካቶች ህይወታቸው አልፏል። በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን ተሰደዋል።

የትግራይ መዲና የሆነችው መቀለ በፌደራል መንግሥት ሠራዊት ቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ ወታደራዊ ዘመቻው መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ተናግረው ነበር።