"ማንኪያ ሳይቀር ነው የዘረፉኝ" በመቀለ የሚገኙ ተፈናቃይ

በሱዳን ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

"ልጆቼንና ባለቤቴን ይዠ የ80 አመት ሽማግሌ አባቴን ለብቻው ጥዬ ነው የመጣሁት፤ ያየሁትን ነገር ለመናገር አቅም የለኝም። ከባድ መሳሪያ ከላያችን ላይ እየተተኮሰብን ነፍሰ ጡር ሴቶች በየመንገዱ እየወለዱ አንዱን አንስተን አንዱን ጥለን ነው መቀለ የደረስነው" በማለት በመቀለ በጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ የምትገኘው ፈረይ በሳግና በለቅሶ በተቆራረጠ ድምፅ ትናገራለች።

ፈረይ በትግራይ ክልል የተከሰተውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ነፍሳቸውን ለማትረፍ ከሸሹት መካከል አንዷ ናት።

ፈረይ ጦርነቱን ሸሽታ ከሽረ ከተማ ወደ መቀለ ገብታለች። በመቀለ ከተማ ውስጥ ባሉና በጊዜያዊነት በተለያዩ የትግራይ ክፍሎች ተፈናቅለው ለመጡ በመጠለያነት በተቀየሩት ትምህርት ቤቶች ውስጥ በአንዱ ትገኛለች።

ተፈናቃዮቹ ያሉበትን ችግር ለመናገር እንባ የሚተናነቃት ፈረይ "እዚህም የሚበሉትን ያጡ አራስ እናቶች አሉ ሁሉም ችግር ነው" በማለት ለቢቢሲ በስልክ ተናግራለች።

ከምግብ እጥረት በተጨማሪ የልብስና የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ እጥረት በመጠለያው ውስጥ የሚገኙ ሴቶችን ህይወት አክብዶታል።

ይህንን ችግር የተረዱ የመቀለ ነዋሪዎችም የሴቶች ንፅህና መጠበቂያና አንሶላ ቢለግሷቸውም ለሁሉም መከፋፈል አልቻለም።

"የሚቀይሩት ልብስና የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ አጥተው ከቤት የማይወጡ ወጣት ሴቶችና እናቶች አሉ። እኛም ልብስም ሆነ ጫማ የለንም ብዙ የሚጎድለን አለ" ትላለች በኃዘን በተሰበረ ድምጿ

ይህ የፈረይ ታሪክ ብቻ ሳይሆን በርካታ በግጭቱ ምክንያት የተፈናቀሉ የክልሉ ነዋሪዎች እያለፉበት ያለ መከራ ነው።

ከሽራሮ ከተማ ተፈናቅለው በመቀለ ትምህርት ቤት ውስጥ ተጠልለው የሚገኙት አቶ ተስፋይም ሲፈናቀሉ የመጀመሪያቸው አይደለም፤ ለሁለተኛ ጊዜም ተጎጅ ናቸው።

ከሁለት አመት በፊት ከጎንደር ተፈናቅለው ከመጡ በኋላ ያላቸውንም ገንዘብ ሰብስበው በ500 ሺህ ብር ባድመ ከተማ ላይ የወርቅ ማንጠሪያ ድርጅት ከፈቱ።

ሽራሮ ከተማ ላይ ደግሞ ጋራዥ ከፍተው የመካኒክ ስራ እየሰሩ እንደነበሩ ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅት ግን በግጭቱ ምክንያት ቤሳ ቤስቲን የላቸውም። ያለ የሌለ ንብረታቸው ተዘርፏል።

"ሁሉንም አጥቻለሁ ማንኪያ ሳይቀር ነው የዘረፉኝ እኔ የሶስት ልጆች አባት ነኝ። ልጆቼ ምን ሆነህ ነው የነበረህን ያጣኸው? ቢሉኝ ምን ብዬ እመልስላቸዋለሁ። የቱን ታሪክ ነው የምነግራቸው? ይህንን ሳስብ መመለስ ይከብደኛል። እዚህ መቀመጥ ደግሞ ጥዋት ተነስቶ እንጀራ ወይም ዳቦ መጣ ወይ እያሉ ተመፅዋች መሆን ከባድ ነው" ይላሉ።

በቅርቡም የአውሮፓ ሕብረት በከፍተኛ ዲፕሎማቱ ጆሴፕ ቦሬል በኩል ባወጣው መግለጫ "ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ ግድያዎች፣ ዘረፋዎች፣ አስገድዶ የመድፈር ድርጊቶችና ስደተኞችን በግዴታ ወደ አገራቸው መመለስና የጦር ወንጀል ድርጊቶች ሊሆኑ የሚችሉ ክስተቶችን በተመለከተ በተከታታይ መረጃ ይደርሰናል" ብለዋል።

በሽራሮ ከተማ በነበረው ግጭት ንብረታቸውን ያጡት ሌላኛዋ ወ/ሮ አወጣሽም በመቀለ በሚገኘው ጊዜያዊ የትምህርት ቤት መጠለያ ውስጥ ያሉ ሲሆን ህይወት እንዴት እየፈተነቻቸውም እንደሆነ ለቢቢሲ ትግርኛ በስልክ ተናግረዋል።

"አንዳንድ ቀን ፆማችንን እናድራለን። አንዳንዴም እንበላለን። ለአንድ ሰው በተሰጠ ፍራሽ ላይ የአንዱን ሽታና በሽታ ችለን ተጠጋግተን እናድራለን። እዚህ ከባድ ህይወት እያሳለፍን ነው።"

የሚሉት ወ/ሮ አወጣሽ ቀይ መስቀል ወደመጡበት እንውሰዳችሁ የሚል ጥያቄ ቢያቀርብም "ወደመጣንበት መመለስ ስናስብ ግን ወታደር ስላለ ስጋት አለን። እዚህ ለአንድ ወር ብለው ከሰጡን እርዳታ ውጭ ህዝቡ ነው የሚደግፈን" ይላሉ

በተለያዩ ትምህርት ቤቶች የሚገኙት ተፈናቃዮች ወደቀደመ ህይወታቸውም ለመመለስ የሚታሰብ እንዳልሆነና ከፍተኛ ፍራቻ እንዳላቸውም ይገልፃሉ።

በክልሉ ውስጥ ያለው ሁኔታ አስከፊ እንደሆነና "በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ ምክንያት ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉ" አንድ የመንግሥት ባለስልጣን መናገራቸውን ከእርዳታ ሠራተኞች ጋር ከተደረገ ስብሰባ ላይ ሾልኮ የወጣ ማስታወሻ ላይ የሰፈረ ጽሁፍ ማመልከቱ የሚታወስ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ጦርነት በተካሄደባቸው የትግራይ ክልልና አዋሳኝ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ደኅንነትና ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑንና የሰብአዊ ቀውስን ሊያስከትል እንደሚችል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ገልጿል።

በትምህርት ቤቶቹ ተጠልለው ለሚገኙ ተፈናቃዮች ድጋፍ ከሚያደርጉ በጎ አድራጊ ድርጅት መሪዎች መካከል አቶ ሙሉ ኃይለሥላሴ አንዱ ናቸው።

አቶ ሙሉ ለተፈናቃዮች የህክምና አገልግሎት ለመስጠት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ከፍተኛ የሆነ የመድኃኒት እጥረት መኖሩን ያስረዳሉ።

ተፈናቃዮቹ መድኃኒት ሲፈልጉ በነፃ የሚሰጡ ፋርማሲዎች እንዳሉና የተወሰኑ ሆስፒታሎችም ባለው አቅም አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ቢገልፁም የመድኃኒት አቅርቦት ችግር እንዳለ ያስረዳሉ።

ነዋሪዎች ከጤና አገልግሎት እጥረት ጋር በተያያዘ እየሞቱ እንደሆነና በምግብና ውሃ እጥረትም በከፍተኛ ሁኔታም መጎዳታቸውን ሮይተርስ ክልሉን ከጎበኙ የእርዳታ ድርጅቶች ያገኘውን መረጃ ዋቢ አድርጎ ዘግቧል። ነዋሪዎች አሁንም በድንጋጤ ላይ መሆናቸውንም ዘገባው አስነብቧል።

ከመቀለ ከተማ ውጭ ባሉ አካባቢዎች በተለይ የጤና አገልግሎት እንደሌለና በሳንባ ምችና በወሊድ ምክንያትም የሚሞቱ እንዳሉም ሮይተርስ ድንበር የለሽ የሃኪሞች ቡድን (MSF) ድንገተኛ ፕሮግራም ኃላፊ ማሪ ካርመን ቪኖሌስን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።

በአዲግራትና አክሱም አካባቢ የሚገኙ የገጠር አካባቢዎችን የጎበኙት የእርዳታ ድርጅቱ አባላት በአዲግራት የሚገኙ ዶክተሮችና ነርሶች "የተራቡ ህመምተኞችን" በህይወት ለማቆየት ሲታገሉ ማየታቸውንና ዋነኛው የከተማይቱ ሆስፒታል አምቡላንሶችም ተሰርቋል ማለታቸውን ሮይተርስ በዘገባው አስነብቧል።

በጎበኙባቸውም አካባቢዎች የምግብ እጥረት፣ ውሃ፣ የጤና አገልግሎት ችግርና በፍራቻ የተዋጡ ሰዎችን ያገኙ ሲሆን "ሁሉም ምግብ ነው" የሚጠይቁት ብለዋል ኃላፊዋ ማሪ ካርመን።

የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ በዚህ ሳምንት ሰኞ እለት ባወጣው መግለጫ በሽረ ባሉ ክሊኒኮች በርካቶችን እየገደለ ያለው የምግብ እጥረት እንዳለ ያሳወቀ ሲሆን ሁኔታውንም የከፋ ነው ብሎታል።

ከግጭቱም በፊት በርካታ ሰዎች በምግብ ዕጦት ሲሰቃዩ የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ በግጭቱ ሁኔታ እንደተባባሰና በተለይም ጦርነቱን ፈርተው በተራራዎች ላይ የተደበቁ ሰዎችም በምግብና በህክምና አቅርቦት እጥረትም መቸገራቸውንና መድረስ እንዳልተቻለ ተገልጿል።

ሮይተርስ በተጨማሪ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳዳሪ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሙሉ ነጋን (ዶ/ር) ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ባለስልጣኑ ተራራማ የሆኑ ገጠራማ ቦታዎች እርዳታ ለማድረስ የመጓጓዣ እጥረት የነበረ ቢሆንም፣ እርዳታ ማድረስ መጀመራቸውን አስታውቀዋል።

ከሰሞኑም እንዲሁ በክልሉ ምግብ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችና የሕክም አቅርቦቶች የሰብዓዊ ድጋፍ ለ1.8 ሚሊዮን ሰዎች መድረሱን የሠላም ሚኒስቴር ገልጿል።

ሚኒስቴሩ ድጋፍ ለሚፈልጉ ሰዎች እየቀረበ ያለውን እርዳታ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ ከተጠቀሱት ሰዎች በተጨማሪ በክልሉ 2.5 ሚሊዮን ተጠቃሚዎችን ለማስተናገድ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን አመልክቷል።

ከዚህም በተጨማሪ በክልሉ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ የስደተኞች ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነም የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን፣ ዩኤንኤች ሲ አር አስታውቋል።

በስደተኞቹ ሁለት ጣቢያዎች ድርጅቱ መገኘት እንደቻለና መሰረታዊ በሚባሉ አቅርቦት እጦትም እየተሰቃዩ እንደሆነ አስታውቋል።

የኮሚሽኑ የኢትዮጵያ ተወካይ ክሪስ ሜልዘር ለቢቢሲ እንደተናገሩት ኤጀንሲው በስደተኞች ካምፑ አካባቢም አገልግሎት መስጠት ይቻል ዘንድም ጊዜያዊ መጠለያ እያቋቋመ ይገኛል።

በቅድሚያም ምግብና ንፁህ ውሃ አቅርቦት ቅድሚያ የሚሰጠው ስራ ነው ያሉት ተወካዩ "ለባለፉት ሁለት ወራት በስደተኞች መጠለያ ካምፕ አቅራቢያ ከሚገኝ ወንዝን በመጠቀም ነው ምግብ ለማብሰል፣ ለመጠጥም ሆነ ለመታጠቢያነት ሲጠቀሙ የነበሩት። ለዚያም ነው ተቅማጥ በከፍተኛ ሁኔታ የተባባሰበው" ብለዋል።

በምዕራብ ትግራይ በሚገኙት ማይ አይኒና አዲ ሃሩሽ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ 25 ሺህ የኤርትራ ስደተኞች የሚገኙ ሲሆን ቁጥራቸውም በግጭቱ ምክንያት ቀንሷል ተብሏል። ግጭቱንም ፍራቻ በርካታ ስደተኞች መሰደዳቸውም ተነግሯል።

የስደተኞቹ መጠለያ ቤቶቹም ሆነ ትምህርት ቤቱ ጉዳት እንዳልደረሰበት የጠቀሱት ክሪስ ሆኖም " የህክምና ባለሙያዎች፣ መምህራን የሉም። የውሃ አገልግሎትም ተቋርጧል" ብለዋል።

ዩኤንኤችሲአር እንዲጎበኛቸው የተፈቀደላቸው እነዚህ ሁለት ካምፖች ከባድ ውጊያ የተካሄደባቸው አይደሉም።

ከኤርትራ ጋር በሚያዋስነው ድንበር በኩል በሰሜን ትግራይ የሚገኙት የሺመልባና ህፃፅ ካምፖችን ለመጎብኘት ዩኤንኤችሲአር በተደጋጋሚ ለኢትዮጵያ ያደረገው ጥሪ ሊሳካ አልቻለም።

ከግጭቱ በፊት በኤርትራ ያለውን ፖለቲካዊ ጭቆና በመፍራትም የተሰደዱና በትግራይ አራቱ ካምፖች ውስጥ የተጠለሉ ስደተኞች ቁጥር ወደ መቶ ሺህ ይጠጋ ነበር።

በትግራይ ክልል ግጭት የተቀሰቀሰው ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በወቅቱ ክልሉን ያስተዳድር የነበረው ሕወሓት የሰሜን ዕዝን ማጥቃቱ ከተገለፀ በኋላ ነበር።

የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት በኅዳር ወር አጋማሽ ላይ መቀለን ከተቆጣጠረ በኋላ በትግራይ ያካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ መጠናቀቁን መግለጹ ይታወሳል።

ነገር ግን አልፎ አልፎ ውጊያ እንደሚካሄድ የተነገረ ሲሆን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በክልሉ ያለውን የሰብአዊ ሁኔታ "የከፋ" ሲል ገልጾታል።

ጨምሮም "ምግብ አለመኖር ወይም በገበያዎች ላይ ያለው አቅርቦት ውስን መሆን እየባሰ የሚሄድ የምግብ እጥረት አደጋን እየፈጠረ መሆኑን ሪፖርቶች እያመለከቱ ነው" ብሏል።

በተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት ላይ እንደተጠቀሰውና የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል እንደሚለው በትግራይ ክልል 4.5 ሚሊዮን ሕዝብ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ያስፈልገዋል።

የተባበሩት መንግሥታትም ሆነ የተለያዩ የእርዳታ ድርጅቶች ህዝቡን መደረስ እንዳልቻሉም ሲናገሩና መንግሥት እንዲያመቻች ሲጠይቁም ተሰምተዋል።