ትግራይ፡ የአውሮፓ ሕብረት በትግራይ ክልል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ የሚሰጠውን የበጀት ድጋፍ አገደ

የአውሮፓ ሕብርት የበጀት ድጎማውን ያዘገየው በትግራይ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአውሮፓ ሕብርት የበጀት ድጎማውን ያዘገየው በትግራይ የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ ነው

የአውሮፓ ሕብረት ለኢትዮጵያ የሚያደርገውን የ107 ሚሊዮን ዶላር የበጀት ድጋፍን የሰብዓዊ ርዳታ ድርጅቶች በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚፈልጉ ሰዎች ያለ አንዳች ገደብ ዕርዳታ ማቅረብ እስኪችሉ ድረስ ማገዱን አስታወቀ።

የአውሮፓ ሕብረት ባወጣው ጽሑፍ ላይ የሕብረቱ ከፍተኛ ዲፕሎማት ጆሴፕ ቦሬል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በትግራይ የተከሰተውን ግጭት ለማስቆም ቀደም ሲል ካገኙት የሰላም ኖቤል ሽልማት አንጻር እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቀዋል።

አክለውም "ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነን፣ ነገር ግን ለሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢዎች ያለው ዕድል ክፍት እስካልሆነ ድረስ የአውሮፓ ሕብረት የታቀደውን የበጀት ድጋፍ ለኢትዮጵያ መንግሥት አይሰጥም" ብለዋል።

ሮይተርስ በጉዳዩ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጽህፈት ቤትን ምላሽ የጠየቀ ቢሆንም አስተያየታቸውን ለማግኘት እንዳልቻለ ገልጿል።

ከዚህ ቀደም የአውሮፓ ሕብረት ለኢትዮጵያ ከመደበው የበጀት ድጋፍ ውስጥ 90 ሚሊዮን ዩሮ (110 ሚሊዮን ዶላር) እንዲዘገይ ያሳለፈው ውሳኔ በተመለከተ እርምጃው በተሳሳተ ግምገማ ላይ የተመሰረተ ነው ሲል የኢትዮጵያ መንግሥት ቅሬታውን ገልፆ ነበር።

በወቅቱ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፣ ሕብረቱ የደረሰበት ውሳኔ "ሁኔታውን በተገቢው ሁኔታ ካለመገንዘብ" የተወሰደ ነው ሲሉ ገልፀውት ነበር።

በታኅሣስ ወር የኢትዮጵያ መንግሥት ከተባበሩት መንግሥታት ጋር ርዳታ ድርጅቶች በክልሉ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች እርዳታ ማድረስ እንዲችሉ ስምምነት ላይ መድረሱን ገልጾ ነበር።

በትግራይ ክልል ግጭት የተቀሰቀሰው ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በወቅቱ ክልሉን ያስተዳድር የነበረው ሕወሓት የሰሜን ዕዝን ማጥቃቱ ከተገለፀ በኋላ ነበር።

ከዚህ በኋላ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የክልሉ ነዋሪዎች ቤት ንብረታቸውን ጥለው ወደተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሲሸሹ፣ ከ50,000 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ወደ ሱዳን ተሰድደዋል።

በኅዳር ወር መጨረሻ ላይ የፌደራል መንግሥቱ የህወሓት ኃይልን አሸንፎ የክልሉን ዋና ከተማ፣ መቀሌን መቆጣጠሩን እንዲሁም ጦርነቱ ማብቃቱን ማስታወቁ ይታወሳል።

የተባበሩት መንግሥታት ግን አሁንም በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ጦርነት እየተካሄደ ስለመሆኑ መረጃ አለ ሲል ገልጿል።

በታኅሣስ ወር የአውሮፓ ሕብረት በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ ለኢትዮጵያ መንግሥት የመደበውን የበጀት ድጎማ ማዘግየቱ ተሰምቶ ነበር።

ቦሬል በትግራይ ክልል የተቀሰቀሰው ግጭት "ሕግን ከማስከበር በላይ ነው" በማለት ለአጠቃላይ ቀጠናው መረጋጋት ስጋት ነው ማለታቸውም ተሰግቧል።

"ማንነትን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ ግድያዎች፣ ዘረፋዎች፣ አስገድዶ የመድፈር ድርጊቶችና ስደተኞችን በግዴታ ወደ አገራቸው መመለስና የጦር ወንጀል ድርጊቶች ሊሆኑ የሚችሉ ክስተቶችን በተመለከተ በተከታታይ መረጃ ይደርሰናል" ብለዋል።

ጨምረውም "ይልቁንም ግጭቱ ወደ ቀጠናዊ ወደ መሆን የመሸጋገር እድል አለው፣ ለምሳሌ የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ግጭት ውስጥ መሳተፋቸው፣ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከሶማሊያ መውጣታቸው" በማለት አስረጅ ጠቅሰዋል።

በትግራይ አላማጣ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚያከፋፍለውን የእርዳታ እህል የተሸከመች ሴት

የፎቶው ባለመብት, AFP

የአውሮፓ ሕብረት ባለፉት ሰባት ዓመታት በኢትዯጵያ ላሉ የሌላ አገር ስደተኞች ካደረገው የ409 ሚሊዮን ዩሮ ድጋፍ በተጨማሪ፣ 815 ሚሊዮን ዩሮ የእርዳታ ድጋፍ አድርጓል።

የተባበሩት መንግሥታት ሐሙስ ዕለት በትግራይ ክልል በሚገኙና በርካታ ኤርትራውያን ስደተኞች በተጠለሉባቸው ሁለት መጠለያ ጣቢያዎች የዓለም አቀፍ ሕግ ጥሰት መኖሩን አስታውቆ ነበር።

ድርጅቱ አክሎም በሽመልባና ህጻጽ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች በቅርቡ ቃጠሎ መድረሱንና ውድመት መኖሩን የሳተላይት ምስሎች እንደሚያሳዩ ይፋ አድርጓል።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት በእነዚህ የመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ የሰብዓዊ እርዳታ እጥረት መኖሩን አስታውቆ፣ ባለፉት 10 ቀናት ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት መኖሩንም ገልጿል።

ድርጅቱ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነቱ ከየትኛው ወገን እንደሆነ ግን ያለው ነገር የለም።

የኤርትራው ማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ የማነ ገብረመስቀል ዛሬ አርብ፣ በትዊተር ገጻቸው ላይ "የተባበሩት መንግሥታት ስደተኞች ድርጅት በድጋሚ ኤርትራ ላይ ሌላ ኃላፊነት የጎደለው ስም የማጥፋት ዘመቻውን ቀጥሏል" ሲሉ ጽፈዋል።

የኤርትራና የኢትዮጵያ መንግሥታት በተደጋጋሚ የኤርትራ ጦር በትግራይ ግጭት ውስጥ አልተሳተፈም ቢሉም፣ አንድ የኢትዮጵያ ጄነራል ግን የኤርትራ ወታደሮች ሳይጋበዙ መግባታቸውን በክልሉ መገናኛ ብዙሃን ላይ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

ቦሬል አክለውም ሱዳንና ኢትዮጵያ በድንበራቸው አካባቢ የገቡበትን ውጥረት እንዲያረግቡ ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ ሰሞኑን የኢትዮጵያ ገበሬዎች በሚገኙበትና ሱዳን የእኔ ነው በማለት በኃይል በተቆጠጠረችው አካባቢ በምታሰፍራቸው ወታደሮች ምክንያት ትዕግስቷ እየተሟጠጠ መሆኑን ገልጻለች።

የሱዳን መከላከያ ሚኒስትር በበኩሉ የኢትዮጵያ ተዋጊ ጄት የአየር ክልሉን ጥሶ መግባቱን በመግለጽ ድርጊቱን "አደገኛና ተገቢ ያልሆነ ውጥረት መፍጠር" ሲል ገልጾታል።