ሱዳን በምሥራቃዊ ግዛቷ የአየር ክልል በረራ እንዳይካሄድ አገደች

የኢትዮጵያንና የሱዳንን ድንበር የሚያሳይ ካርታ

ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በሚያዋስናት ምሥራቃዊው የአል-ቀዳሪፍ ግዛት ላይ ማንኛውንም የአየር በረራ እንዳይካሄድ አገደች።

የሱዳን ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን ሐሙስ ዕለት "በአገሪቱ ምሥራቃዊ ክፍል የአል ቀዳሪፍና የአል ፋሽጋ አየር ክልል ላይ ማንኛውም በረራ እንዳይካሄድ" ውሳኔ መተላለፉን የሱዳን መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

የአገሪቱ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን ኃላፊ ኢብራሂም አድላን እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት ረቡዕ ዕለት የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሱዳንን አየር ክልልን ጥሶ ገብቷል በሚል አገራቸው ከከሰሰች በኋላ ነው።

በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ምንም ዓይነት ምላሽ አልሰጠም።

ይህንን ተከትሎም ሱዳን ኢትዮጵያን እንዲህ አይነት ድርጊት "መዘዙ የከፋ ይሆናል" በማለት አስጠንቅቃለች።

የሱዳን ወታደሮች ኢትዮጵያውያን የሚኖሩባቸውን የእርሻ መሬቶችን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ኢትዮጵያ ጉዳዩን አለዝባ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት ያላትን ፍላጎት በመግለጫዎች ብታሳውቅም ነገሮች እየተጠናከሩና እየተባባሱ በመምጣት ላይ ናቸው።

ባለፈው ሳምንት በድንበር አካባቢ ያለውን አለመግባባት በተመለከተ ጉዳዩ በሁለቱ አገራት መንግሥታት አማካይነት በሠላማዊ መንገድ እንደሚፈታና ለዚህም ጥረት እያደረገች እንደሆነ ስትገልጽ የነበረችው ኢትዮጵያ ከሱዳን ሠራዊት በኩል የሚደረገው እንቅስቃሴ እንዳሳሰባት ገልጻለች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንደተናገሩት በድንበር አካባቢ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እየበረታ መጥቷል።

ከሁለት ወር በፊት በትግራይ ክልል የተከሰተውን ግጭት በመጠቀም የሱዳን ጦር ድንበር ጥሶ መግባቱን የገለጹት ቃል አቀባዩ፣ አሁን ደግሞ "የሱዳን ወታደራዊ ኃይል በድንበር አካባቢ ወደ ተጨማሪ ቦታዎች ዘልቆ ለመግባት የተጠናከረ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው" ሲሉ ከስሰዋል።

ችግሩን በትዕግስትና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለመፍታት መሞከር "ፍርሃት ወይም መወላወል አይደለም" ያሉት አምባሳደር ዲና፣ አካባቢውን ከግጭት ለመጠበቅ ሲባል ኢትዮጵያ ጉዳዮች እንዳይካረሩ ለማድረግ እየጣረች ቢሆንም ይህ ታጋሽነት ገደብ እንዳለው ሲሉ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ ሱዳን ድንበሬን ጥሳ ገብታለች በሚል ስትከስ፣ የሱዳን ጦር በበኩሉ የኢትዮጵያ ሚሊሽያ ላለፉት 25 ዓመታት በቁጥጥሩ ስር አድርጎት የነበረውን የራሳችንን መሬት መልሰን ይዘናል ሲል መናገሩ ይታወሳል።

ከሳምንታት በፊት ወደ አወዛጋቢው የድንበር አካባቢ የሱዳን ሠራዊት ዘልቆ ከገባ በኋላ በእርሻ ማሳዎችና በንብረት ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን ሁለት ሺህ የሚሆኑ ነዋሪዎች መፈናቀላቸው ተነግሯል።

ከሁለት ሳምንት በፊት የሱዳን የማስታወቂያ ሚኒስትር ለሮይትርስ ዜና እንደተናገሩት ሠራዊታቸው ይገባናል የሚሉትን ከኢትዮጵያ ጋር የሚዋሰኑበትን አብዛኛውን አካመቆጣጠሩን ገልጸው ነበር።

ኢትዮጵያ ሱዳን በሁለቱ አገራት መካከል የነበረውን ስምምነት ጥሳለች በማለት በተደጋጋሚ የከሰሰች ሲሆን፤ በድንበር አካባቢ ያለው ሁኔታ ወደ ነበረበት ተመልሶ ችግሩ በውይይት እንዲፈታ በተደጋጋሚ ጠይቃለች።

የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

የፎቶው ባለመብት, ETHIOPIAN PM OFFICE

የምስሉ መግለጫ, የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

ለመሆኑ ከዚህ ድንበር ጋር በተያያዘ ያለው ታሪክ ምንድነው?

ኢትዮጵያና ሱዳን የሚጋሩት ድንበር ርዝመት 750 ኪሎ ሜትር ያካላል። ነገር ግን ይህ ድንበር አብዛኛው ርቀት ግልጽ በሆነ መንገድ መሬት ላይ አልተመላከተም።

ይህን ለማሳካት ተደጋጋሚ ንግግሮች ተጀምረው በተደጋጋሚ ተቋርጠዋል።

ዶ/ር ወንድወሰን ተሾመ የተባሉ ተመራማሪ፤ "የአፍሪካ ቅኝ ግዛት ዘመን ድንበሮች በተለይም የሱዳንና ኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ" በተሰኘና በእንግሊዝኛ በተጻፈ ጥናታቸው እንደገለጹት የሁለቱ አገሮች ድንበር የአሁን ጊዜ ወሰን እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1902 እና በ1907 የተደረጉ የአንግሎ-ኢትዮጵያ የካርታ ላይ ምልከታ ስምምነቶችን መሠረት ያደረጉ ናቸው።

በቅኝ ግዛት ወቅት በሱዳንና በኢትዮጵያ መሬት ላይ ለተመላከቱ ድንበሮች ኃላፊነቱ ተሰጥቶት የነበረው ሁነኛ ሰው የአይሪሽ ተጓዥና አሳሽ የነበረው ቻርለስ ግዊይን ነበር።

የሱዳን ገዳሪፍና ብሉ ናይል ግዛቶች ከአማራ ክልል ጋር ይዋሰናሉ። በ1908 ነበር በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ድንበር የተሰመረው።።

የአልፋቃ ማዕዘን

ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በይገባኛል የምትወዛገብብት አካባቢ ረዥም የግዛት ድንበር ነው ያላት። ሁለቱም አገሮች ለም ነው የሚባለውን ፋሽቃ አካባቢን እጅጉኑ ይፈልጉታል።

ይህ በሁለቱ አገሮች ዓይን ውስጥ ያለው አካባቢ የአልፋሽቃ ማዕዘን ወይም የአልፋሽቃ ጥግ ተብሎ ይጠራል።

በዚህ ድንበር ሁለቱም አቅጣጫ የሚገኙ ገበሬዎች ባሻገራቸው ያሉ ለም መሬቶች ላይ ያማትራሉ። አልፋሽቃ ማዕዘን በደቡብ ምሥራቅ ሱዳን ምሥራቃዊ ገዳሪፍ የሚገኝ ለም መሬት ነው።

አልፋሽቃ መሬት 250 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍንና 600 ሺህ ኤክር ለም መሬትን የሚሸፍን ነው። ለለምነቱ ምክንያት የሆኑት እንደ አትባራ፣ ሰቲት እና ባስላም ወንዞችም በቅርብ ይገኛሉ።

ሁለቱ መንግሥታት ከዚህ ቀደም ይህንን አወዛጋቢ ድንበር በድጋሚ ለማስመር፣ የጋራ ፕሮጀክቶችን ለመጀመር እና የአካባቢው ሕዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር።

ቀደም ካለው አስተዳደር ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሬው ሕዝብ ሉአላዊ መሬቱን ቆርሶ እየሰጠ ነው በሚል ተደጋጋሚ ወቀሳ ሲቀርብበት ነው የቆየው።

እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ2014 የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የወቅቱ ሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸውን ድንበሩ መሬት ላይ የሚመላከትበትን የመጨረሻ ቀን እንዲያሳውቁ መመርያ አስተላልፈውላቸው ነበር።

ሆኖም አወዛጋቢውን ድንበር መሬት ላይ የማመላከቱ ሥራ እስከዛሬም አልተሳካም፡፡