ጋዜጠኞች ከእነ ጃዋር መሐመድ ችሎት እንዲወጡ ተደረገ

የፎቶው ባለመብት, MAHEDER HAILESELASSIE TADESE
በረሃብ አድማ ላይ ናቸው የተባሉት እነ ጃዋር መሃመድ በዛሬው ችሎት ሃሳባቸውን ማስረዳት እንደተሳናቸው ከጠበቆቻቸው አንዱ የሆኑት አቶ መሐመድ ጅማ ለቢቢሲ አስረድተዋል።
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የፀረ ሽብርና ሕገ-መንግሥታዊ አንደኛ ችሎት ዛሬ ማለዳ በእነ አቶ ጃዋር መሐመድ የክስ መዝገብ የተከሰሱ የ24 ተከሳሾች የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ቀጠሮ ይዞ ነበር።
በቀጠሮው መሰረት የቀረቡት አቶ ጃዋር መሃመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ሃምዛ አዳነ እና አቶ ሸምሰዲ ጠሃ የረሃብ አድማ ላይ ከሆኑ ዛሬ 8ኛ ቀናቸው መሆናቸውን የተናገሩት አቶ መሀመድ፣ "ሰውነታቸው በጣም ስለተዳከመ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። እነሱ ብዙ መናገር ስላልቻሉ እኛ ሃሳባቸውን አስረድተናል።" ብለዋል።
ጠበቃቸው አቶ መሃመድ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ደንበኞቻቸው እነ አቶ ጃዋር መሀመድ እና አቶ በቀለ ገርባ የረሃብ አድማ ከጀመሩ 8ኛ ቀናችው መሆኑን ጠቅሰው "በጣም ተዳክመን፣ ራሳችንን ስተን የህክምና እርዳታ የሚያስፈልገን ከሆነ እኛ በመረጥነው ሃኪም ብቻ የህክምና ርዳታ ይደረግልን' ሲሉ ፍርድ ቤቱን እንደጠየቁም አስረድተዋል።
ፍርድ ቤቱም አቤቱታቸውን ካደመጠ በኋላ በግል ሃኪም እንዲታዩ ፈቅዷል።
አቶ መሐመድ በረሃብ አድማ ላይ ያሉት እነ ጃዋር ስላሉበት ሁኔታ ተጠይቀው "እኔ በግሌ እንዳስተዋልኩት፣ በተለይ ጃዋር በጣም ተጎድቷል። በጣም ስለተዳከሙ ብዙ መናገር አልቻሉም። በጣም ተጎድተዋል።" ብለዋል።
ፖለቲከኞቹ አቶ ጀዋር መሐመድ፣ አቶ በቀለ ገርባ፣ አቶ ሐምዛ አዳነ እና አቶ ሸምሰዲን ጠሃ የረሃብ አድማ እያደረጉ ያሉት የፖለቲከኞችን እስር እና በመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚደርሰውን ጫና በመቃወም እንደሆነ ሌላኛው ጠበቃቸው አቶ ቱሊ ባይሳ ትናንት ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ጠበቃው ቱሊ ባይሳ ፖለቲከኞቹ እያደረጉት ያሉት የረሃብ አድማ እንዳደከማቸው ገልጸው፤ ደንበኞቻቸው ለማነጋገር በሄዱበት ወቅት ወጥተው ሊያነጋግሯቸው ስላልቻሉ "ተኝተው ባሉበት" ለማነጋገር ተገድደናል ሲሉ ለቢቢሲ ደንበኞቻቸው ያሉበትን ሁኔታ አብራርተዋል።
የእነ ጃዋር የፍርድ ቤት ውሎ ምን ይመስላል?
ማለዳ የተጀመረውን የችሎት ውሎውን ለመዘገብ እና ለመከታተል በችሎቱ የተገኙ ጋዜጠኞች እና የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም ሠራተኞች ተፈትሸው ወደ ችሎቱ ከገቡ በኋላ በጸጥታ አስከባሪዎች ከችሎቱ እንዲወጡ ተደርገዋል።
የፌደራል ፖሊስ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባላት የቢቢሲውን ሪፖርተር ጨምሮ 8 ጋዜጠኞችን እና የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባልደረባ ከችሎቱ በማስወጣት የፍርድ ሂደቱን እንዳይከታተሉ መከልከላቸውን የቢቢሲ ጋዜጠኛ ተናግሯል።
ጋዜጠኞች የፍርድ ሂደቱን እንዳይከታተሉ ከፍርድ ቤት እንዲወጡ የተደረገበት ምክንያት ባይገለጽላቸውም፤ አንዳንድ የፖሊስ አባላት ግን "ከላይ በመጣ ትዕዛዝ" ጋዜጠኞችን እንዳስወጡ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
በመጀመሪያ ተከሳሾች እና ጠበቆች ችሎቱ ለህዝብ ክፍት መሆኑን መጠየቃቸውን የተናገሩት አቶ መሐመድ፣ ከዚህ በፊት በነበረው ቀጠሮ ላይ ቢጫ የለበሱ ሰዎች እንዳይገቡ መከልከላቸውን በመጥቀስ ፍርድ ቤቱም መከልከላቸው ተገቢ አለመሆኑን መናገሩን አስረድተዋል።
ጠበቆቹ ይህ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተከብሮ እንደሆነም ጠይቀዋል።

የፎቶው ባለመብት, Yadi Pictures, BBC, Hamza Borena FAcebook
አክለውም ፍርድ ቤት በተለየ ሁኔታ ችሎቱን ዝግ ካላደረገ በስተቀር ተከሳሽ በክፍት ችሎት የመዳኘት መብት አለው በማለት ለችሎቱ ማቅረባቸውን ገልፀዋል።
የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ከአንድ ሳምንት በፊት ተይዞ የነበረው ቀጠሮ ቢጫ ቀለም ልብስ በለበሱ ግለሰቦች ችሎቱ ወደዛሬ እንዲሸጋገር መደረጉ የሚታወስ ነው።
የፍርድ ሂደቱን ለመከታተል ቢጫ ልብስ ለብሰው በፍርድ ቤት የተገኙ ሰዎች ወደ ፍርድ ቤቱ እንዳይገቡ በፖሊስ መከልከላቸውን ተከትሎ ተከሳሾች እና ጠበቆች ያሰሙትን አቤቱታ ተከትሎ ነው ተለዋጭ ቀጠሮ ለዛሬ የተሰጠው።
በማሕበራዊ ሚዲያዎች ላይ በርካቶች ቢጫ ልብስ የመልበስ ዘመቻ ሲያከናውኑ የቆዩ ሲሆን ይህም ተከሳሾች በማረሚያ ቤት እና ፍርድ ቤት ሲቀርቡ የሚለብሱትን ባለ ቢጫ ቀለም ቱታ ለመወከል ነው።
ፍርድ ቤቱ በእነጃዋር መሃመድ የችሎት ሂደት ላይ ድጋፍንም ሆነ ተቃውሞን የሚያመላክቱ አልባሳትን ለብሶ መገኘት ከአመጽ ጋር ሊያያዝ ይችላል በማለት የድጋፍ ልብስ እንዳይለበስ ብሎ መወሰኑን አቶ መሐመድ ጅማ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ፍርድ ቤቱ ማንኛውም በችሎት የሚታደም አካል አድማ የሚመስሉ ድጋፍንም ሆነ ተቃውሞን የሚያመላክቱ አልባሳትን ለብሶ ችሎት መታደም እንደማይችል ገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ አቶ መሐመድ በዛሬው የእነ ጃዋር ችሎት ቤተሰቦች እና ጋዜጠኞች እንዳይገቡ ተደርገዋል ብለዋል።
ፍርድ ቤቱ ከዚህ በኋላ ጋዜጠኞች እና የቤተሰብ አባላት በአቅራቢያው ካሉ ይግቡ ብሎ ነበር ማለቱን ጠቅሰው፣ አንዴ እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ 'ካሉ ተመልሰው ይግቡ' መባሉ ትክክል አይደለም ማለታቸውን ገልፀዋል።
ከችሎቱ እንዲወጡ የተገደዱት ጋዜጠኞች ችሎቱን እንዳይከታተሉ ለምን እንደተከለከሉ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት እና ምክትላቸውን የጠየቁ ሲሆን ኃላፊዎቹም ጉዳዩን አጣርተው ምላሽ እንደሚሰጧቸው ተናግረዋል።
በዛሬው ቀጠሮ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ ጋዜጠኞች ወደ ችሎት ብቻም ሳይሆን ወደ ፍርድ ቤቱ ቅጥር ግቢ ተንቀሳቃሽ ስልክ ይዘው እንዳይቀርቡ ተከልክለው ነበር።
ከዚህም በተጨማሪ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ መልኩ በርካታ የፖሊስ አባላት በፍርድ ቤቱ ዙሪያ ተሰማርተው ታይተዋል።
በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ የፀረ ሽብርና የህገ መንግስት ጉዳዮች የወንጀል ችሎት፣ የተጠርጣሪዎቹን የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ለየካቲት 22 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በቁጥጥር ሥር የዋሉት እነ አቶ ጃዋር ከቀረቡባቸው ተደራራቢ አስር ክሶች ስድስቱ እንዲቋረጡ ፍርድ መወሰኑ ይታወሳል።
የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ፤ የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል አዋጅ ፤ የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ የመተላለፍ ክሶች ከተመሰረቱባቸው ክሶች መካከል ሲሆኑ፤ እንዲቋረጡ የተደረጉት ክሶች የጦር መሳሪያ አስተዳደር እና ቁጥጥር አዋጅ 1177/2021 ጋር የተያያዙ ናቸው።












