ትግራይ፡ ፀረ መንግሥት ተቃውሞች በትግራይ የሰዎች ሕይወት መቅጠፋቸው ተነገረ

የመቀለ ከተማ ከተቃውሞው በፊት

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency

የምስሉ መግለጫ, የመቀለ ከተማ ከተቃውሞው በፊት

በትግራይ ክልል በዚህ ሳምንት በተነሳው ተቃውሞ ቢያንስ ስምንት ሰዎች መገደላቸው ተገለፀ።

ከአዲስ አበባ የተላኩ የሃይማኖት አባቶችና የሃገር ሽማግሌዎችን ወደ መቀለ መምጣትን በመቃወምም ሰልፈኞች በጎዳናዎች ላይ ጎማ ሲያቃጥሉ እንዲሁም በርካቶች ቤት ውስጥ በመቀመጥ ተቃውሟቸውን ገልፀዋል።

ልዑካኑ ከክልሉ የተለያዩ የማህበረሰብ አባላት ጋር የሰላም ውይይት ለማድረግ ነው የመጡት ተብሏል።

እንግዶቹ በሳምንቱ መጀመሪያ ሰኞ ምሽት፣ የካቲት 1/2013 ዓ. ም ላይ ወደ ከተማዋ መግባታቸውን ተከትሎ ነዋሪው ላይ ቁጣ ማስከተሉን የአይን እማኞች ይናገራሉ።

በርካታ ተጋሩዎች የልዑካኑን ቡድን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የተወሰደውን ወታደራዊ እርምጃ በመደገፍ ከመንግሥት ጎን ቆመዋል በማለት ይወነጅሏቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ የክልሉን ህዝብ ጥሪ ችላ ብለዋልም ይሏቸዋል።

"መቀለ አሁንም ቢሆን ሙሉ በሙሉ እንቅስቃሴ የሌለባት ከተማ ናት። የተወሰነ በሚባል መልኩ ወይም ደግሞ ምንም አይነት የሰዎች እንቅስቃሴ የለም።

ሱቆችም ሆኑ የግል ተቋማት ተዘግተዋል። በከተማዋ ውስጥ የትራንስፖርት አገልግሎት የለም" በማለት አንድ ነዋሪ ለቢቢሲ በዚህ ሳምንት ረቡዕ ዕለት ተናግረዋል።

ከመቀለ በተጨማሪ በሽረ፣ አዲግራት እንዲሁም ከመቀለ 45 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ውቅሮ በተከሰተ ተቃውሞ ስምንት ሰዎች መገደላቸውን የውቅሮ ነዋሪ የሆነና ስሜ አይጠቀስ ያሉ አንድ የህክምና ባለሙያ ተናግረዋል።

የመቀለ ከተማ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጠዓመ በበኩላቸው ተቃውሞውን አውግዘው "ለዘረፋ ለስርቆት እንዲመቻቸው ተራ ዱርየዎች ያወጁት ነው" ማለታቸውን የአካባቢው ሬድዮ በዘገባው አሰምቷል።

የፌደራል መንግሥቱ የክልሉን መዲና መቀለን ህዳር 19፣ 2013 ዓ. ም መቆጣጠሩን ተከትሎ ውጊያው ማቆሙን ገልጿል።

ይህ ሁኔታ በፌደራል መንግሥቱና በህወሓት በሚመራው የትግራይ ኃይሎች በጥቅምት 24፣ 2013 ዓ.ም የተነሳው ግጭት መቋጫ ተደርጎም ታይቷል።

ምንም እንኳን መንግሥት ወታደራዊ እርምጃው ተጠናቋል ይበል እንጂ የተባበሩት መንግሥታትን ጨምሮ ሌሎች የረድዔት ድርጅቶች በአንዳንድ የትግራይ ክፍሎች ውጊያው እንደቀጠለ ይናገራሉ።

በፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል ለረዥም ጊዜ የዘለቀው መቃቃርና አለመግባባት ተካሮ የህወሓት ኃይሎች የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል በማለት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የፌደራሉን ጦር ወደ ትግራይ ማዝመታቸው ይታወሳል።

ህዝቡን ያስቆጣው ምንድን ነው?

የሰሞኑ ተቃውሞ የፌደራል መንግሥቱ መቀለን መቆጣጠሩን ተከትሎ የተነሳ የመጀመሪያ ህዝባዊ እምቢተኝነት ነው።

በህዝባዊ ስብሰባው ላይ የአካቢቢውን የሃይማኖት አባቶች ወክለው እንዲሳተፉ ተጠርተው የነበሩ ግለሰብ እንደሚናገሩት የሰላም ውይይት የሚለው ጉዳይ የህዝቡን "ቁጣ እንዳገነፈለው" ነው።

"እነዚህ የሃይማኖት አባቶች ህዝቡ አንድ ላይ እንዲመጣ ይፈልጋሉ። በችግራችን ወቅት የት ናችሁ? ብለው አልጠየቁንም። በአሁኑ ወቅት በአለም አቀፍ ሚዲያዎች ታጅበው በትግራይ ሰላም ሰፍኗል የሚል ገፅታን ለመፍጠር እየሞከሩ ነው ይህ ደግሞ ሀሰት ነው" ብለዋል።

ግለሰቡ ራሳቸው ህዝባዊ ጉባኤው ሊጀመር 20 ደቂቃ ሲቀረው ለጉባኤው እንዲሳተፉ እንደተጠሩና ግብዣውንም ውድቅ ማድረጋቸውን ይናገራሉ።

"ትግራይ በጦርነት ላይ ናት። ህዝብ በየቀኑ እየሞተ ነው። እንደ ሃይማኖት አባት እንዲህ አይነት ግብዣን አልቀበልም። የደረሰውን ግፍ ሳያወግዙ የሰላም ድርድር ምን ማለት ነው? በርካታ ካህናት ሲገደሉ፣ አብያተ ክርስቲያናትና የእምነት ተቋማት ሲቃጠሉና ሲወድሙ እነዚህ የእምነት ተቋማት አንዲት ቃል ትንፍሽ አላለሉም" ይላሉ።

መንግሥት በትግራይ ኃይሎች ላይ ለወሰደው ወታደራዊ እርምጃ በርካታ የእምነት ተቋማት ድጋፋቸውን ያሰሙ ሲሆን ይህም በርካታ ተጋሩዎችን አስቆጥቷል።

የትግራይ ክልል የህዝብ ግንኙነት እቴነሽ ንጌሴ በበኩላቸው "ነዋሪው ከቤት እንዳይወጣና የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቆም ሃሰተኛ መረጃ ተሰራጭቷል" ብለዋል።

አክለውም " ህዝባዊ ጉባኤው የተካሄደው በሃይማኖት አባቶቹና በአካባቢው ተወካዮች መካከል ነው። ከተማዋን ለመጎብኘት ሲመጡ እነዚህ ልዑካን የመጀመሪያዎቹ አይደሉም። በዚህ ወቅት የመጡት በትግራይ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ለመመልከትና ቁልፍ የሚባሉ ጉዳዮችም ላይ ለመወያየት ነው" በማለት ይናገራሉ።

በፌደራል መንግሥት የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር ሰላምና መረጋጋት እንዲመጣ ነዋሪዎች ከአስተዳደሩ ጋር እንዲሰራ ይፋዊ መግለጫ መሰጠቱን ያወሳሉ።

"ችግሮች ካሉ ቢነግሩን እናሻሽላለን። ያለበለዚያ እንዲህ አይነት ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎች ሰላሙን የሚያጠለሹና ወደኋላም የሚጎትቱን ናቸው" በማለት ይናገራሉ።

በተቃውሞው ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ምን ያህል ነው ተብለው ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሟቾችም ሆነ የቁስለኞች ቁጥርን በተመለከተ መረጃ እንደሌላቸው ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ማክሰኞ የተፈጠረው ምንድን ነው?

ተቃውሞውን ማን እንዳስተባበረው ግልጽ አይደለም።

አብዛኛው ነዋሪ ከቤት አልወጣም ነበር። መደብሮችና ሌሎችም የግል ድርጅቶች ዝግ ነበሩ። አንድ ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የአይን እማኝ "ትራንስፓርት አልነበረም" ሲሉ በስልክ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የጸጥታ ኃይሎች ነዋሪዎች ሱቃቸውን እንዲከፍቱ ሲያስገድዱ እንደነበር የገለጹት የአይን እማኙ "በፕላኔት ሆቴል የተካሄደውን ጉባኤ ሰዎች እንዲሳተፉ ሲገደዱ ነበር። ይህም በአብዛኛው የከተማው አካባቢዎች ወጣቶች በድንጋይ መንገድ እንዲዘጉና ጎማ እንዲያቃጥሉ ምክንያት ሆኗል" ብለዋል።

አንዳንዶቹ ወጣቶች የጸጥታ ኃይሎች ላይ ድንጋይ ሲወረውሩ፤ የጸጥታ ኃይሎቹ በምላሹ ተቃዋሚዎቹ ላይ ጥይት እንደተኮሱም የአይን እማኙ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

በመቀለ በሚገኝ ሆስፒታል የሚሠሩ ባለሙያ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ስምንት ጉዳት የደረሰባቸው ግለሰቦች ሆስፒታል ሄደዋል።

አዲሀዋሲ ሰፈር የሚኖሩ አንድ ግለሰብ እንዳሉት በተለያዩ ቦታዎች ፍተሻ እየተካሄደ ነበር። በከተማዋ በከፍተኛ ሁኔታ ጥበቃ ሲደርግና የጸጥታ ኃይሎች እየተዘዋወሩ ሲቆጣጠሩም ነበር ሲሉም አክለዋል።

አይደር አካባቢ የሚኖሩ ሌላ ግለሰብ ረቡዕ ምሽት የተኩስ ድምጽ እንደሰሙና የጸጥታ ኃይሎች ከመንገድ ዘወር እንዲባል ማድረጋቸውን አስረድተዋል።

የመቀለ ከተማ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ነዋሪዎች ሱቃቸውን እንዲከፍቱና አለበለዚያ ግን የከተማ መስተዳድሩ በሕግ እንደሚጠይቃቸው ማስጠንቀቃቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

በተቃውሞው ተሳትፈዋል የተባሉ 12 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውንም ጨምረው ተናግረዋል።

ነዋሪዎች እንደሚሉት "ብዙ ሰዎች በቁጥጥር ስር እየዋሉና እየተደበደቡም "ነው።

በሌሎች ከተሞች የተነሱ ተቃውሞዎች

ተቃውሞ ከተነሳባቸው ከተሞች አንዷ ውቅሮ ናት። ተቃውሞው የተቀሰቀሰው ረቡዕ ጠዋት፣ የካቲት 3/2013 ዓ.ም ነበር።

አንድ ነዋሪ ለቢቢሲ እንደገለጹት የሃይማኖት መሪዎች ወደ ውቅሮ ሄደው ከነዋሪዎች ጋር የሰላም ውይይት እንደሚያደርጉ እየተወራ ነበር።

ይህንን ተከትሎም ሁሉም መደብሮችና መንገድም እንደተዘጋ እንዲሁም አንዳንድ ተቃዋሚዎች ጎማ እንዳቃጠሉ ነዋሪው ገልጸዋል።

ረቡዕ እለት ስልክ ከጠዋቱ 2 ሰዓት እስከ 9 ሰዓት ተቋርጦ ነበር።

ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የሕክምና ባለሙያ "መንገድ ላይ ነበርኩ። ከዚያም የተኩስ ድምጽ ሰማን። ሁላችንም ወደየቤታችን መሮጥ ጀመርን። ኢላማ የተደረጉት መንገድ ላይ ቀርተው የነበሩ ሰዎች ናቸው" ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለሙያውን ስናናግራቸው ከጎረቤቶታቸው ሁለት ሰዎች እንደተገደሉ ገልጸውልናል። ሟቾቹ ጋሪ በመንዳት ይተዳደሩ ነበር።፣

በርካቶች ጉዳት ሲደርስባቸው፤ ስምንት ሰዎች ደግሞ እንደሞቱ ተገልጿል። ከሞቱት ሰዎች መካከል አንድ የቀበሌ 16 ነዋሪ፣ ሁለት በቅሳነት ትምህርት ቤት እቅራቢያ ይኖሩ የነበሩ እና አንድ ሌላ በመቀለ ጫፍ የሚኖሩ ሰው እንደሚገኙበትም ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ነዋሪዎች እንደሚሉት፤ ከተገደሉት ሰዎች መካከል እርዳታ ለመውሰድ ከገጠር ከተሞች የሄዱ ይገኙበታል።

ሐሙስ ዕለት የሁለት ሰዎች ሥርዓተ ቀብር፣ ረቡዕ ዕለት ደግሞ የሦስት ሰዎች ሥርዓተ ቀብር በእንዳ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል። ሌሎች ሁለት ግለሰቦች በእንዳ አቡነ አረጋዊ ቤተ ክርስቲያን ተቀብረዋል።

በጉዳዩ ላይ የፌደራል መንግሥት እስካሁን አስተያየት አልሰጠም። ቢቢሲ የክልሉን ቃል አቀባይ ጨምሮ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ምላሽ ለማግኘት እየሞከረ ነው።

ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ ሐሙስ እለት ነገሮች መሻሻል አሳይተዋል። ጥቂት ሰዎች ከቤት መውጣትም ጀምረዋል።

ግጭቱ ከተጀመረ 100 ቀናት ያለፉ ሲሆን፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ትግራይ ውስጥ ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። በተጨማሪም ከ60 ሺህ በላይ ሰዎች ወደ ሱዳን ተሰደዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአውሮፓ ሕብረት በክልሉ የተከሰው ሰብዓዊ ቀውስ እንደሚያሰጋቸው ገልጸው፤ እርዳታ ሰጪዎች ያለ ምንም ገደብና ክልከላ ወደ ክልሉ እንዲገቡ ጠይቀዋል።

መደፈር፣ ብሔርን መሠረት ያደረገ ግድያ፣ መታፈን እና ዘረፋ ሪፓርት መደረጋቸውን በተመለከተ በገለልተኛ አካል እንዲጣራም አሳስበዋል።

ባለፈው ሳምንት የዓለም ምግብ ፕሮግራምና የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ከ3 ሚሊዮን በላይ ለሆኑ ነዋሪዎች ምግብ ማድረስ ለመጀመር ስምምነት አድርገዋል።